ባሕር ዳር፡ ግንቦት 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አበጋር በወሎ አካባቢ በስፋት አገልግሎት ላይ የሚውል ባሕላዊ የዳኝነት እና የእርቅ ሥነ ሥርዓት ነው፡፡ በሀገራችን ሰዎች በሚያደርጓቸው ማኅበራዊ መስተጋብሮች ውስጥ ግጭት የማይቀር አንድ ክስተት ሲኾን ይህንን የሚፈቱ በርካታ የግጭት አፈታት ሥርዓቶች አሉ፡፡
እውቁ የሥነ-ማኅበረሰብ ሊቅ ጆርጅ ሲመል ”ግጭት ምንም እንኳን ከሁለት የተጋጩ ወገኖች ውስጥ በአንደኛው ላይ ጠባሳን ጥሎ ቢያልፍም ሁለት የማይጣጣሙ ፍላጎቶችን በማስታረቅ ወደ አንዳች ዓይነት መቀራረብ መድረስ የሚያስችል መንገድ ነው” ይላል፡፡ ባሕላዊ የእርቅ ሥነ ሥርዓቶች ግጭቶች በማኅበረሰቡ ሕይዎት፣ አካል እና ንብረት ላይ አደጋ ከማድረሱ እና የበለጠ ውድመት ከማስከተሉ በፊት ለመቆጣጠር የሚረዱ ናቸው፡፡ ለዛሬም የአበጋር ባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓትን እንቃኛለን፡፡
አበጋር የሽምግልና ሥነ ሥርዓት በአብዛኛው የወሎ አካባቢ ማኅበረሰቡ የሚጠቀምበት የዳኝነት እና የእርቅ ሥነ-ሥርዓት ነው፡፡ አበጋር የሚለው ቃልም አስታራቂ የሚል ፍቺ እንዳለው ይነገርለታል፡፡ አበጋር የተጣላን የሚያስታርቅ፣ ክፉ እንዳይሠራ በሀገር ሽማግሌዎች ፊት ተው የሚባልበት እና መጥፎ ነገሩን ዱአ ወይም ጸሎት አድርገው ወደ ፈጣሪ በመለመን በተጣሉት ሰዎች መካከል ጥላቻን የሚያርቁበት ሥርዓት መኾኑን ነው ከአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የተገኘው መረጃ የሚያመላክተው፡፡
በደቡብ ወሎ ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ የባሕል እሴቶች እና ኢንዱስትሪ ልማት ቡድን መሪ የኾኑት ኃይሉ ታደሰ አበጋር በወሎ አካባቢ የሚተገበር የሽምግልና ሥርዓት ሲኾን ከሌሎች ለየት የሚያደርገው በዘር የሚወረስ መኾኑ ነው ይላሉ፡፡ አንድ አበጋር የኾኑ አባት ማዕረጋቸውን ከልጆቻቸው ውስጥ በአስተሳሰብ መልካም ለኾነው፣ የተሻለ አቅም እና ቀና አመለካከት ላለው ልጃቸው መርቀው እንደሚያስተላልፉ ነው የገለጹልን፡፡
አበጋር ላይ የሚስተናገዱ የግጭት ዓይነቶች ከትንሽ እስከ ትልቅ ማለትም ዛቻ፣ የንብረት ውድመት፣ ድብደባ፣ የግድያ ወንጀሎች እና ሌሎችም ናቸው ብለዋል፡፡ ሁሉም የግጭት ዓይነቶች ወደ አበጋር ከቀረቡ ይፈታሉ ነው ያሉት፡፡ ይሁን እንጂ ግጭቶች እንዲፈቱ ወደ አበጋር የሚሄዱት በጎረቤት እና በዘመድ ካልተፈታ እና ግጭቱ ጠንክሯል ተብሎ ሲታሰብ እንደኾነም አቶ ኃይሉ ይገልጻሉ፡፡
በአበጋር ሥርዓት በዳዩ በድያለሁ አስታርቁኝ ብሎ ሲጠይቅ እና የአካባቢው ማኅበረሰብ ችግሩን ተረድቶ ወደ ከፋ ደረጃ ከመድረሱ በፊት ወደ አበጋር ሄደው ይታረቁ ብሎ በእድር መሪዎች እና በታዋቂ ሽማግሌዎች አማካኝነት ሲጠይቅ መኾኑንም ጠቅሰውልናል፡፡ እርቅ እንዲከናወን ጥያቄው ከቀረበ በኋላ አበጋሮች ችግሩ ከተፈጠረበት ቦታ ሄደው ድንኳን ይጥላሉ፤ ማኅበረሰቡ እንዲገባ ድቢ ወይም ከበሮ ይመታሉ ነው ያሉት፡፡ ከዚያም የአካባቢው ማኅበረሰብ አበጋር መጣ በማለት የሚበላ እና የሚጠጣ ይዘው ይቀርባሉ፤ እየበሉ እና እየጠጡ ዱኣ ወይም ጸሎት ያደርጋሉ ነው ያሉት፡፡
በመቀጠልም ችግሩን በመረዳት ያንን ሊፈቱ የሚችሉ ሽማግሌዎች ከበዳይም ከተበዳይም ይመረጣሉ፡፡ ሁለት አበጋሮች ከማኅበረሰቡ ሽማግሌ ሊኾኑ የሚችሉ ከሁለቱም ወገን ዘመድ፣ የሀገር ሽማግሌ እና የሃይማኖት አባቶች ተመርጠው በቀጠሮ ወደ እርግማን ከመገባቱ በፊት እውነቱን እንዲያወጡ ይጠየቃሉ ነው ያሉን፡፡
ከዚያም የበደለ ሰው አምኖ ይገባል፤ በዚህ ጊዜ ከፍተኛ የኾነ የምረቃ ሥርዓት ይከወናል ነው ያሉት። ምረቃው ወንዝ ያሻግራል፤ አምኖ ካልገባ ግን በአንጻሩ እርግማን ይኾናል ብለዋል አቶ ኃይሉ፡፡ ይህም “አርከባስ” ይባላል፡፡ በዳዩ ያደረገውን ነገር ከዋሸ የሚደርስበት እርግማን ሲኾን ይህ እርግማን የደረሰበት ሰው እስከ ሰባት ትውልድ ይጎዳል፤ ዘር አይወጣለትም፤ አዝመራው አይዝለትም፤ ከብት አይረባለትም ተብሎ ስለሚታሰብ አይደብቅም ነው ያሉት።
አበጋር በማኅበራዊ ዘርፍ በቀል እና ቂምን ከስሩ በመንቀል በኩል ሚናው ከፍተኛ ነው፡፡ ለአብነት አንድ ወንጀለኛ ጥፋት አጥፍቶ በፍርድ ቤት ቅጣቱን ጨርሶ ከወጣ በኋላ የተበደለው ሰው በተመሳሳይ ደም ሲመልስ ይስተዋላል፡፡ ነገር ግን በአበጋር የታረቀ ሰው ቂም በቀል እንደሌለው እና በፍቅር አብረው እንደሚኖሩ አንስተውልናል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ‘’እምባ የሚደርቀው በፍርድ ብቻ ሳይኾን በፍቅርም ነው’’ የሚል ፍቅርን እና መዋደድን የሚያበረታታ ባሕል ይዘው አንዳንድ በጣም ከባድ የኾኑ ግጭቶችን ለማስቆም ሲባል ሁለቱ ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች በጋብቻ እንዲተሳሰሩ፣ እንዲወልዱ እና እንዲዛመዱ በማድረግ ደም እንዲደርቅ የማድረግ ሥራ እንደሚሠራም ነው የገለጹልን፡፡
የእርቅ ሥነ-ሥርዓቱ ከሦስት እስከ አራት ቀናት ውስጥ የሚጠናቀቅ በመኾኑ የሚባክን ጊዜ እና ጉልበት የለም፡፡ በፍርድ ቤት ብዙ ጊዜ፣ ጉልበት እና ገንዘብ የሚወስደው ችግር በአጭር ይቋጫል ብለዋል፡፡ ሼህ ሱልጣን ለይሱን ደግሞ በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ የሚኖሩ አበጋር ናቸው፡፡ እርሳቸውም እንደሚሉት አበጋር ማለት አስታራቂ ማለት ሲኾን የአስታራቂ ሽማግሌዎች የማዕረግ ስምም ነው ብለዋል፡፡
በአበጋር የተበደለን በመካስ እና በዳይ ይቅርታ እንዲጠይቅ በማድረግ ቂም በቀል እንዲጠፋ ይደረጋል፡፡ ለተለያዩ የወንጀል ዓይነቶች የተለያዩ ካሳዎችንም እንደሚተገብሩ ገልጸውልናል፡፡ ለአብነትም ለሰው ሕይዎት መጥፋት 2 መቶ ሺህ ብር፣ ለአካል ጉዳት እና ለሌሎች የንብረት ውድመቶች በየደረጃው የተቀመጡ ቅጣቶችን በዳይ ለተበዳይ እንዲክስ ይደረጋል ነው ያሉት፡፡ የታረቁ ወገኖችም እርቁን አክብረው በሰላም ይኖራሉ፡፡
ከዚህ በተቃራኒው እርቁን አፍርሶ የተገኘ ሰው ከማኅበራዊ ሕይዎት በማግለል አካባቢውን እስከማስለቀቅ የሚደርስ ቅጣት ስላለው ማንም ከባሕሉ አፈንግጦ የሚወጣ የለም ነው ያሉት፡፡ የዞኑ ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ይህንን ባሕላዊ እሴት አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ በጽሑፍ እና በዶክመንታሪ ፊልም መሰነዱን ከዞኑ ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡
አበጋሮችም ከወረዳ ጀምሮ እስከ ክልል ድረስ እውቅና እንዲያገኙ፣ ማበረታቻዎችን በመስጠት እና በተለያዩ መድረኮች እየተገኙ ተሞክሯቸውን እንዲያጋሩ እየተደረገም ነው፡፡
ዘጋቢ፡ ፍሬሕይዎት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን