አሸተን ማርያም

0
111

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ‎ላስታ እና ቡግና በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጎልተው ከሚታወቁ አካባቢያዊ ስሞች ተጠቃሽ ናቸው። በእነዚህ ሥፍራዎች በነገሥታት የተሠሩ በርካታ መካነ ቅርሶች እንደሚገኙ የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ መረጃ ያሳያል።

ቅዱሳን ነገሥታት የኖሩባቸው አካባቢዎቹ አያሌ ቅርሶችን አቅፈው ይዘዋል። ቅርሶቹ ጥንታዊነታቸውን እንደጠበቁ ዘመናትን ተሻግረዋል። የዓለም አቀፍ ጎብኝዎች መዳረሻም ናቸው። ከላሊበላ ከተማ በቅርብ ርቀት ከሚገኙት በርካታ የመስህብ ቦታዎች መካከል ለዛሬው አሸተን ማርያም እንቃኛለን።

አሸተን ማርያም በላስታ ወረዳ ከላሊበላ ከተማ በሥተ ምሥራቅ ስምንት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ 3 ሺህ 90 ሜትር ከፍታ ካለው ተራራ ላይ የምትገኝ ውቅር ቤተክርስቲያን ናት። ከላሊበላ ከተማ አሸተን ማርያም ድረስ በበቅሎ፣ በእግር ወይም በመኪና መሄድ ይቻላል፡፡

አሸተን ማርያም ለመድረስ በልዩ ግርማ ሞገስ የቆመውን ተራራ መውጣት ግድ ይላል። ከተራራው ጫፍ ለመድረስ ትንሽ ሲቀር 20 ሜትር ርዝመት ያለው መሿለኪያ ይገኛል፡፡ ከመሿለኪያው ዳርቻ ደግሞ በቅዱስ ላሊበላ እንደተጀመረ የሚነገር ግንባታ አለ፡፡

የአካባቢው ማኅበረሰብም አሸተን ማርያምን በላሊበላ እንደተሠራች ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ቤተ ክርስቲያኗ የተሠራችው በአጼ ነአኩቶለአብ ዘመነ መንግሥት መኾኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ መጀመሪያ ስትሠራ በሦስት በኩል አምዶች የነበሯት ቢኾንም በአምዶቹ መካከል የነበረው ክፍት ቦታ በድንጋይ እና በጭቃ ተሞልቷል።

አሸተን ማርያም ረጅም ዘመን ያስቆጠሩ በጨርቅ እና በእንጨት ላይ በውኃ ቀለም የተሳሉ ሥዕሎች፣ የብራና መጻሕፍት እና በተለያየ ቅርጽ የተሠሩ ታሪካዊ መስቀሎች ይገኛሉ፡፡

ቅርሶች ጎብኝዎች በሚጎበኙበት ጊዜ ሁሉ ለዕይታ የሚቀርቡ ናቸው፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here