ዳረጎት- የድንቁ ምድር አንዱ መገለጫ!

0
61

ባሕር ዳር: ሰኔ 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ምግቡ በመሶብ ቀርቦ ሁሉም እንደ ባሕሉ እና እንደ ሥርዓቱ ቤት ያፈራውን መመገብ ያለ እና የነበረ እሴት ነው። በዚህ መሶብ ላይ ፍቅር ይታያል፣ መተሳሰብ ከፍ ብሎ ይገለጻል። በዚህ ሂደት ውስጥ ታዲያ አንዱ ለሌላው እጁ የቻለለትን አመቻችቶ እና አስተካክሎ እንካችሁ ይላል ለወደደው እና ላፈቀረው ሰው።

“ፍቅር እና ጉርሻ ሲያስጨንቅ ነው” እያለም የፍቅሩን መጠን ሊገልጽ ከመአዱ ያነሳውን ህብስት እንካችሁ ይላል። ተቀባዩም አያንገራግርም አፉ የቻለለትን ጎርሶ በእጁ ደግፎ እና በልቡ ደግሞ ሞልቶ ከፈሰሰው ፍቅር እየተጋራ የሚያስጨንቀውን ፍቅር እና ጉርሻ በደስታ ይቀበላል።

በኢትዮጵያ ብሎም በአማራ ምድር አጥብቆ ላጠና እና አስተውሎ ለቃኘው ብዙ ድንቅ ነገሮችን አቅፎ ይዟል። በርካታ ባሕል እና ዕሴቶች አቅፎ የያዘው ይህ ምድር የፍቅሩ መግለጫ ዳረጎት (ጉርሻ)ነው። ዳረጎት (ጉርሻ) በድንቁ የአማራ ምድር በሁሉም አካባቢዎች የሚታወቅ እና የሚተገበርም እሴት ነው።
ይህ የፍቅር እና የመተሳሰብ መግለጫ ነው።

አባት ለልጁ አለያም እናት ለልጇ የፍቅራቸው መገለጫ አድርገው ሲጠቀሙበትም ይስተዋላል። የቀየው ሕዝብ ባዘጋጀው ግብዣ ላይም ይኸው ድንቅ ትውፊት ይተገበራል። በአጉራሹ “በሞቴ፤ አፈር ስኾን” እየተባለ በተቀባዩ “ምንባልክ” የሚል ምላሽ እየተሰጠ ከብስቱ አልፎ ፍቅር ይጎመራል፤ አካባቢው በሳቅ ይደምቃል፤ ሰላምም ደምቆ ይታያል።

ይህ እሴት የአብሮነት እና የመተሳሰብ ማንበሪያና ትልቅ ማስተሳሰሪያ ገመድ ኾኖ ለረጅም ዘመን ተሻግሯል። ፍቅርን አጽንቷል፤ መተሳሰብን አስፍኗል፤ አንተ ትብስ አንች ትብሽ አባብሏል፤ ፍቅር እንዲጎመራ ሰላም እንዲደምቅ እና ከፍ ብሎ እንዲታይ አድርጎ ቆይቷል። በተለይ የመዓዱ ማሳረጊያ የኾነው ዳረጎት (ጉርሻ) ለአካባቢው፤ ለቀየው እና ለመንደሩ ፍቅርን የሚያጋባ መተሳሰብን የሚያጭር ነው።

ቀደም ባሉ ዘመናት በነበሩ ነገሥታት ይዘጋጅ በነበረ የንጉሥ እራት ዳረጎት በስፋት የሚከወን የማዕድ ዙሪያ ትዕይንት ነበር። በአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የባሕል እሴቶች እና ኢንዱስትሪ ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ብርሃን ጸጋዬ ይህንን እሴት የበለጠ ለማጎልበት እስካሁን የተደራጀ ሥራ ባይሠራም በየዓመቱ በሚከናውነው የንጉሥ እራት ዝግጅት ላይ እንደሚተገበር ገልጸዋል።

ቢሮው እንደ አንድ እሴት ሊሠራበት የሚገባው እንደኾነም ያምናል ነው ያሉት። እሴቱ ፍቅርን እና አንድነትን የሚያኖር በመኾኑ ወደፊት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራም አስገንዝበዋል።

ከክልሉም አልፎ ከሌሎችም ሕዝቦች ጋር ያለውን መልካም ግንኙነት እና አንድነት ለማጠናከር እንዲህ አይነት እሴቶች ተግባራዊ ቢደረጉ የተሻለ ለውጥ የሚያመጡ በመኾኑ ወደፊት ትኩረት ሰጥተው እንደሚሠሩበት ነው ያብራሩት።

ዘጋቢ: ምሥጋናው ብርሃኔ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here