ደብረ ብርሃን: ሚያዝያ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ እና ዘርፈ ብዙ ግልጋሎት የሚሰጠው በሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኘው የወፍ ዋሻ ደን በቅርቡ ብሔራዊ ፓርክ ለመኾን በዝግጅት ላይ መኾኑ ተገልጿል። የአንኮበር፣ የጣርማበር እና የባሶና ወራና ወረዳዎችን የሚያካልለው ይህ ደን ልዩ ልዩ ሀገር በቀል እጽዋት፣ እንስሳት እና አእዋፍ መገኛ በመኾኑ “የንጉሣውያን ደን” እየተባለ ይጠራል።
ይህን ሥፍራ ብሔራዊ ፓርክ ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ የቆዩ ሲኾን አስፈላጊ ሰነዶች ተሟልተው ለክልል ምክር ቤት እንዲጸድቅ ቀርቧል። በተጨማሪም በቀጣይ 10 ዓመታት የሚተገበር የአሥተዳደር ሰነድ ቀርቦ በደብረ ብርሃን ከተማ ውይይት እየተካሄደ ነው።
የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ ተክለየስ በለጠ በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት የተፈጥሮ ሀብቶችን ማልማት እና መንከባከብ የሕልውና ጉዳይ ነው። የወፍ ዋሻ ደንን ይበልጥ በማልማትም ምጣኔ ሀብታዊ ተጠቃሚነትን ማሳደግ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ኀላፊ ተሾመ አግማስ የወፍ ዋሻ ደን ከ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ በማኅበረሰቡ ሲጠበቅ የቆየ እና ታሪካዊ መዳረሻዎች ያሉት መኾኑን ገልጸዋል። በተጨማሪም እድሜ ጠገብ የኾኑ እና ለዘር ምንጭነት የሚያገለግሉ የደን ምንጮች መገኛም እንደኾነ ጠቁመዋል።
ይሁን እንጂ የአካባቢውን ሕዝብ ከመጥቀም እና የቱሪዝም አቅም ከመኾን አንጻር የሚጠበቀውን ያህል ውጤት ማምጣት እንዳልተቻለ አቶ ተሾመ አመልክተዋል። ይህንን አካባቢ በዘላቂነት ለማልማት እና ተፈላጊው ውጤት እንዲመጣ ወደ ብሔራዊ ፓርክ ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መኾናቸውንም አብራርተዋል።
የውይይት መድረኩ በዊፎረስት ኢትዮጵያ እና በአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ትብብር የተዘጋጀ ሲኾን የማኅበረሰብ ተወካዮች፣ የአሥተዳደር አካላት እንዲሁም የፌደራል፣ የክልል እና የዞን የሥራ ኀላፊዎች እየተሳተፉበት ይገኛሉ።
ሚያዝያ 4/2017 ዓ.ም ደግሞ የመንዝ ጓሳን የማኅበረሰብ ጥብቅ ሥፍራ የአሥተዳደር ዕቅድ አስመልክቶ ውይይት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!