ተድባበ ማርያም!

0
126

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ አድባራት ወገዳማት ተድባበ ማርያም ገዳም ከክርስቶስ ልደት በፊት በዘመነ ብሉይ በቀዳማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በ982 ዓመተ ዓለም ተመሠረተች፡፡ በኢትዮጵያ መስዋዕት ኦሪት ከተሰዋባቸዉ አክሱም ጽዮን፣ መርጦ ለማሪያም እና ጣና ቂርቆስ ጋርም ትመደባለች፡፡ በአመሠራረትም ከአክሱም ጽዮን ቀጥላ ሁለተኛዋ ባለታሪክ ደብር ናት፡፡

ገዳሟ በአማራ ክልል፣ በደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት በአማራ ሣይንት ወረዳ አጅባር ከተማ ሰሜናዊ ምሥራቅ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይም ትገኛለች፡፡ ዙሪያዋ ገደል ሆኖ በግራና ቀኝ በጉንዳ፣ በገዳማይ እና በበሽሎ ወንዝ ታጅባለች፡፡ አምባው ፊት በር ፣ ቦካ ፣ ገተም፣ ሞገራ ግራኝ ፣ ታሪኳ ፣ የዘንጌ ፣ አሳስት፣ አጎና ፣ አምጣ ፈረሴን ፣ አህያ መደብለያ እና የጌለት የሚባሉ 12 በሮች አሏት፡፡

ሌዋዊያን ካህናት በአዛሪያስ መሪነት ከእስራኤል ተነስተው በየጁ አልፈው ከዛሬዋ አማሐራ ሳይንት ደረሱ፡፡ 12 በር ባለው ተራራ ላይ ለእግዚብሔር ቤተ መቅደስ ከሠሩ በኋላ ከፊሎቹ ደብረ ይባብ እንበላት ሲሉ፤ አዛርያስ እና የዳዊት የወንድም ልጆች ሳቤቅ የኢየሩሳሌም የዳዊት መታሰቢያ ከተማ ትኾን ዘንድ ተድባበ ጽዮን ብለው እንደሰየሟት ይነገራል፡፡

በዘመነ ሐዲስ ክርስትና ሲስፋፋ የአክሱም ነገሥታት አብረሃ እና አጽበሃ ተድባበ ጽዮንን ተድባበ ማርያም ብለው ሰየሙ፡፡ ትርጓሜውም ለእግዚአብሔር የተመረጠ ከፍተኛ ቦታ ማለት ነው፡፡ ገዳሟ በብሉይ ኪዳን ስለመመስረቷ አመላካች አንዳንድ የኦሪት ሥርዓቶች ሲከናወኑ ይስተዋላሉ፡፡ ታቦታቱ በሚነግሡበት ወቅት በምሥራቅ ያሉ አማኞች ነዋያተ ቅዱሣቱን ይዘው በምዕራብ ካህናት ተሰልፈው በሰሜን ያሉ ምዕመናን መጋረጃን ይዘው በደቡብ ያሉ ምዕመናን ጎራዴውን እና ካስማውን ይዘው መንቀሳቀሳቸው በኦሪት ዘሁልቁ ምዕራፍ 2 ከቁጥር 3 እስከ 4 ያለውን የኦሪት ሥርዓት ያመለክታል፡፡

ተድባበ ማርያም እነዚህን የሐዲስ ኪዳን ሥርዓቶች በመፈፀም ቀዳሚ ናት፡፡ ቀዳማዊ ምኒሊክ ከአባቱ ከንጉሡ ሰሎሞን መንግሥት ተቀብሎ ከኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ አራት መናብርተ ጽዮንን ይዞ መጣ፡፡ እነርሱም የአክሱም ጽዮን ንቡረ ዕድ፣ የተድባበ ማርያም ፓትርያርክ ፣ የመርጡለ ማርያም ርዕሰ ርዑሳን እና የጣና ቂርቆስ ሊቀ ካህናት ናቸው፡፡

ከእነዚህ ጋር ቀዳማዊ ምኒልክን ተከትለው ወደ ኢትዮጵያ የመጡ በሺህዎች የሚቆጠሩ መሣፍንት፣ መኳንንት፣ ወይዛዝርት እና የተግባረ ዕድ ሥልጡኖች በየክፍለ ሀገሩ ሥራቸውን ጀምረዋል፡፡ ጽዮን አክሱም ላይ ስትደበር የዳዊት የወንድም ልጅ ሳቤቅ የሰሎሞን አጎት ከአዛሪያስ ጋር ተከዜን ተሻግሮ አምሐራ ሳይንት ደረሰ፡፡ የአሁኗ ተድባበ ማርያም ካለችበት አምባ ላይ ሲደርስ ቤተ እግዚአብሔር ሠራ፡፡

ተድባበ ማርያም ከአክሱም ቀጥላ ሁለተኛዋ መናብርተ ጽዮን ናት፡፡ በሥርዓቱም መሠረት የአክሱም ጽዮን አሥተዳዳሪ ንቡር ዕድ የተድባበ ማርያም አሥተዳዳሪ ፓትርያርክ የመርጡለ ማርያም አሥተዳዳሪ ርዕስ ርዑሳን የጣና ቂርቆስ አሥተዳዳሪ ሊቀ ካህናት በመባል ይጠራሉ፡፡ ከቀዳማዊ ምኒልክ ጀምሮ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን መንግሥት ድረስ በየዘመኑ ለነገሡት ነገሥታት ቅብዐ መንግሥቱን በመቀባት ሁሉም የየራሳቸው ድርሻ ነበራቸው፡፡ዓመታዊ ክብረ በዓሏ ግንቦት አንድ ቀን ነው።

በዘመነ ክርስትና አብረሃ እና አጽብሃ ተድባበ ማርያምን አንጽው ካጠናቀቁ በኋላ በዓሏን ጥር 21 ቀን ለማክበር ደንግገው ነበር፡፡ ይህም እስከ አጼ ገላውዴዎስ ቆይቶ ነበር። ንጉሥ ገላውዴዎስ ግን የቅድስት ድንግል ማርያም ልደቷ ግንቦት አንድ በመኾኑ እና የልደታን ጽላት አስገብተው ስለነበር የተድባበ ማርያምን በዓል ግንቦት አንድ ቀን እንዲኾን አደረጉ፡፡

በተድባበ ማርያም ከ300 በላይ የብራና መጽሐፍት፣ ገድሎች፣ ስዕሎች፣ የነገሥታት ዘውዶች፣ ወንበር እና አልባሳት፣ የአጼ ገላውዲዎስን ጨምሮ የነገሥታት አጽም፣ የጥንት ነገሥታት የጦር መሳሪያዎች ይገኛሉ፡፡ የበግ ምስል እና የተቆለመለመ የበግ ቀንድ ያለበት መስቀልም ይገኛል፡፡ መስቀሉ የሚያንፀባርቅ ሲኾን ከምን አይነት ማዕድን እንደተሰራ አይታወቅም፡፡

አጼ ካሌብ ከደቡብ አረቢያ ዘመቻ ሲመለሱ በስለት የሰጡት ጋሻ በቦታው እንደሚገኝ መዛግብት ይናገራሉ፡፡ ከአንድ ሺህ ያላነሱ በአክሱም ዘመነ መንግሥት የተጻፉ የብራና ጥንታዊ መጽሐፍት ይገኛሉ፡፡ በአረበኛ እና በግዕዝ የተጻፉ መጻሕፍት፣ ወንጌል ዘወርቅ እየተባለ የሚጠራ ትልቅ የወርቅ ጉብጉብታ ያለበት የወንጌል መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሉቃስ እንዳሳላት የሚነገርላት የቅድስት ድንግል ማርያም ስዕለ አድኖ፣ ባለ ሦስት ተከፋች የገበታ ስዕል እና ጥንታዊ ሥነ ጥበባዊ ቅርሶች ይገኛሉ፡፡

በተድባበ ማርያም በርካታ ጥንታዊ የእጅ እና የመጾር መስቀል እና ሌሎች በርካታ ቅርሶች እንደሚገኙም መረጃዎች ይናገራሉ፡፡ የገዳሟን ታሪክ ጠብቆ ለትውልድ ለማቆየት እና ትውልዱ ታሪክ፣ ባሕል እና ሃይማኖቱን እንዲያውቅ ለማድረግ 25 ኪሎ ሜትር መንገድ እየተገነባ ነው። ሙዚየሙም እየተገነባ እንደሚገኝ በደቡብ ወሎ ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ባለሙያ ካሣ መሐመድ ነግረውናል፡፡

የመብራት እና የውኃ አቅርቦት ገና መኾኑን እና ቱሪስቶች በበዙ ጊዜ እጥረት እንዳያጋጥም እየተሠራ መኾኑን ነው ባለሙያው የገለጹልን፡፡ በተጨማሪ የመረጃ ምንጭነት የደቡብ ወሎ ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ እና ሐመር መፅሄት ሚያዝያ 2002 ዓ.ም ዕትም ተጠቅመናል።

በዋሴ ባየ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here