አሰን ጣሂሩ ዋሻ !

0
159

ባሕር ዳር: መጋቢት 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ወሎ ዞን የበርካታ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት ነው። ዛሬ በዞኑ ውስጥ ወደሚገኘው ለገሂዳ ወረዳ ተጉዘን የአሰን ጣሂሩ ዋሻ የቱሪስት መስህብን እንቃኛለን። ይህ ዋሻ በተፈጥሮ ክስተት የተፈጠረ ልዩ ክስተት እንደኾነ የሚናገሩት የለገሂዳ ወረዳ ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሰይድ ሁሴን አሊ ለወረዳውም ኾነ ለዞኑ የቱሪዝም መጨመር የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊወጣ የሚችል ቦታ ነው ብለውታል።

ኀላፊው የዋሻው ስያሜ የመጣው አሰን ጣሂሩ የተባሉ በአካባቢው የታወቁ ሰው ይሮሩበት ስለነበር እንደኾነ ጠቁመዋል፡፡ ይህ ዋሻ ከ1930ዎቹ ጀምሮ ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ሲኖሩ ኅብረተሰቡን በማስጠለል አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር ነው ያስረዱን፡፡ ዋሻው አራት በሮች እንዳሉት እና አኹን ላይ ግን ለጎብኝዎች አገልግሎት እየሰጠ ያለው አንዱ በር ስለመኾኑ ተብራርቷል።

የዋሻው ከፍታው 10 ሜትር ሲኾን ስፋቱ ደግሞ 18ሜትር እንደኾነ ጠቁመዋል። የዋሻው ርዝመት ከለገሂዳ ጀምሮ ወደ ዞኑ ሌላው የለጋምቦ ወረዳ ድረስ እንደሚደርስ ነው የነገሩን። ዋሻው ቀደም ብሎ በውስጡ ምን አይነት አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር የሚያመላክቱ ቁሳቁሶችን የያዘ ነው። ከፍ ያሉ አልጋዎች፣ የእህል ማስቀመጫ የነበሩ ፍርስራሽ ጎታዎች፣ የማብሰያ እቃዎች በተደረገ ጉብኝት መገኘቱን ነው ኀላፊው ያብራሩት።

ይህ ዋሻ የቅርስ ጥናት እና ጥበቃ ባለሥልጣን ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ እና ሁሉም ሰው ሊጎበኘው የሚችል የተፈጥሮ ገጸ በረከት ስለመኾኑም ነው ያስረዱን፡፡ ዋሻው በስማቸው የተሰየመላቸው ግለሰብ ልጃቸው የኾኑት ጀማል አሰን ለአሚኮ እንዳሉት ዋሻው ቀደም ሲል በአደጋ ጊዜ መጠለያ ኾኖ ያገለግል እንደነበር እና የቀየው ሰው ከፍተኛ አክብሮት ይሰጠው የነበረ ስለመኾኑ ተናግረዋል።

አቶ ጀማል እንደሚሉት ቦታው ቢተዋወቅ እና የሀገር ውስጥም ኾነ ከውጭ የሚመጡ ሰዎች ቢጎበኙት ከአካባቢው ሕዝብ በተጨማሪ ዞኑንም ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል ነው ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here