የትፋሻ ፏፏቴ!

0
75

ባሕር ዳር: ግንቦት 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የትፋሻ ፏፏቴ በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በጠገዴ ወረዳ የሚገኝ ውብ የተፈጥሮ ጸጋ ነው። የፏፏቴው መገኛ ቦታ የአየር ጸባይ ደጋ እና ወይናደጋ በመኾኑ ለሁሉም ነገር የተመቼ ነው። ፏፏቴውን ለዐይን የሚማርክ ተራራ፣ ሸለቆ እና ሜዳማ መልክዓ ምድር እምቧለሌ ተጠምጥመውበታል።

የትፋሻ ፏፏቴ ከወረዳው ዋና ከተማ ማክሰኞ ገበያ በ1 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። የፏፏቴው ዙሪያ ገባ በበርካታ ሀገር በቀል እጽዋት የተሸፈነ በመኾኑ አየሩ ልዩ ነው። በተለይ ከግንቦት እስከ ጥቅምት ወራት ድረስ ፏፏቴው እጅግ ለምለም ነው። በእነዚህ ወራት ውስጥም አካባቢው አረንጓዴ ሥጋጃ የተነጠፈበት ይመስላል። ያምራል! በዙሪያው የሚገኙት ዛፎችም አረንጓዴ ወዘናቸውን እንደጠበቁ ይዘልቃሉ።

በዚህ ወቅት ከተራራ ላይ ወጥቶ ቁልቁል ለተመለከተ ሀገር ጎብኝ አካባባቢው የአማዞን ጫካን ያስታውሰዋል። አካባቢውን ለቅቆ ለመሄድ ያስቸግረዋል። ፏፏቴው ከላይ ተነስቶ የአለት ንብርብሩ ጋር እስከ ሚደርስበት ያለው ርቀት 120 ሜትር ርዝመት አለው። ከዚህ ርቀት ላይ ተነስቶ ሲወረወር የሚፈጥረው ድምጽ ለመንፈስ ልዩ ግርማ ሞገስን ያላብሳል። ውኃወም መልካም የአማራ ሴት የነደፈችው ጥጥ ያስመስለዋል። የትፋሻ ፏፏቴ ወደ ጎን 20 ሜትር ስፋት አለው።

በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በጠገዴ ወረዳ የቱሪስት መዳረሻ ልማት ባለሙያ ደሳለኝ ነጋ ለአሚኮ እንደተናገሩት ፏፏቴው ከከተማ በቅርብ እርቀት እንደመገኘቱ የእድሜና ጾታ ልዩነት ሳይኖር የአካባቢው ማኅበረሰብ የሚዝናናበት ድንቅ ሥፍራ ነው፡፡ ባለሙያው ይህንን ሥፍራ ለማልማት ጥረቶች መቀጠላቸውንም አስረድተዋል፡፡ ትፋሻ ፏፏቴን ማልማት በቱሪስት ልማቱ ዘርፍ አካባቢውንም ኾነ የአማራ ክልልን በእጅጉ ተጠቃሚ እንደሚያደርገው ነው የገለጹት፡፡

በቀደመው ሥርዓት የትፋሻ ፏፏቴን እንደ ሀገር አንጡራ ሃብት ቆጥሮ ከማልማት ይልቅ ውኃው ወደ ፏፏቴው እንዳይሄድ በማድረግ ለማድረቅ እና ለማጥፋት ተሠርቷል ነው ያሉት አቶ ደሳለኝ። ለአብነትም የትፋሻ ፏፏቴን ውኃ አቅጣጫ አስቀይሮ ለመስኖ በሚል ሰበብ ደብዛውን ለማጥፋት ተሞክሮ እንደነበርም ጠቁመዋል።

አሁን ፏፏቴው ለአካባቢው እና ለክልሉ የገቢ ምንጭ እንዲኾን እየተሠራ መኾኑንም ባለሙያው ተናግረዋል።

ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here