ባሕር ዳር: ግንቦት 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ክልል በርካታ ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ የኾኑ የቱሪዝም ሀብቶች ባለቤት ነው። በክልሉ አያሌ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶች እና ባሕላዊ እሴቶችም ይገኛሉ።
ይህንን እምቅ የቱሪዝም ሀብት፣ ባሕል እና ትውፊት በተሻለ መልኩ ለማስተዋወቅ ዓላማ ባደረገው የድንቅ ምድር እውቅና እና ሽልማት በ2015 ዓ.ም ዝግጅት ላይ የቁንጅና ውድድር ተካሂዶ “ወይዘሪት ቱሪዝም አማራ” መመረጧ ይታወሳል። በወቅቱም ወይዘሪት ቤዛ ሣኅሉ የውድድሩ አሸናፊ ኾና የክልሉ የቱሪዝም አምባሳደር በመኾን ተመርጣለች።
ከተመረጠችበት ጊዜ ጀምሮ የክልሉን ሕዝብ ባሕል፣ እሴት፣ ወግ፣ ተፈጥሯዊ፣ ሰው ሠራሽ ቅርሶችን እና የቱሪስት መዳረሻዎች በተሻለ መንገድ ለማስተዋወቅ ኀላፊነት እንደተሰጣት ወይዘሪት ቤዛ ገልጻለች። ወይዘሪት ቤዛ ሣኅሉ ከተመረጠችበት ጊዜ ጀምሮ የክልሉን የቱሪስት መስህብ ሀብቶች፣ የሕዝቡን ባሕል፣ ወግ እና ትውፊት ለማስተዋወቅ ጥረት ማድረጓን ተናግራለች። የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀምም የክልሉን የቱሪስት መዳረሻዎችን እና የቱሪዝም ምርቶችን ስታስተዋውቅ መቆየቷን ጠቁማለች።
የክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ በፈጠረላት እድል እና ባደረገላት ድጋፍም በታላላቅ ሀገራዊ እና ክልላዊ ሁነቶች ላይ በመሳተፍ የክልሉን ባሕል ለማሳየት ጥረት ማድረጓን ነው የገለጸችው። በብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን እና በሀገር አቀፍ የቱሪዝም ቀን ላይ በመገኘት የክልሉን ባሕል ማስተዋወቋን አንስታለች።
በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ግን በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በመዘዋወር በሚፈለገው ልክ የክልሉን ባሕል እና እሴት ማስተዋወቅ አለመቻሏን ጠቅሳለች። የአምባሳደርነት ዘመኗ እስከሚጠናቀቅ ድረስም ከቢሮው ጋር ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነች መኾኗንም ነው የገለጸችው።
በአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር መልካሙ አዳም የወይዘሪት ቱሪዝም አምባሳደር ስትመረጥ ክልሉ ያለውን ታላላቅ የመዳረሻ ሀብቶችን ወኪል ኾና እንድታስተዋውቅ እና የክልሉን ገጽታ የመገንባት ሥራ እንድታከናውን ኀላፊነት እንደተሰጣት ተናግረዋል። ይህ ኃላፊነት ሲሰጣት ቢሮው በጀት መድቦ ከሌሎች የቁንጅና ተወዳዳሪዎች ጋር በባለሙያ የተደገፈ ሁሉን አቀፍ ሥልጠና እንደሰጣትም ተናግረዋል።
በክልሉ ባጋጠመዉ የጸጥታ መደፍረስ ምክንያት ቢሮው ከአምባሳደሯ ጋር በቅርበት እና በታሰበው ልክ ለመሥራት ውስንነት የነበረ መኾኑን አንስተዋል። ይሁን እንጂ በተቻለ መጠን መልካም አጋጣሚዎችን እና አማራጮችን በመጠቀም የተሰጣትን ኀላፊነት ለመወጣት ጥረት ስታደርግ መቆየቷን አብራርተዋል።
በአዲስ አበባ በተካሄደው የኢጋድ አባል ሀገራት የቱሪዝም ኢግዚቢሽንን ጨምሮ በክልላዊ እና ሀገር አቀፍ የቱሪዝም መድረኮች ላይ አምባሳደሯን በማሳተፍ የክልሉን የገጽታ ግንባታ ሥራ እንድታከናውን ማድረጉንም ተናግረዋል። በተጨማሪም በግሏ ማኅበራዊ ገፆችን በመጠቀም ሥራዋን ለማከናወን ጥረት ስታደርግ መቆየቷንም ተናግረዋል።
የክልሉን የመስህብ ሀብቶች በዚህ መንገድ ማስተዋወቅ አዲስ የተጀመረ ስትራቴጅ መኾኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ ለቀጣይ ጥሩ መነሻ ኾኖናል ነው ያሉት። በቀጣይም ክልል አቀፍ የቁንጅና ውድድር በማካሄድ ወይዘሪት ቱሪዝም አማራ እንደምትመረጥ ተናግረዋል። አሁን የተገኙትን ልምዶች በማጠናከር እና የነበሩትን እጥረቶች በመቅረፍ አዲስ የምትመረጠውን የቱሪዝም አምባሳደር በመጠቀም የተሻለ የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚሠራም አመላክተዋል።
የወይዘሪት ቱሪዝም አምባሳደር ቤዛ ሣኅሉ በቀጣይ የቁንጅና ውድድር ተካሂዶ ሌላ አምባሳደር ሲመረጥ የሥራ ዘመኗ እንደሚያበቃ ተገልጿል።
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን