“ዋልያ ከስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ከጠፋ፣ ከዓለም ነው የሚጠፋው” የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ጋሻው ግስሙ (ዶ.ር)

0
72

ደባርቅ፡ ሚያዝያ 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ “ዋልያን ከጥፋት እንታደግ” በሚል መሪ ሃሳብ ከባለድርሻ አካላት ጋር በደባርቅ ከተማ የምክክር መድረክ አካሂዷል። የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ቱሪዝምና ሆቴል ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ኀላፊ መምህር አፈራ ገብረመድኅን ዋልያዎችንና ፓርኩን እያጋጠመ ካለው ጥፋት እንዴት መከላከል ይቻላል ? የሚል የማጠንጠኛ ሀሳብ ያለው የዳሰሳ ጥናት አቅርበዋል ። በጥናታዊ ጽሑፉ ላይ ውይይት ተደርጎበታል።

በመርሃ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ጋሻው ግስሙ (ዶ.ር) የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ከዋልያ በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ብዝኃ ሕይዎቶችን አቅፎ የያዘ፣ ከፍተኛ ጥበቃና ከለላ ሊደረግለት የሚገባ ፓርክ ነው ብለዋል። ብርቅዬው ዋልያ ጠፋ ማለት ከፓርኩ ብቻ ሳይሆን የሚጠፋው ከዓለም በመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መንከባከብን ይሻል ነው ያሉት።

ከጥቂት ቀናት በፊት የፓርኩን ሕጋዊ ወሰን ጥሶ በመግባት በዋልያዎች ላይ የደረሰው ጥፋት ሊወገዝ የሚገባው አስነዋሪ ድርጊት ነው ብለዋል። በዋልያዎችና በፓርኩ ላይ እየደረሰ ያለውን ጥፋት ለማስቆም በጋራ መወያየትና ወደሥራ መግባት በማስፈለጉ ዩኒቨርሲቲው ኅላፊነት ወስዶ የውይይት መድረክ ማዘጋጀቱን ነው የገለጹት።

የሰሜን ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪና የንግድና ገቢያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ቢምረው ካሳ ብርቅዬ የሆነው ዋልያ በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ በስፋት የሚታወቅ ከፓርኩ አልፎ ለአካባቢው ማኅበረሰብም መገለጫ ነው ብለዋል። በሰበብ አስባቡ ዋልያዎች እየተገደሉ መኾናቸውን ገልጸዋል ። ዋልያዎችን በሚያጠቁ አካላት ላይ ከሚወሰደው ሕጋዊ ርምጃ በተጨማሪ የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች ከመምከርና ከማስተማር ባለፈ የጥፋት ድርጊቱን ማውገዝ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅት በፓርኩ የሚገኙት ዋልያዎች ቁጥር 306 ተብሎ ይጠቀስ እንጅ ቁጥሩ ከዚህም ሊወርድ የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ ገልጸዋል። እስከ ቀበሌ ድረስ ባሉ መዋቅሮች ጊዜ ወስዶ ማኅበረሰቡን የማወያየትና ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ በመሥራት መሠረታዊ የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት ዋልያዎቹንና የሚገኙበትን ፓርክ ከጥፋት መታደግ ይገባል ነው ያሉት።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ጠባቂዎች ሥራውን በብቃት የመከዎን አቅም ማነስ፣ በበቂ ሁኔታ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ አለመሠራት እና ለጉዳዩ የተሰጠው ትኩረት አናሳ መኾን ፓርኩን እንደጎዳው ተናግረዋል። በመርሐ ግብሩ የተሳተፉት የሰሜን ጎንደር ዞን የሀገር ሽማግሌዎች ማኅበር ኀላፊ አየልኝ ክብረት በዋልያዎች ላይ እየደረሰ ያለው የጥፋት ተግባር በሃይማኖት፣ በታሪክና በባሕል መመዘኛዎች ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው ብለዋል። ከጥፋት ድርጊቱ በመታቀብ የታሪክ ተወቃሽ ከመሆን መዳን እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የቅድመ መከላከል ሥራ በበቂ ሁኔታ በማከናዎን ዋልያዎችንና ፓርኩን ከጥፋት መታደግ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ሊሆን እንደሚገባ ተመላክቷል። የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ጽፈት ቤት ኀላፊ ማሩ ቢያድግልኝ ዋልያ ለአካባቢው ማኅበረሰብና ለበርካታ ሀገር አቀፍ ተቋማት ስያሜና መገለጫ መሆን የቻለ ብርቅዬ እንስሳ ነው ብለዋል። የአካባቢው መገለጫ የሆነውን ዋልያ ከጥፋት ለመጠበቅም የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር እየተካሄደ የሚገኘው ተከታታይነት ያለው የውይይትና የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ አንዱ እንደሆነ አብራርተዋል። “የዋልያ አምባሳደር” በሚል ለአካባቢው ወጣቶች ሥልጠና በመስጠት የማሰማራት ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በፓርኩ በአጠቃላይ ከ86 በላይ የፓርክ ጥበቃዎች አሉ ያሉት ኀላፊው ለብዙ ዓመታት ያገለገሉትንና እድሜያቸው የገፉትን የፓርክ ጠባቂዎች ጥቅማጥቅማቸውን በማስጠበቅ ተተኪ ወጣቶችን ለመቅጠር ጥረት እየተደረገ ነውም ብለዋል። በዚህም አስር ወጣቶች በጊዜያዊነት ተቀጥረው እያሠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ለአካባቢው አርሶ አደሮች ድጎማ በማድረግና አማራጭ የሥራ እድል በመፍጠር አካባቢውን በማራቆት ፓርኩን አደጋ ላይ ከሚጥል ሥራ እንዲቆጠቡ የማድረግ ተግባር እየተከናወነ እንደሆነም ተናግረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here