ባሕር ዳር: ግንቦት 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሁለተኛው ዙር የወይዘሪት አማራ የቁንጅና ውድድር ከግንቦት አጋማሽ ጀምሮ በደሴ ከተማ እንደሚካሄድ የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል። የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ አባይ መንግሥቴ ለፕሮግራሙ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ መኾኑን ተናግረዋል።
የወይዘሪት ቱሪዝም አማራ ቆንጆን መምረጥ እና የአማራን ሕዝብ ባሕል እና ወግ ማስተዋወቅ ዋና ዋና የፕሮግራሙ አላማዎች እንደኾኑም ተናግረዋል። የምትመረጠው ወይዘሪት አማራ በተገቢው መንገድ ባሕል እና ወግን ማስተዋወቅ ላይ መሥራት የምትችል፣ የአማራ ክልልን የቱሪዝም ጸጋዎች ለሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች እና ለዓለም ማስተዋወቅ የምትችል እና ሌሎችንም መስፈርቶች የምታሟላ መኾን ይኖርባታል ብለዋል፡፡
እስከ ቀጣይ የወይዘሪት ቱሪዝም ውድድር ምርጫ ድረስ ከክልሉ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ጋር ውል በመውሰድ በሀገር ውስጥም ኾነ በውጭ ሀገራት በሚደረጉ መድረኮች የክልሉን የቱሪዝም ጸጋዎች የማስተዋወቅ ኀላፊነትም አለባት ነው ያሉት፡፡ በፕሮግራሙ በቱሪዝም፣ በባሕል እና በቅርስ ዙሪያ ከፍተኛ የኾነ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦች፣ ተቋማት እና ድርጅቶችም የእውቅና እና የሽልማት ስጦታ ይደረጋል ብለዋል ምክትል ኀላፊው፡፡
ይህ እዲኾን ያስፈለገበት ምክንያት አገልግሎት ሰጭ ተቋሞች ምርት እና አገልግሎታቸው ጥራት እንዲኖረው፣ ባሕል እና ቅርሶች በተገቢዉ መንገድ እንዲጠበቁ፣ ባሕልን እንዲንከባከቡ እና ለቱሪዝሙ አቅም መገንቢያ እንዲኾኑ ለሚደረገው ጥረት ከፍተኛ አቅም ስለሚኾን ነው ብለዋል።
የወይዘሪት አማራ የቁንጅና ውድድሩ ከግንቦት አጋማሽ ጀምሮ ይካሄዳል ነው የተባለው፡፡
ዘጋቢ: ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን