የአጼ ፋሲል ግቢ በመባል የሚታወቀው ቦታ ስፋት 70 ሺህ ካሬ ሜትር ይሸፍናል፡፡ ስፍራው በ17ኛው እና በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ መሪዎች ከነበሩት መካከል የስድስቱን አብያተ መንግሥታት እና ሌሎች የሕንፃ ፍርስራሾችን የያዘ ነው፡፡
የአፄ ፋሲል ግቢ ቀደም ብሎ አገልግሎት የሚሰጡ 12 በሮች ነበሩት፡፡ እነዚህ በሮች አገልግሎት የሚሰጡት የኅብረተሰብ ክፍል እንደነበራቸው በግቢው ውስጥ አስጎብኝ የኾኑት ኪዳነማርያም ኃይሉ ይገልጻሉ፡፡
አስጎብኝው አቶ ኪዳነማርያም ስለበሮቹ እና ስለሚሰጡት አገልግሎት የሚከተለውን ብለዋል፡፡
👉 ፊት በር ወይም ጃን ተከል በር ንጉሰ ነገስቱ የሚገቡበት በር ነው፡፡
👉 ወንበር በር ዳኞች የሚገቡበት በር ነው፡፡
👉 ራስ በር መሳፍንት እና መኳንንት የሚገቡበት በር ነው፡፡
👉 አዛዥ ጠቋሬ በር የግቢው አዛዦች የሚገቡበት በር ነው፡።
👉 አደናግር በር ጥጥ ፈታዮች የሚገቡበት በር ነው፡፡
👉 ኳሊ በር የነገሥታት አጃቢዎች የሚገቡበት በር ነው፡፡
👉 እምቢልታ በር የሙዚቃ መሳሪያ የሚጫወቱ ሰዎች የሚገቡበት በር ነው፡፡
👉 ባልደራስ በር የቤተመንግሥት ፈረሶች አለቃ የሚገቡበት በር ነው፡፡
👉 እርግብ በር ስጦታዎች የሚገቡበት በር ነው፡፡
👉 ተስካር በር ለሙታን መታሰቢያ የሚመጡ ሰዎች የሚገቡበት በር ነው፡፡
👉 እንኮይ በር እትጌ ምንትዋብ እና ልዕልት እንኮየ የሚገቡበት በር ነው፡፡
👉 እቃ ግምጃ ቤት በር ወደ ግምጃ ቤት ማርያም የሚያስኬድ በር ነው፡፡
አስጎብኝው ብዙ ምስጢር የያዘውን ይህን ቦታ ጥምቀት እየተቃረበ በመኾኑ ለሀገር ውስጥም ለውጭ እንግዳም ለማስጎብኘት ዝግጅት እያደረጉ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡ ሰዎች የእረፍት ጊዜያቸውን በዚሁ ስፍራ በመገኘት ታሪካቸውን እንዲያውቁ እና ራሳቸውንም እንዲያዝናኑ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በምሥጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!