‘ከአባቶቻችን የወረስነውን ባሕል እና ታሪክ ሳይበረዝ ለትውልድ የማስተላለፍ ግዴታ አለብን”

0
112

ደብረ ማርቆስ: ሚያዝያ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎጃምን ባሕል፣ ወግ፣ ትውፊት እና ታሪክ ለመዘከር ያለመ ሚያዝያን በደብረ ማርቆስ መርሐ ግብር በተለያዩ ዝግጅቶች በጥንታዊቷ ደብረ ማርቆስ ከተማ እየተከበረ ነው። መርሐ ግብሩ በከተማዋ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ሲኾን ዛሬ በዕድሳት ላይ የሚገኘው የቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስትያንን በመጎብኘት እና በዓደባባይ ባሕላዊ ትዕይንቶች እና በፓናል ውይይት እንዲሁም በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡

የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ ከአባቶቻችን የወረስነውን ባሕል እና ታሪክ ሳይበረዝ ለትውልድ የማስተላለፍ ግዴታ አለብን የሚል መልዕክትም አስተላልፈዋል፡፡ የጎጃምን ባሕላዊ እሴቶች እና ታሪክን ለማሳወቅ ትልቅ ፋይዳ ያለውን ሚያዝያን በማርቆስ ክብረ በዓል በመላ ኢትዮጵያውያን እንዲታወቅ እና የቱሪስት መስህብ ኾኖ እንዲቀጥል ይሠራል ብለዋል፡፡

ትውልዱ ከመጤ ባሕል ይልቅ የራሱን ማንነት የሚያጎሉ ባሕል እና ትውፊቱን ይዞ ሊቀጥል እንደሚገባ ያሳሰቡት የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ የውልሰው ወርቅነህ የጎጃምን ሕዝብ የአለባበስ፣ የአጊያጊያጥ፣ የአመጋገብ፣ የአነጋገር ለዛ፣ ታሪካዊ ስፍራዎችን ለማሳወቅ እና ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ ታልሞ መርሐ ግብሩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

ትውልድ እና ሀገርን ማስቀጠል የሚቻለው ታሪክን ማስጠናት እና ማሳወቅ እንዲሁም ባሕልን በወጉ መዘከር ሲቻል መኾኑንም ኀላፊዋ አመላክተዋል፡፡ የዚህ ዘመን ትውልድ ከባሕሉ እና ወጉ ያፈነገጡ መንገዶችን ሲከተል ይስተዋላል ያሉት ደግሞ አሚኮ ያነጋገራቸው የበዓሉ ተሳታፊ ወጣቶች ናቸው፡፡

ወጣቶች ወደ ቀልባቸው ተመልሰው የራሳቸውን ባሕል እና ታሪክ ጠንቅቀው ማውቅ ብሎም ለሌሎችም ማስተላለፍ ይጠበቅባቸዋል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡ የመርሐ ግብሩ ታዳሚዎች ጎጃም የበርካታ አስደናቂ ባሕሎች እና ታላላቅ ምሁራን እንዲሁም አርበኞች መፍለቂያ ቢኾንም በአግባቡ ማስተዋወቅ ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

የጎጃምን ባሕል እና ታሪክ ለትውልድ ለማስተማር ብሎም ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ ሚያዝያን በማርቆስ ዓይነት ዝግጅቶች አበረታች በመኾናቸው ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ በየዓመቱ በድምቀት የሚከበረው የቅዱስ ማርቆስ ዓመታዊ የንግስ በዓል የዚሁ መርሐ ግብር አካል ሲኾን ኅብረተሰቡ በበዓሉ ዕለት በመገኘት ታሪካዊ በኾነው የቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን እንዲታደምም ጥሪ ቀርቧል።

መርሐ ግብሩ ከሚያዝያ 27/2017 ዓ.ም እስከ ሚያዝያ 30/2017 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበርም ተመላክቷል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here