ቅርሶችን ለመታደግ ተስፋ የተጣለበት የኖራ ማቃጠያ ፋብሪካ!

0
62

ባሕር ዳር: ግንቦት 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ቅርሶች የሰው ልጅ የማንነት መገለጫ፣ የቀደምት ማኅበረሰብ የባሕል እና የትውፊት ማሳያ፣ የጥበብ እና ሥልጣኔ አሻራ፣ ለአኹኑ ትውልድ ደግሞ የኩራት ምንጭ የወል ሀብቶች ናቸው። ቅርሶች የማንነት መገለጫ በመኾን ሀገርን ወይም አካባቢን ከማስጠራታቸው በተጨማሪ በቱሪስት መዳረሻነትም የኢኮኖሚ ምንጭ በመኾን አማራጭ የገቢ ምንጭ ናቸው።

በአማራ ክልልም በርካታ ቋሚ የኾኑ ጥንታዊ ቅርሶች ይገኛሉ። አብዛኞቹ በቀደምት ትውልዶች ተገንብተው፤ ረጅም ዘመናትን ተሻግረው በትውልድ ቅብብሎሽ ዛሬ ላይ ደርሰዋል። እነዚህ ጥንታዊ ቅርሶች እንደዛሬው ቴክኖሎጅ ሳይስፋፋ ባሕላዊ ጥበብን እና ሀገር በቀል ዕውቀትን ተጠቅመው በሀገር በቀል የግንባታ ግብዓቶች የተገነቡ ናቸው።

በጊዜ ሂደትም በሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ምክንያቶች ጉዳቶችን ሲያስተናግዱ ይስተዋላል። ቅርሶችን የቀደመ ይዘታቸውን እንደጠበቁ ለመጠገን ከሚያስፈልጉ ግብዓቶች መካከል ደግሞ ኖራ አንዱ እንደኾነ በቅርስ ባለሙያዎች ይገለፃል። በአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የቅርስ ጥበቃ እና እንክብካቤ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ጋሻዬ መለሰ በክልሉ የሚገኙት በተለይም ከ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ የተገነቡት አብዛኞቹ ጥንታዊ ቅርሶች ኖራን በግብዓትነት በመጠቀም የተገነቡ መኾናቸውን ገልጸዋል።

የኖራ ግብዓቱንም በቅርብ ማግኘት ባለመቻሉ ጉዳት ሲያጋጥማቸው ለመጠገን እንቅፋት ኾኖ መቆየቱን ተናግረዋል። በአኹኑ ወቅትም የኖራ ግብዓቱን እጥረት ለመቅረፍ የሚያስችል የኖራ ማቃጠያ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምዕራብ በለሳ ወረዳ ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩን አቶ ጋሻዬ መለሰ ገልጸዋል።

ከክልሉ መንግሥት በተመደበ 17 ሚሊዮን ብር ወጭ ፋብሪካውን በማስገንባት የኖራ አቅርቦት ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት እየተሠራ መኾኑን ነው አቶ ጋሻዬ የተናገሩት። የኖራ ማቃጠያው ጨረታ ወጥቶ ለተቋራጭ መሰጠቱን እና ቦታው ከሦስተኛ ወገን ነጻ ኾኖ የግንባታ ሂደቱም የተጀመረ መኾኑን ገልጸዋል።

ግንባታው ተጠናቅቆ ወደ ሥራ ሲገባ በክልሉ የሚገኙ ቅርሶችን በሙሉ አቅም ለመጠገን እንደሚያስችል እና የቅርሶችን ጉዳት ለመታደግ ተስፋ የተጣለበት መኾኑን ጠቁመዋል። ማቃጠያው ሚናው ከፍ ያለ መኾኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ የክልሉ መንግሥት ከአኹን በፊት ለቅርስ ጥገና የሚያወጣው ወጭ በአብዛኛው ለኖራ አቅርቦት ግዥ የሚውል በመኾኑ በቀጣይ ይህንን ወጭ እንደሚያስቀርም አመላክተዋል።

ግንባታውን በቶሎ ለማጠናቀቅ እና ወደ ሥራ ለማስገባት የአካባቢው ማኅበረሰብ፣ የአካባቢውን አሥተዳደር እና ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና መወጣት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት። የቅርስ ጥበቃ እና እንክብካቤ ከፍተኛ ባለሙያ ሙላት ጥላሁን ጥንታዊ ቅርሶች ማኅበረሰቡ በደረሰበት የሥልጣኔ ደረጃ በባሕላዊ መንገድ ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን በመጠቀም የተገነቡ መኾናቸውን ገልጸዋል።

አብዛኞቹ ቅርሶች ሲገነቡም ኖራ እንደ ማጣበቂያ ጥቅም ላይ የዋለ ስለነበር አኹንም የቀደመ ይዘታቸውን በጠበቀ መልኩ ለመጠገን የኖራ ዱቄትን መጠቀም የግድ መኾኑን አንስተዋል። ከአኹን በፊት የኖራው አቅርቦት በክልሉ ባለመኖሩ በወቅቱ ለመጠገን እንቅፋት ኾኖ መቆየቱን አስታውሰዋል። በቀጣይ የሚገነባው የኖራ ማቃጠያ ወደ ሥራ ሲገባ ቅርሶችን በወቅቱ ለመጠገን ምቹ ኹኔታን ይፈጥራል ብለዋል።

የኖራ ማቃጠያው ለቅርስ ጥገና የሚኾን ልም የኾነ ኖራ ማምረት የሚችል ነው ብለዋል። ከኖራ ዱቄት በተጨማሪም ለቅርስ ጥገና የሚውሉ ጌጠኛ ድንጋዬችን በተለያዩ ዲዛይኖች በማምረት ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥርም የቅርስ ባለሙያው አንስተዋል።

ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here