“ቅርስ ያለው ታሪክ አለው” አሉላ ፓንክረስት (ዶ.ር)

0
84

ደሴ: ግንቦት 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ባሕላዊ ቅርሶች እና ማኅበራዊ ሽግግር ላይ ባደረጉዋቸው ሰፊ ጥናቶቻቸው ዕውቅናን ያተረፉ ማኅበራዊ አንትሮፖሎጂስት እና ተመራማሪ ናቸው አሉላ ፓንክረስት (ዶ.ር)። የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር ምክትል ፕሬዝዳንት እና የቅርስ አስመላሽ ብሔራዊ ኮሚቴ አባልም በመኾንም እያገለገሉ ይገኛሉ።

የደሴ ሙዚየም እድሳትና ጥገና ተደርጎለት ዳግም አገልግሎት መሰጠት በጀመረበት በዛሬው ሥነ ሥርዓት ላይ ዶክተር አሉላ ፓንክረስት ተገኝተዋል። በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይም ሙዚየም ትውልድን የሚያገናኝ ድልድይ፤ የባሕል ሽግግር እዲፈጠር የሚያስችል፤ ለትምህርት፣ ለምርምር እና ለፈጠራ የሚያግዝ ኀይል ነው ብለዋል ዶክተር አሉላ ፓንክረስት።

አንጋፋው የደሴ ሙዚየም በተፈጥሮ እና በጦርነት ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት እንደነበረ ዶክተር አሉላ ጠቅሰዋል። ሙዚየሙ ታሪካዊ ይዘቱን ሳይለቅ ዘመኑን በዋጀ መልኩ መታደሱ እንዳስደሰታቸውም አንስተዋል። ቅርሶችን ለመጠበቅ ኅብረተሰቡን ማስተማር እና ስለታሪክ እና ስለማንነት ማሳወቅ ተገቢ ነውም ብለዋል።

የአኹኑ ትውልድ ከቴክኖሎጂ ጋር የተሳሰረ መኾኑን የገለጹት ዶክተር አሉላ ፓንክረስት በሌሎች ዓለማት እንደምናዬው በሙዚየሞች ውስጥ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ትውልዱ ታሪኩን እና ማንነቱን እንዲያውቅ ማድረግ ይቻላልም ብለዋል። ከሙዚየሙ በርካታ ቅርሶች ተዘርፈዋል ያሉት ዶክተር አሉላ ፓንክረስት የጠፉ ቅርሶችን ለማስመለስ ሁሉም ሊረባረብ ይገባልም ነው ያሉት። “ቅርስ ያለው ታሪክ አለውም” ብለዋል።

ወሎ በግጭት አፈታት፣ በድርድር እና በሽምግልና ይታወቃል ያሉት ዶክተር አሉላ የጠፉ፣ የተዘረፉ ቅርሶችን ከውጭ ሀገራት ከማስመለስ ባለፈ ጠፍተው በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚገኙትንም በማግባባት ማስመለስ እንደሚገባም ገልጸዋል።

ዘጋቢ፦ መስዑድ ጀማል

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here