“የጎንደር ጥንታዊ ምሽግ እና የዘመናት ምስክር”

0
95

ባሕር ዳር: ግንቦት 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ ውበት እና ታሪክ መገለጫ ከኾኑት ስፍራዎች አንዱ የኾነው ራስ ግንብ ከአጼ ፋሲል አብያተ መንግሥታት በስተሰሜን ምዕራብ 280 ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። ይህ በድንጋይ እና በኖራ የተገነባው ግርማ ሞገስ ያለው ሕንጻ በ1636 ዓ.ም

ለአጼ ፋሲል የጦር አበጋዝ እና አምቻቸው ለነበሩት ራስ ቢትወደድ ወልደጊዮርጊስ ክብር እንደተሠራ የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ። የራስ ግንብ የተሠራው ለራስ ቢትወደድ ወልደጊዮርጊስ ቢኾንም በወቅቱ የጦር አበጋዞች በየሀገሩ ስለሚዘዋወሩ እሳቸው ሳይቀመጡበት በ1664 ዓ.ም አርፈዋል።

✍️ የራስ ግንብ የነገስታት መኖሪያ ግልጋሎት! ከራስ ቢትወደድ ወልደጊዮርጊስ በኋላ የጎንደር ሹማምንቶች እና ራሶች ግንቡ ውስጥ ይኖሩበት እንደነበርም ታሪኩ ያስረዳል።

✍️ የግንቡ የተለያዩ ዘመናት ግልጋሎት! በጣሊያን ወረራ ጊዜ ለጄኔራሎች መኖሪያነት፣ በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን ደግሞ ለሰሜኑ ጠቅላይ ግዛት ቤተመንግሥት ኾኖ አገልግሏል።

✍️ የራስ ግንብ የዛሬ አገልግሎት! ይህ በርካታ ታሪኮችን ያስተናገደው እና 381 ዓመታት ዕድሜ ያለው ጥንታዊ ሕንጻ፣ አሁን የጎንደር ከተማን ታሪክ እና ባሕል የሚያሳይ ድንቅ ሙዚየም ኾኖ እያገለገለ ይገኛል። ግንቡ አሁን ላይም ተጠግኖ በውስጡ በርካታ ቅርሶችን ይዟል።

✍️ በራስ ግንብ ሙዚየም ውስጥ ምን ያገኛል? ራስ ግንብ አራት ፎቆች ያሉት ሲኾን እያንዳንዱ ፎቅ የራሱ የኾነ ታሪክ እና አገልግሎት አለው።

የመመገቢያ፣ የማንበቢያ እና የጸሎት ክፍሎች፣ የጥንት ነገስታት እና ሹማምንቶች አኗኗር የሚያሳዩ ቅርሶችም ይገኛሉ። ይህ ድንቅ የቱሪስት መስህብ የጎንደር ሹማምንት፣ የአጼ ኃይለሥላሴ እና የእቴጌ መነን መኝታ ክፍሎችን ጨምሮ የቤተመንግሥት ሕይዎትን የሚያሳይ ሁነትንም በውስጡ አቅፎ የያዘ ነው።

✍️ የራስ ግንብ የዓለም ቅርስ አካል ኾኖ መቸ ተመወገበ? የአጼ ፋሲል ግንብ በ1971 ዓ.ም በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ኾኖ ሲመዘገብ ራስ ግንብም እንደ ዋና አካል ተካቶ በቅርስነት መመዝገቡን ከጎንደር ከተማ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here