ባሕር ዳር:ሚያዝያ 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የዓለም ዐይኖችን የሚስበው የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በውስጡ ብርቅዬ እንስሳትን አቅፎ ይዟል። ቀይ ቀበሮ እና ዋልያ ደግሞ ከቀዳሚዎቹ መካከል ናቸው። የአካባቢውን ድንቅ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ እና ብርቅዬ እንስሳትን ለማየት የሚጓጉ ጎብኝዎች ወደ ሥፍራው በስፋት ይሄዳሉ።
ነገር ግን የእነዚህ ጎብኝዎችን ቀልብ የሚስቡ ብርቅዬ እንስሳት ተደጋጋሚ ችግር እየገጠማቸው ነው። በተለይም ዋልያ አደጋ እንደተጋረጠበት እና ልዩ ጥበቃ እንደሚፈልግ የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ማሳወቁ ይታወሳል። ከሰሞኑም ዋልያዎች በአዳኞች መገደላቸው ተገልጿል።
የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ማሩ ቢያድግልኝ ዋልያዎች በጥይት መገደላቸውን ተናግረዋል።ዋልያዎችን የገደሉ አካላትን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የጸጥታ አካላት እየሠሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል። ዋልያዎቹ ወደ ተገደሉበት አካባቢ አጣሪ ቡድን ተልኮ እያጣራ መኾኑን ነው የተናገሩት።
ከአሁን በፊት በተደረገ ጥናት በዋልያዎች እና በሌሎች እንስሳት ላይ አደን እንዳለ መመላከቱን አንስተዋል። በዚህም ምክንያት ዋልያዎች ቁጥራቸው እየቀነሰ መኾኑን ነው የተናገሩት። በዋልያዎች ላይ ምንም ዓይነት አደን አይደረግም ለሚሉ አካላት ከሰሞኑ የተፈጸመው ድርጊት ምስክር መኾኑን ነው የገለጹት። በዋልያዎቹ ላይ የደረሰው ጉዳይ በጥናት የተመለካተውን ስጋት የበለጠ የሚያሳይ መኾኑን ነው የተናገሩት።
የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና በአጠቃላይ የአካባቢው ማኅበረሰብ ብርቅዬ እንስሳትን መጠበቅ እንደሚገባም አሳስበዋል። ዋልያ ለአካባቢው ልዩ ትርጉም ያለው መኾኑ መታወቅ አለበት ነው ያሉት። ካለፈ በኋላ ጸጸት እንዳይመጣ የቀሩትን መጠበቅ ይገባልም ብለዋል።
በዋልያዎቹ ላይ የደረሰው ጥቃት ከሕግ እና ከእሴት ያፈነገጠ መኾኑን ተናግረዋል። ዋልያ ብቻ ሳይኾን ሌሎች እንስሳትም እንዳይገደሉ በጋራ መጠበቅ ይገባል ነው ያሉት። አጥኝ ቡድኑ የሚደርስበት ግኝት እና ተጨማሪ መረጃዎች በቀጣይ እንደሚገለጹም አመላክተዋል።
የአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ኀላፊ ተስፋሁን ዓለምነህ ስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተፈጥሮ ሃብት ቅርስነት ከተመዘገቡ ቦታዎች መካከል አንዱ መኾኑን ገልጸዋል።
በዓለም አቀፍ የተፈጥሮ ቅርስ መዝገብ እንዲመዘገብ ካደረጉት መስፈርቶች መካከል ብርቅየ የዱር እንስሳትን እና እጽዋትን አቅፎ የያዘ በመኾኑ ነው ብለዋል።
ከእነዚህ ብርቅየ የዱር እንስሳት መካከል ዋልያ አንዱ እና ዋነኛው መኾኑን ነው የተናገሩት። የዋልያ ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ ከ800 ወደ 300 እየቀነሰ ይገኛል ነው ያሉት።
ለዚህ የዝርያ ቁጥር መቀነስ ዋነኛ መንስኤው ደግሞ ሕገወጥ አደን መኾኑን ነው የተናገሩት።
የተፈጥሮ ሃብት የትውልድ ሃብት ነው ያሉት ኀላፊው ይህን ድርጊት የሚፈጽሙ አካላትን በዝምታ መመልከት በታሪክም ኾነ በመጭው ትውልድ ተጠያቂ ያደርጋል ብለዋል።
ከስሜን ተራራሮች ብሔራዊ ፓርክ ዋልያ ከጠፋ አሁን ያለውን የዓለም ቅርስነት እና የቱሪዝም አቅም ይዞ ይቀጥላል ለማለት ያስቸግራል ነው ያሉት።
ይህ ጉዳይ የማይመለከተው የማኅበረሰብ ክፍል ስለሌለ ድርጊት ፈጻሚዎችም ከዚህ ማኅበረሰብ የተሰወሩ ስላልኾነ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ሊመክራቸው እና በማይመከሩት ላይ አስተማሪ ርምጃ እንዲወሰድባቸው መተባበር ያስፈልጋል ብለዋል።
ዋልያ በአንድ አካባቢ የሚኖር ከመኾኑ ጋር ተያይዞ ዝርያው እንዳይጠፋ፤ በቅርብ ቀን የጸደቀው የዋልያ የጥበቃ ስልት እና የጥበቃ ዝርዝር ተግባራት ዕቅድ በጊዜ የለንም መንፈስ በፍጥነት ሊተገበር ይገባዋል ነው ያሉት።
የልማት ጥበቃ ስልት እና ተግባራት ለመፈጸም የበርካታ አጋር አካላትን ተሳትፎ ስለሚጠይቅ ለአፈጻጸሙ ድርሻ ያላቸው አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን