የሊቃውንት መፍለቂያ!

0
90

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤልያስ ወረዳ የሚገኘው ደብረ ገነት ነብዩ ኤልያስ ቤተ ክርስቲያን በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአጼ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት በ1466 ዓ.ም እንደተመሠረተ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። የአኹኑ ቤተ ክርስቲያን ሕንጻ የተሠራው በ1964 ዓ.ም በሁለተኛው የኢትዮጵያ ጳጳስ አቡነ ቴዎፍሎስ ፓትርያሪክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ መኾኑን አንዳንድ ታሪክ አዋቂዎች እና የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡

ደብረ ገነት ነብዩ ኤልያስ ቤተ ክርስቲያን ዕድሜ ጠገብ ከመኾኑ ጋር ተያይዞ የመፍረስ አደጋ እንዳይደርስበት በቅርቡ ታሪካዊ ይዘቱን ሳይለቅ እጅግ በአማረ እና በተዋበ መንገድ የጣራ እና ሌሎች የእድሳት ሥራዎች ተደርገውለታል። የቤተ ክርስትያኑ አጥር ግቢ ለቤተ ክርስትያኑ ተጨማሪ ግርማ ሞገስን አጎናፅፎታል።

በደብረ ገነት ኤልያስ ቤተክርስቲያን ለደብሩ አሥተዳዳሪዎች የሚሰጥ የማዕረግ ስያሜ “ድምሐነ-ገነት”የሚል ሲኾን ትርጓሜውም “የገነት መሐል ወይንም ራስ” ማለት ነው፡፡ ይህ ስያሜ የራሱ የኾነ ትርጓሜ ሲኖረው በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት እንደማይሰጥ አባቶች ይገልጻሉ፡፡ በዚህ ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ ቀደም ሲል ሰዎች እንደነበሩ በአፈ ታሪክ የሚታመኑ ሁለት ድንጋዮች አሉ፡፡

ድንጋዮቹ በመጠን እና በቅርጽ እጅግ የተለያዩ ናቸው፡፡ ኅብረተሰቡ በተለይም በተለምዶ ሴት እየተባለች የምትጠራውን ድንጋይ ለማንሳት የተለያዩ ሙከራዎችን ያደርጋል፡፡ ድንጋዋን በማንሳትም ኅብረተሰቡ የተለያዩ አንድምታዎችን (ትርጓሜዎችን) ሲሰጥ ይስተዋላል፡፡ የደብረ ገነት ነብዩ ኤልያስ ቤተክርስትያን ከጥንት እስከ ዛሬ የዜማ፣ የቅኔ፣ የአቋቋም፣ የመጽሐፍ እና የቅዳሴ መምህራንን በማፍራት ለሀገሪቱ እጅግ ባለውለታ ነው፡፡

ከደብረ ገነት ነብዩ ኤልያስ የዕውቀት መነሻቸውን አድርገው ለዓለም እና ለኢትዮጵያ ባለውለታ የኾኑ እንቁ ሰዎችን አፍርቶ ያበረከተ እና አኹንም በማበርከት ላይ የሚገኝም ነው።

ከእነዚህም ውስጥ፡-

👉ታላቁ ደራሲ እና የቤተ ክህነት ሊቅ ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሤ

👉 አቡነ ቴዎፍሎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

👉 ታላቁ እና እውቁ የረጅም ልብ ወለድ ድርሰት አባት ክቡር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ ይጠቀሳሉ።

በርካታ ሊቃውንትን ያፈራው ቤተ ክርስቲያኑ በአኹኑ ወቅትም በአምስቱ ጉባኤያት በርካታ የአብነት ተማሪዎችን በማስተማር ላይ እንደሚገኝ ከምሥራቅ ጎጃም ዞንባሕል እና ቱሪዝም የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በደመወዝ የቆየ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here