“የሀገር ምልክቱ ዋሊያን ስለመታደግ”

0
82

ጎንደር: መጋቢት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የሚገኘውን የዋሊያ አይቤክ ደኅንነት ለመጠበቅ ያለመ ውይይት በጎንደር ከተማ እየተካሔደ ነው።

በውይይቱ የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ስለሽ ግርማ፣ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኩመራ ዋቅጅራ፣ የአፍሪካ ዋይልድ ላይፍ ፋውንዴሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ፊሊፕ ሙራቲ (ዶ.ር)፣ የአፍሪካ ዋይልድ ላይፍ ላንድስኬፕ ዳይሬክተር ብሪያን ሜይ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የዪኒቨርሲቲ ምሁራን፣ የአማራ ክልል የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን፣ የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የሥራ ኀላፊዎች እና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

በውይይቱ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሽ ግርማ የስሜን ብሔራዊ ፓርክ ሥነ ምኅዳር መጠበቅ እንደሚገባ አንስተዋል። የፓርኩ ደኅንነት ከተጠበቀ ለቱሪዝሙ እንቅስቃሴ አስተዋፅኦ የጎላ እንደሚኾን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። የፓርኩን ደኅንነት የበለጠ ለመጠበቅ የማኅበረሰቡ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።

መንግሥት ከአምስቱ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም ውስጥ ቱሪዝምን አንዱ አድርጎ እየሠራ መኾኑን ሚኒስትር ዴኤታው አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኩመራ ዋቅጅራ በበኩላቸው የዋሊያ አይቤክስ የህልውና አደጋ ለመቀልበስ በጋራ መሥራት እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

የዋሊያ አይቤክስ ቁጥርን ለመመለስ እና ለማሣደግ በጥናት የተመሠረተ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ መዘጋጀቱን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በስትራቴጂካዊ ዕቅዱ መሠረት ማን ምን ኃላፊነት መወጣት እንዳለበት እና የሀገር ምልክት የኾነውን ዋሊያ አይቤክስን እንታደገዋለን ብለዋል።

የዋሊያ አይቤክስ ቁጥር ለምን እየቀነሰ መጣ? እና መፍትሔው ምንድን ነው? በሚል ርእስ ጥናታዊ ጽሑፍ እየቀረበ ይገኛል። በቀረበው ጽሑፍ መሠረት ከውይይቱ ተሣታፊዎች የመፍትሔ ሀሳቦች ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ዘጋቢ:- አገኘሁ አበባው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here