የቱሪዝም እንቅስቃሴው ተስፋ ሰጭ ነው።

0
80

ባሕር ዳር: ሰኔ 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ብዙ የቱሪዝም ሃብቶች የሚገኙበት እና የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ መስህቦች ባለቤት ነው፡፡ በርካታ ቁጥር ያላቸው የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኝዎችም ክልሉን ይጎበኙታል፡፡ ቱሪዝም ለክልሉም ኾነ ለሀገራችን የሚያበረክተው አስተዋጽኦም ቀላል የሚባል አይደለም፡፡

ይኹንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልሉ በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት ቱሪዝሙ መቀዛቀዝ ውስጥ ገብቷል፡፡ አቶ ቸርነት አንዳርጌ በደባርቅ ከተማ የሆቴል ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ በክልላችን በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት የሆቴል እና የቱሪዝም ዘርፉ በጣም ተጎድቶ ነበር ብለዋል።
አኹን ባለው አንጻራዊ ሰላም ደግሞ አልፎ አልፎ ጎብኝዎች ወደ ከተማችን መምጣት ጀምረዋል ነው ያሉት፡፡

አኹንም ያለው ነገር አጥጋቢ ነው ባይባልም ቢያንስ ከመቀዛቀዝ ወጥተን የተወሰነ መንቀሳቀስ ጀምረናል ብለዋል፡፡ በፊት ምንም አይነት የመኝታ አገልግሎት የማንሰጥበት ጊዜ ነበር አኹን ግን በተወሰነ መልኩ እየተንቀሳቀስን ነው፤ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ወደ ከተማችን እየመጡ ነው፤ አገልግሎትም እየሰጠን እንገኛለን ነው ያሉት፡፡

እንደ አቶ ቸርነት ገለጻ አኹንም ቢኾን እንቅስቃሴውን ሰላማዊ አድርጎ በማስቀጠል የበለጠ ጎብኝዎች ወደ ከተማችን እንዲመጡ የሰላሙ ኹኔታ ተሻሽሎ መቀጠል አንዳለበት ገልጸዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ከጎንደር ወደ ደባርቅ ጎብኝዎች የሚመጡት በመኪና በመኾኑ መንገድ ላይ ያለው የጸጥታ ችግር መሻሻል እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

በደባርቅ ከተማ አሥተዳደር የባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የቱሪስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ብቃት ማረጋገጥ ባለሙያ ጀማነሽ ካሴ አኹን በከተማችን ባለው አንጻራዊ ሰላም የቱሪዝም እንቅስቃሴው ያለፉትን ሁለት ወራት ጨምሮ በተወሰነ መልኩ መሻሻል የታየበት መኾኑን ገልጸዋል፡፡

በደባርቅ አቅራቢያ የሚገኘውን የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ የሚጎበኙ የውጭ ሀገር እና የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ቁጥር እየተሻሻለ መጥቷል ነው ያሉት፡፡ ነገር ግን ጎብኝዎች ቢመጡም የቆይታ ጊዜያቸው በጣም አጭር ነው፤ አብዛኛዎቹም ሳያድሩ እንደሚመለሱ ነው የተናገሩት፡፡

ይህ ደግሞ ከተማዋ ከዘረፉ የምታገኘውን ገቢ ይቀንሰዋል ብለዋል። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የጸጥታ ችግሩ የፈጠረው ስጋት መኾኑን አንስተዋል። አኹን ያለው እንቅስቃሴ ከነበረው ነባራዊ ኹኔታ አንጻር የተሻለ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል ነው ያሉት፡፡ በቀጣይ የቱሪዝም እንቅስቃሴውን አጠናክሮ ለመቀጠል የሰላሙን ኹኔታ ማሻሻል አስፈላጊ እንደኾነም ነው የተናገሩት፡፡

የአካባቢው ኅብረተሰብ እና መንግሥት በጋራ መሥራት አለባቸው ብለዋል። እንደ ባሕል እና ቱሪዝም ተቋም በሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፉ የተሠማሩ ባለሃብቶችን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን የማወያየት እና ለሚመጡ ጎብኝዎች የተሻለ አግልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ድጋፍ እየተደረገ መኾኑንም አንስተዋል፡፡
የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ አባይ መንግሥቴ በክልላችን በተከሰተው የጸጥታ ችግር ቱሪዝሙ በችግር ላይ ያለ መኾኑ የሚታወቅ ነው ብለዋል፡፡

ግን ደግሞ በችግር ውስጥ ቢኾን በተቻለ መጠን የሚጎበኙት የክልላችን ሃብቶች፣ ባሕል እና ቅርሶች የሕዝቡ ሃብቶች በመኾናቸው እና የጎብኝዎችን ደህንነት ሕዝቡ የሚጠብቅ በመኾኑ እስካኹን ድረስ በጎብኝዎች ላይ የደረሰ ጉዳትም የለም ብለዋል፡፡
የጸጥታ ችግሩ ሙሉ በሙሉ ባይቀረፍም የቱሪዝም እንቅስቃሴውን ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ እንደኾነ ነው የገለጹት፡፡

በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች አስተማማኝ ሰላም ተደራሽ አድርገናል ብለን ባንወስድም ቢያንስ “አንጻራዊ ሰላም በሰፈነባቸው ዋና ዋና መዳረሻዎች ማለትም ጎንደር፣ ደባርቅ፣ ላሊበላ እና ባሕር ዳር የቱሪዝም እንቅስቃሴው እየተሻሻለ እንደመጣ ነው” ብለዋል።

የቱሪዝም ዘርፉ ኢኮኖሚውን ከመቆም ወደ መንቀሳቀስ ሊወስድ የሚችል የማይበገር ዘርፍ ለማድረግ የሚሠራውን ሥራ የሚያሳይ እና ለወደፊትም ልምድ የተገኘበት መኾኑንም አንስተዋል፡፡

ሰላሙ ከዚህ በላይ እየተሻሻለ የሚሄድ ከኾነ የክልሉ የቱሪዝም ሃብቶች በጣም ሰፊ በመኾናቸው የማርኬቲንግ እና የትውውቅ ተግባራት ላይ መበርታት ይኖርብናል ብለዋል።

በሚቀጥለው በጀት ዓመት ወደ ክልላችን የሚመጡ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ጎብኝዎችን ፍሰት መጨመር እና ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ እንደኾነም ነው የገለጹት፡፡

በዚህ ወቅት እየታየ ያለው መነቃቃት ለቀጣይ ዓመት ዘርፉን ተስፋ ሰጭ አድርጎታልም ብለዋል።

ዘጋቢ፡ ፍሬሕይወት አዘዘው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here