ታሪክን ያሻገረው ብራና!

0
156

ባሕር ዳር: ግንቦት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አብዛኛው የዓለም ሀገራት ታሪካቸውን በአፈ ታሪክ ሲያስተላልፍ በነበረበት ዘመን ኢትዮጵያውያን ፊደል እና ቁጥር ቀርጸው፤ ሥዕል ሥለው፤ በረቀቀ መልኩ ታሪክን እና ጥበብን ከትበው ከትውልድ ወደ ትውልድ አስተላልፈዋል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያን የፊደል እና የቁጥር ባለቤት ከኾኑት ጥቂት የዓለም ሀገራት ውስጥ አንዷ እንድትኾን አድርገዋል። በአፍሪካ ደግሞ ብቸኛዋ ሀገር ናት። በዘመናት ሂደት የዳበረ እና የጠነከረ ሥልጣኔ እና ታሪክ ያላት ሀገርም አድርጓታል።

ኢትዮጵያ ታሪካዊ እና የብዙ ቅርሶች መገኛ ከሚያደርጓት ሃብቶች አንዱ የብራና ቅርሷ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ከልዩ ልዩ እንስሳት እና አራዊት ቆዳ በተዘጋጁ ብራናዎች ላይ ታሪካቸውን ከትበው ከትውልድ ወደ ትውልድ አስተላልፈዋል። ብራና ለትምህርት መማሪያ፣ ለመልዕክት መለዋወጫ፣ ደንብን፣ ወግ እና ሥርዓትን ለማውጣት፤ አዋጅ እና ትዕዛዝ ለማስተላለፍ፣ ታሪክን ለመመዝገብ ጥቅም ላይ ውሏል። የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ሥልጣኔ፣ ማንነት እና ስለ ድንበሯ ቅርሶች ወዘተ ተሰንዶባቸዋል፡፡

የዜማ፣ የኪነ ጥበብ፣ ሥነ ሥዕል፣ ቅርጻ ቅርጽ፣ ኪነ ሕንጻ፣ ሥነ ጽሑፍ፣ ሥለ ከዋክብት ጥናት፣ የዘመን አቆጣጠር፣ ስለ አልባሳት እና ጌጣጌጥ አዘገጃጀት፣ ሥለ ማዕድናት፣ ስለ መድኃኒት ቅመማ፣ ስለ ሥነ ፈለግ፣ የሒሳብ ቀመር፣ ፍልስፍና ወዘተ ያልዳሰሱት ነገር የለም ማለት ይቻላል፡፡ ዛሬ ለተፈጠሩት የሥልጣኔ እና ዘመናዊ ሁነት፤ የባሕል መዳበር ሥር መሠረት እና ፈር ቀዳጆች ናቸው፡፡

በአኺኑ ሰዓት ከኛ ከባለቤቶቹ ይልቅ የውጭ ሀገራት መጻሕፍቱን መርምረው በበለጠ ሲጠቀሙባቸው ይታያል፡፡

👉 ብራና ከምን ይዘጋጃል?

በኢትዮጵያ ታሪክ ብራና ለጽሕፈት ከማገልገሉ በፊት ጽሑፍ ይጻፍ የነበረው በድንጋይ፣ በብረት፣ በእንጨት ወዘተ ላይ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል፡፡ በሂደት ደግሞ ብራናን ለመጻፊያነት መጠቀም ተጀመረ ይላል። መቼ እና ማን እንደጀመረው ብዙ ጥናት የሚጠይቅ ቢኾንም ከ1500 ዓመታት በፊት እንደተጀመረም ይነገራል።

ብራና ከሚዘጋጅባቸው ነገሮች ውስጥ የበሬ፣ የበግ፣ የፍየል፣ የፈረስ ቆዳዎች በዋነኛነት ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይ የፍየል ጠቦት ቆዳ ለብራና አገልግሎት በጣም ተመራጭ ነው እንደኾነም ይነገራል። በዘመናችን የመጻፍያ መሳሪያ የኾነው ወረቀት ከመፈጠሩ በፊት ብራና ለረጅም ዘመናት ለጽሕፈት አገልግሏል። እስካኹን የሰው ልጅ ከደረሰባቸው እንደ ደንገል (ፓፒረስ ) እና ወረቀት ከመሰሉ የጽሑፍ መሳሪያዎች ይልቅ ብራና ረጅም ዘመን መቆየት የቻለ ነው።

👉 ምን ዓይነት ቀለማት ጥቅም ላይ ውለዋል?

ጥቁር እና ቀይ በአብዛኛው ለጽሕፈት ጥቅም ላይ የዋሉ ቀለማት ናቸው። ጥቁሩ ሐተታ ለመጻፍ ሲያገለግል፣ ቀዩ ደግሞ የእግዚአብሔርን፣ የቅድስት ድንግል ማርያምን፣ የቅዱሳትን እና የሰማዕታትን ሥም ለመጻፍ ይጠቀሙበታል፡፡ ከሁለቱ ቀለማት በተጨማሪ ሰባቱ ቀለማት የተባሉትን ማለትም ቢጫ፣ ወይን ጠጅ፣ አረንጓዴ፣ ውኃ ሰማያዊ እና ነጭ ቀለማት ሥዕሎችን እና ሐረጋትን ለመሳል ሲጠቀሙባቸው እንደነበር በታሪክ ተከትቧል።

👉 ቀለማቱ በምን ይዘጋጃሉ ?

የተለያዩ ኅብረ መልክ ያላቸውን ቀለማት ከተለያዩ የዕፅዋት ቅጠል፣ አበባ እና ሥር፣ ከተለያዩ አዝርዕት እና አፈር በተለያየ ዘዴ በማዋሃድ ይዘጋጃሉ።

👉 ጥቁር ቀለም፡- ይህን ቀለም ለማምጣት ልዩ ልዩ ዕፅዋት በማሳረር ይዘጋጃል። ከዚህም ባለፈ ከጥላሸት፣ ከሐሩር እህል ይዘጋጃል ይላል ታሪኩ፡፡

👉 ቀይ ቀለም፡- ልዩ ልዩ ቀይ ቀለማት ያላቸውን አበቦች፣ የጅብ ሽንኩርት አበባ፣ የቀጋ አበባ፣ ከበርበሬ ዛላ፣ ቀይ አፈር ተፈጭቶ፣ ተነፍቶ፣ ተቀቅሎ ከእንቁላል አስኳል እና ሙጫ ጋር ተደባልቆም ይዘጋጃል፡፡ ከዚህ ባለፈ ሌሎችን ቀለማት በማዳቀልም ይዘጋጃል።

👉 የመጻፊያ ብዕሩን በተመለከተ ቀጫጭን መቃ እና ሸምበቆ ሹል ኾኖ ተቀረጾ ለመጻፊያነት ያገለግላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የታላላቅ አሞራዎችን ላባም ለብዕርነት ይውል እንደነበርም ታሪኩ ያስረዳል፡፡

በመረጃ ምንጭነት ኃይለማሪያም ኤፍሬም በ2013 ዓ.ም ያሳተሙት ድብ አንበሳ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ቅርስ፣ ባሕል እና የተፈጥሮ መስህብ በሚል ያሳተሙትን መጽሐፍ እና የተለያዩ ሰነዶችን ተጠቅመናል።

ዘጋቢ: ዳግማዊ ተሠራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here