የአራት ዐይና ጎሹ ሀገር – ሞጣ

0
150

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሞጣ ከተማ ከባሕር ዳር 120 ኪ.ሜ፣ ከደብረ ማርቆስ 202 ኪ.ሜ እና ከአዲስ አበባ ደግሞ 370 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኝ የሁለት እጁ እነሴ ወረዳ መቀመጫ ከተማ ናት፡፡

በ1747 ዓ.ም እንደተቆረቆረች የሚነገርላት ሞጣ የ270 የእድሜ ባለፀጋ ናት። ሞጣ ከተማ ከ2ዐዐዐ ዓ.ም ጀምሮ የከተማ አሥተዳደር ደረጃ አግኝታለች፡፡ በ6 ቀበሌዎች የተዋቀረችው እና 1 ሺህ 995 ሄክታር ስፋት ያላት ሞጣ ከ62 ሺህ ሕዝብ በላይ እንደሚኖርባት ከሞጣ ከተማ አሥተዳደር ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

በሞጣ ከተማ ከሚገኙ የቱሪስት መስህቦች መካከል:-

👉ሞጣ ጊዮርጊስ

ጥንታዊ እና ከከበሩ ማዕድናት የተሠሩ ቅርሶች ባለቤት የኾነው የሞጣ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ከነዘመናዊ ሙዝየሙ ተጠቃሽ ነው፡፡

👉አራት ዐይና ጎሹ

ስመ ጥር የጎጃም ባለቅኔ የሞጣው አራት ዐይና ጎሹም ታሪካቸው ከሞጣ ጋር በእጅጉ ይያያዛል፡፡ መምህሬ ጎሹ ዜማ፣ ቅኔ፣ መፅሐፍት እና አቋቋም ጠንቅቀው ያውቁ እና የበቁ መምህር በመኾናቸው “አራት ዐይና” የሚል የጠቢብ ቅፅል የተሰጣቸው አባት ነበሩ፡፡

ዐይነ ስውሩ መምሬ ጎሹ አእምሯቸው ዐይናማ ስለነበር በርካታ ሊቃውንትን አፍርተው አልፈዋል፡፡ በዚህም ሞጣን ያስጠራሉ፡፡ አሁን ድረስ ታሪካቸውን የሚዘክር አራት ዐይና ጎሹ መጻሕፍት ጉባኤ የሚባል እና ሌሎችም መታሰቢያዎች አሏቸው፡፡

👉የአዳሻ መስጊድ

ሞጣ በጥንታዊው የአዳሻ መስጊድም ትታወቃለች፡፡ መስጊዱ የተመሠረተው በ1747 ዓ.ም እንደኾነ ይነገራል፡፡ ሙስሊሞቹ አዳሻ ከሚባል ቦታ ስለመጡ አዳሻ መባሉ ነው የሚነገረው፡፡

ጌታው ሼህ ኢብራሂም በሞጣ ከፈለቁ ታላላቅ የእስልምና ምሁራን መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ከአዳሻ መስጊድ ምሥረታ ጋርም ስማቸው ይነሳል፡፡ ከተለያዩ አካባቢዎች በመሄድ እስልምናን የሚማሩም ነበሩ፡፡

በሞጣ ከተማ እስልምና እና ክርሥትና በመልካም ጉርብትና ተስማምተው እና ተደጋግፈው የመኖር ታሪክ አላቸው፡፡ በሠርግ ጊዜም የሌማቱ ድግስ በየራሳቸው ኾኖ ደስታ እና ጭፈራውን በጋራ እንደሚያደርጉ ይነገራል፡፡

👉ሠባቱ ዋርካ

ከሞጣ የጥንታዊነት ምልክቶች መካከል ሰባቱ ዋርካዎችም ይጠቀሳሉ፡፡ ዋርካዎቹ ከሞጣ ምሥረታ ጀምሮ እንደተተከሉ ይነገርላቸዋል፡፡ ዋርካዎቹን ተክለው ያሳደጓቸው መናኔ ገብረ ሕይወት የተባሉ አባት መኾናቸው ይነገራል፡፡

ድሮ ሞጣ የጎጃም እና ጎንደር መገበያያ ሥፍራ ስለነበረችም ዋርካዎቹ ለመገበያያነት ያገለግሉ ነበር፡፡ የማር ተራ፣ የእህል ተራ፣ የአሞሌ ጨው ተራ፣ የበርበሬ ተራ በሚል ስያሜም ነበራቸው፡፡ ዛሬም ዋርካዎቹ በቅርስነት ተጠብቀው እያገለገሉ ይገኛሉ።

የውርግርግ ፏፏቴ፣ የሰባራው ድልድይ፣ የጮቄ ተራራ እና የዓባይ ስምጥ ሸለቆ በሞጣ ዙሪያ እና በቅርብ ርቀት የሚገኙ መስህቦች ናቸው፡፡

ሞጣ ከተማን ከሌሎች አካባቢዎች የሚያገናኙ መንገዶች፡-

ከባሕር ዳር – ሞጣ – አዲስ አባባ የአስፋልት፣
ከጅቡቲ – መካነ ሠላም – መርጡ ለማርያም – ሞጣ፣
ከፈረስ ቤት – ወይን ውኃ – ሞጣ፣
ከደብረ ማርቆስ – ድጎ – ሞጣ፣
ከደብረ ታቦር – እስቴ – ሞጣ አስፋልት መንገድ (በግንባታ ላይ ያለ) ይጠቀሳሉ፡፡
ይህም በሞጣ እና አካባቢው የሚገኙ መስህቦችን ለመጎብኘት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።

👉ክላምኛ ቋንቋ

ነጋዴዎች እንደጀመሩት የሚነገርለት ክላምኛ ቋንቋ ሞጣ ስትነሳ አብሮ የሚታወስ ነው፡፡ ነጋዴዎች ምሥጢራቸው እንዳይታወቅ ለመግባባት ፈጠሩት የሚባለው ክላምኛ በሂደት የሞጣ ነዋሪዎችም መልመዳቸው ይነገራል፡፡ ለ1931 ዓ.ም የጣሊያን ወረራ ወቅትም እንዳገለገለ ይነገራል፡፡

“መንቴ አስኳፊው ዲጃል ተመሽ” ማለት “ጓዴ ሽፍታ መቷልና አምልጥ” ማለት እንደኾነ ከከተማ አሥተዳደሩ በተገኘ የሞጣ ታሪክ ላይ ተጠቅሷል፡፡ “ተከል መናል ህቶትህን ተመሽ” ማለትም “ሰምተንሃል አንተም ሮጠህ እራስህን አውጣ” እንደኾነ፡፡

ጥንታዊቷ እና ስመ ጥሯ ሞጣ ከተማ አያሌ ታሪኮችን አቅፋ የያዘች፣ የትናንቱን ታሪክ ከዛሬው ጋር ያስተባበረች ከተማ ናት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here