የገጠር ሠርግ ትዝታዬ

0
198

ባሕር ዳር: ሰኔ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በትዝታ ፈረስ ሽምጥ እየጋለብሁ ልጅነቴን ካሳለፍሁባት፣ ትውስታዬን ካኖርሁባት ከደጋማዋ ጽዮን ማርያም ሰናፍጭ ከምትባል መንደር ደርሻለሁ። ጽዮን ማርያም ከደብረ ማርቆስ ከተማ በስተምሥራቅ አቅጣጫ ፈጠን ብሎ ለተጓዘ ሰው በግምት እስከ ሦስት ሰዓት ከሚወስድ የእግር ጉዞ በኋላ የምትገኝ ቦታ ናት።

ሰናፍጭ በምትባለው የገጠር መንደር በልጅነቴ አታሞ (ከበሮ) በተመታበት ቤት ቀርቼ አላውቅም። አያሌ ኮረዶች እና ጎረምሶች በጋብቻ ሲጣመሩ ቆሜ አጨብጭቤ ድሬአለሁ። አሁን ሳስታውስ በክብር እንደተጠራ ሽማግሌ ሠርግ በሚሠረግበት ቤት ከዋዜማው ጀምሮ ቀድሜ ነበር የምገኘው። ታዲያ የልጅነቴ ትዝታ ዛሬ ላይ የጎጃምን የሠርግ ሥርዓት መለስ ብዬ እንዳይ ቀሰቀሰኝ።

ሠርግ የወጣቶች የአዲስ ሕይዎት መጀመሪያ፣ ለወላጆች ደግሞ የልጆችን አዱኛ ማያ መነፅር ነው። በጎጃምም የልጁን አዱኛ ለማየት ያሰበ ወላጅ በተለይም የወንድ ልጅ አባት እና እናት ስለልጃቸው የጋብቻ ሁኔታ ቁጭ ብለው ይመክራሉ። ልጃቸው ለአዱኛ መድረሱን፣ ከማን ዘር መጋባት እንዳለባቸው፣ የሠርግ ወጭን የሚሸፍን ምርት ስለመኖሩ በዝርዝር ከተወያዩ በኋላ ልጃቸውን ለመዳር ይወስናሉ።

የወንድ ወላጆች ወደ ሴቷ ወላጆች ሽማግሌዎችን ይልካሉ፣ ሽማግሌዎቹ ከሴት ወላጆች ቤት ሲደርሱ እንዴት አደራችሁ፣ እንዴት ዋላችሁ ብለው ከደጅ ይቀመጣሉ። የሴት ወላጆችም ምንድን ነው ነገሩ? ሲሉ ይጠይቃሉ። ሽማግሌዎችም ስለጋብቻ ጥየቃው ያስረዳሉ፣ የሴት ወላጆችም ጉዳዩን ከሰሙ በኋላ እንምከርበት ብለው ሽማግሌዎችን ይመልሳሉ። ወላጆችም ቁጭ ብለው ስለመጣው ሰው ዘር፣ የጠንካራ ገበሬ ቤተሰብ ስለመኾኑ፣ ስለልጁ ቁምነገረኛነት፣ ስለመደገስ አቅማቸው ይመክራሉ፣ ይወስናሉ።

ሽማግሌዎች ስለጋብቻው መልስ ለማግኘት እስከ ሦስት ጊዜ እልፍ ሲልም እስከ አራት ጊዜ ሊመላለሱ ይችላሉ። በጎጃም ባሕል የሴት ወላጆች በአንድ ጊዜ እሺ፣ አበጀ ብለው የሽማግሌዎችን ጥያቄ መቀበል እንደነውር ስለሚቆጠር የሽማግሌዎች መመላለስ የግድ ነው። ከብዙ መመላለስ በኋላ ሽማግሌዎቹ ከሴት ወላጆች እሺ፣ ይሁን የሚለውን መልስ ለወንድ ወላጆች ያበስራሉ። የልጆቹ ወላጆችም ተገናኝተው ሠርጉ መቼ እንደሚኾን ቀን ይቆረጥለታል ይህም “ቀጣር” ይባላል። የሠርጉ ዝግጅት በሁለቱም ወገን ያኔ ይጀመራል።

በገጠራማው የጎጃም አካባቢ ሠርግ ለወላጆች ብቻ “ራሳቸው ይወጡት” ተብሎ የሚተው አይደለም። ይልቁንም የቅርቡም የሩቁም ዘመድ ወሬውን እንደሰማ አንድ እንስራ ጠላ፣ ሁለት እንስራ ጠላ (ግማሽ አቆልቋይ) ወይም አንድ አቆልቋይ (አራት እንስራ ጠላ ከመቶ እንጀራ ጋር) እይዛለሁ እያለ ለባለጉዳዩ ይናገራል። ባለጉዳዩም ሠርጉ ስንት አቆልቋይ እንደሚወስድ ገምቶ እና ተረፍረፍ አድርጎ ይደግሳል።

አይደረስ የለ የሠርጉ ቀን ይደርሳል። በዋዜማው ለት ዘመድ አዝማዱ ይሠባሠባል። ሁነኛ ሰው ተመርጦ በጠዋት የመንደሩን ነዋሪዎች በየቤታቸው እያንኳኳ “አያ እገሌ” ልጄን መርቁልኝ ብሏል እያለ ይጠራል። ቤተ ዘመዱ በጠዋቱ በአንድ በኩል ዳሱን ይጥላል (ይሠራል)፣ በሌላ በኩል የሙሽራውን ጫጉላ ያዘጋጃል። ዳሱ እና ጫጉላው እንደተሠራ ፊሪዳ (የበሬ እርድ) ይጣላል። ፊሪዳው ላይ የሚገኙ የቅርብ ዘመድ እና ከመንደሩ የተመረጡ ሽማግሌዎች ብቻ ናቸው። ለፊሪዳ የተባለው አቆልቋይ ይቀርባል፣ ቅቤው ተሰልሶ በቁርጥ ስጋ (ጉማ) ይበላል። ቁርጥ ስጋ በአካባቢው “ጉማ” ተብሎ ነው የሚጠራው። ተሰቅሎ የኖረው አታሞውም (ከበሮ) ይወርድና ስብ (ጮማ) ተቀብቶ ጥሩ ድምፅ እንዲያወጣ በፀሐይ ይሞቃል።

ለዋዜማው አቆልቋይ የያዙ ሰዎች ስጋ ይሰጣቸው እና ወጥ ይሠራሉ። የተጠሩትን የመንደሩን ነዋሪዎች ተዘጋጅተው ይጠብቃሉ። ፀሐይ ዘቅዘቅ ስትል ወደ 10:00 ሰዓት ገደማ ጥሪ የተደረገላቸው የመንደሩ ነዋሪዎች ወደ ሠርጉ ቤት ይመጣሉ። አስተናጋጆች እየተቀበሉ በየአቆልቋያቸው ያስቀምጧቸዋል። ጠላው ይቀርባል፣ እንጀራው ይበላል፣ ይመረቃል፣ ከዚያማ አሼሼ ገዳሜ (ዘፈን) ይጀመራል።

የመንደሩ ሰው ፀሐይ የሞቀውን፣ በስብ የጠገበውን አታሞ እየመታ ሌሊቱን ሙሉ ሲደነከር (ሲጨፈር) ያድራል። የላብ መተኪያ በሚል አሳላፊ ሌሊቱን ሙሉ ወገቡን አስሮ ጠላ ሲቀዳ፣ ደንካሪው ሲጠጣ ነው የሚያድረው። ጠዋት የሠርጉ ‘ለታ የመንደሩ ወጣቶች፣ ልጃገረዶች እና ልጆች ይሠባሠባሉ። ፈረስ ይዘጋጃል፣ አንድ አስር እንጀራ በድቁስ (በአዋዜ) ተቀብቶ፣ በጽዋ ድፍድፍ ተይዞ ሙሽራው ወይም ሙሽሪት በፈረሱ ላይ ተቀምጦ/ጣ የሆም አበባዬ የሆም እየተባለ እየተዘፈነ ጉዞ ይጀመራል።

ወዴት? በብዛት ወንዝ አካባቢ የሚበቅል ሆማ የሚባል ለምለም ዛፍ አለ። እኔም በአደግኩባት ጽዮን ማርያም ይሄ ዛፍ ነበረ። እናም ሙሽራው (ዋን) ሆማ ወደ አለበት ዛፍ ይዘን ሄደን ሦስት ጊዜ እንዞራለን። ከዚያ በጽዋ ያለውን ድፍድፍ ሙሽራው/ዋ ወርውሮ (ራ) በሆማው ዛፍ ይሠበራል። ጽዋው እንደተሰበረ ወዲያውኑ በአዋዜ የተቀባውን እንጀራ ሙሽራው (ዋ) እንደቀመሰ (ች) ከተሸከመችው ልጃገረድ አናት ላይ እንዳለ እንሻማዋለን።

በእጃችን ጨብጠን የያዝነውን እንጀራ እየበላን እና “የሆም አበባዬ የሆም…” እያልን እየዘፈንን ወደ ቤት እንመለሳለን። ከቤት እንደተመለስን ከገብስ የተዘጋጀ ገንፎ (ስልቅ ይባላል) እየተገነፋ ይጠብቀናል። ሙሽራውን (ዋን) ከቤት አስገብተን ትንሽ እንደነክራለን (እንጨፍራለን)። ትዝ የሚለኝ እና ያኔ የማይገባኝ ነገር የሙሽራው (ዋ) እናት ይዘነው የመጣነውን የሆማ ቅጠል በወንፊት ላይ አድርጋ፣ ከአናቷ ላይ አስቀምጣ የምትደነክረው (የምትጨፍረው) ነው። አሁን ለምን ብየ ሽማግሌ ስጠይቅ “ጋብቻው የለመለመ ይሁን” ብላ እናት ስትመኝ ነው አሉኝ።

በገንፎ ላይ የሚታደሙት ሆማ ቆረጣ የሄዱት ልጆች፣ ልጃገረዶች እና ወጣቶች ብቻ ናቸው። ከዳሱ ቁጭ እንል እና የስልቁን ገንፎ ቅቤው እየተንጠፈጠፈ ጥግብ እስክንል እንበላለን። ስምንት፣ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ ሠርገኛ (አጃቢ) ይገባል (ይሠባሠባል)። ሙሽራው ዝግጅት ያደርጋል። እንደ ከተማው ሦስት፣ አራት ሚዜ አያስፈልገውም የገጠር ሙሽራ። አንድ “አሳሳች” የሚባል በአካል ከሙሽራው ጋር የሚቀራረብ እና የቅርብ ጓደኛ ከአጠገቡ ይኾናል። ለሠርገኛ የተዘጋጀው አቆልቋይ ይቀርባል፣ ይበላል፣ ይጠጣል።

ከተበላ፣ ከተጠጣ በኋላ ሙሽራው ከፈረስ ላይ ወጥቶ ሰላሳ፣ አርባ የሚኾን ሠርገኛ እየተከተለ ወደ ሙሽራዋ ቤት ይሄዳሉ። የሙሽራዋ ሀገር ሁለት፣ ሦስት ሰዓት በእግር ሊያስጉዝ ይችላል። ሠርገኛው ሙሽራውን ይዞ ከሙሽሪት ቤት እንደደረሰ ከቤቱ በቅርብ ርቀት ሠብሠብ ብሎ ቁጭ ይላል።

ሙሽራው መምጣቱ በሙሽሪት ቤት እንደተሰማ ሽማግሌዎች ይላኩ እና ሙሽራውን ወደ ዳስ እንዲገባ ይጋብዙታል። “አናስገባም ሠርገኛ” የሚባለው ባሕላዊ ትንቅንቅ ይጀመራል። ሠርገኛ ፈንቅሎ ገብቶ ሙሽራዋን ይዞ ይወጣ እና ከዳስ ይቀመጣሉ። ለሙሽራ የተዘጋጀው አቆልቋይ (ሌማት) ቀርቦ ይበላል።
ለሙሽራ የሚቀርበው ሌማት በጥሩ ባለሙያ የተዘጋጀ የተመረጠ ጠላ እና ጣፍጦ የተሠራ የዶሮ ወጥ ነው።

ከተበላ በኋላ የሙሽራው የቅርብ ሰው የኾነ ሰው የሙሽራዋ “የስር ሚዜ” ተብሎ ይነሳል። ሙሽራዋ በሙሽራው ቤት የቅርብ ዘመድ የምትለው አሳዳሪውን ነው። አሳዳሪውም እንደ እህቱ እንደሚንከባከባት ቃል ይገባል። ቤተሰቦቿ የገዙላትን እና ያዘጋጁላትን አልባሳት (ሁለት፣ ሦስት ቀሚስ ከነጠላው ሊኾን ይችላል)፣ ጀንዲ (ከቆዳ የተሠራ መተኛ) እና መጠጊያ (ከውስጥ ገለባ፣ ከላይ ቆዳ ኾኖ የተሠራ ትራስ)፣ ኩል እና የፊት መስታወት ቆጥሮ ይረከባል።

ርክክቡ እንዳለቀ ሽማግሌዎች ይመርቃሉ፣ ትዳራቸው የተባረከ እና የሰመረ እንዲኾንላቸው ይመኛሉ። ሠርገኛው አታሞን ይዞ ይደልቃል፣ የምር ‘አቧራው ጨሰ” የሚባልለት ድንክራ ይደረግ እና የስር ሚዜው ሙሽሪትን አዝሎ ይዞ ይወጣል። ሠርገኛ ሙሽሪትን ይዞ የሚወጣው ምሽት ሁለት፣ ሦስት ሰዓት ላይ ሊኾን ይችላል። ሰርገኛ በእግሩ፣ ሙሽሮች በፈረስ ኾነው ጉዞ ይጀመራል። የሙሽራዋ ሀገር ራቅ ያለ ከኾነ የሙሽራው ቤት የሚደረሰው ሌሊት አምስት፣ ስድስት ሰዓት ላይ ሊኾን ይችላል።

ሠርገኛ ሙሽሪትን ይዞ ሲጓዝ ሌላ ሠርገኛ መንገድ ላይ ከተገናኘ ለየት ያለ ልማድ አለ፣ በገጠሩ የጎጃም አካባቢ። በተለይም በመስቀለኛ መንገድ አቋርጦ የሚያልፍ ከኾነ እኛ ነን አቋርጠን የምናልፍ ይላል የአንደኛው ሠርገኛ፣ ሌላኛው ደግሞ “አይ” እኛ እናቋርጥ በሚል ከፍተኛ ጠብ ይፈጠራል፣ ይሄ አጋጣሚ ከጦፈ ሙሽሮች ሁሉ ሊማረኩ ይችላሉ። ይህ የሚኾነው በጎጃም መንገድ ማቋረጥ እንደ መጥፎ ዕድል ስለሚወሰድ ነው።

ሙሽራው ከቤቱ እንደደረሰ ቤተ ዘመዱ እልል ብሎ ይቀበለዋል። በግ አርዶ ወደ ጫጉላቸው ይገባሉ። ሠርገኛ ጨፍሮ፣ ጠላ ጠጥቶ፣ የታረደውን በግ ጠብሶ በልቶ የመሸበት ያድራል፣ የቅርቡ ይሸኛል። በነጋታው (ከሠርጉ ማግስት) አንድ አስር የሚኾን ሰው ከሠርገኛው መካከል “ሚዜ” ተብሎ ይመረጣል፣ ሚዜዎቹ ከሙሽሪት ቤት ሄደው የማያሳፍሩ፣ “የሚዜውን ከርፋፋ በለው በአካፋ” የማያስብሉ ይልቁንም “አይ የእገሌ ሚዜዎች ጨዋታ ሲችሉ ተብለው የሚወራላቸው እንዲኾኑ” መደንከር እና ማቀንቀን የሚችሉት ናቸው የሚመረጡት።

በጎጃም በተለይም በገጠሩ ማኅበረሰብ ክብረ ንጽህናዋን (ድንግልና) ጠብቃ ለጋብቻ ዕለቷ የደረሰች ሴት ትልቅ ክብር ይሰጣታል። ክብረ ንጽህናን ጠብቆ መቆየት ለሙሽሪት ወላጆችም ትልቅ ክብር እና ሞገስ ያጎናጽፋል፣ ጥሩ አሳዳጊዎች እንደኾኑ ያስመሰክራል።

ሙሽራው የሙሽሪት ድንግልናዋን ወስዶ ያደረ ዕለት አመሻሽ ላይ ሚዜዎች ደም የነካ እራፊ ጨርቅ ይዘው ወደ ሙሽሪት ወላጆች ቤት ይሄዳሉ፣ “ብር አምባር ሰበረልዎ… ” እያሉ ይጨፍራሉ፣ የያዙትን ደም የነካ እራፊ ጨርቅ ለወላጆች፣ ለዘመድ አዝማዱ ያሳያሉ።

የሚዜዎች ድንከራያ ግሩም ነው። ሌሊቱ እስኪገባደድ የሙሽሪት ዘመድ አዝማድ በየተራ እየተነሳ ሚዜዎች ልባቸው ውልቅ እስኪል ሲያስደነክሩ ማደር የግድ ነው። ሚዜዎች ደከመን በቃን ቢሉ እንኳን ቤተ ዘመዱ በቃችሁ አይልም። “የሚዜ ከርፋፋ” ላለመባል ሚዜዎችም ደከመን የሚል ቃል ከአፋቸው አያወጡም፣ መደንከር ብቻ ነው። ቤተ ዘመዱ ይበቃል ሂዱ ሲል ሚዜዎች ወደ ሙሽራው ቤት ይመለሳሉ።

ከሚዜ የሚዘጋጅ ድግስም ልዩ ነው። ከሠርግ ድግስ በልዩ ጥንቃቄ የሚዘጋጀው የሙሽራ እና የሚዜ ድግስ ነው። የጠላው ጣዕም ከአፍ ላይ ይቀራል፣ ቅቤ በጉማ (ቁርጥ ስጋ) ነው የሚበላው። ይሄ ካልኾነ ሚዜ በምን አንጀቱ ሲደነክር ያድራል።

ከሠርጉ ማግስት ጀምሮ ለሙሽራዋ ልዩ እንክብካቤ ነው የሚደረገው። ለሙሽሪት ጠባቂ ጉብል (በእድሜ አነስ ያለች ሴት ወይም ወንድ ልጅ) ይመደባል። ጠባቂዋ ሙሽሪት ከጫጉላ ስትወጣ ፀሐይ እንዳታያት ጃን ጥላ ትይዛለች፣ የሚበላ የሚጠጣ ከዋናው ቤት ወደ ጫጉላ ታመላልሳለች፣ በጥቅሉ የሙሽሪት ታዛዥ ናት።

የሙሽራዋ መጠጫም ብርሌ ነው፣ በየዕለቱ ጠዋት ቁርስ ስልቅ ገንፎ በቅቤ ነው። ሙሽሪትን ለማየት በየቀኑ የመንደሩ ጉብል ሳምንቱን ሙሉ ከጫጉላ ይመጣል። ታዲያ ጉብላሊት (ልጆች) ሙሽሪትን ዝም ብለው ማየት አይችሉም። ያኔ በልጅነቴ እንደማስታውሰው ሙሽሪት ደኅና ከጠባቂዋ ጋር ስትጫወት የነበረችውን ልጆች ሲመጡ በነጠላዋ ሽፍንፍን ብላ ትቀመጣለች። ያኔ ልጆች ሙሽሪትን ለማየት ይከፍላሉ። ገንዘብ አይደለም የሚከፍሉት። የልብስ ቁልፍ፣ ዶቃ ወይም ዛጎል ነው የሚሰጧት።

ክፍያውን ከተቀበለች በኋላ ትንሽ ፊቷን ገለጥ አድርጋ ትታያለች። እንዲያ እያለች የሠበሠበችውን የልብስ ቁልፍ፣ ዶቃ ወይም ዛጎል የጫጉላ ጊዜው እንደማለፍ ሲል የልብስ ቁልፉን በልብሷ ላይ ሰፍታ፣ ዶቃውን በአንገቷ ክር ድር ድር አድርጋ ታጌጥበታለች።

ሠርጉ አንድ ሳምንት ሲኾነው የሙሽሪት የቅርብ ቤተዘመድ አንድ አራት ኾነው እንጀራውን፣ በርበሬውን፣ ቅባኑጉን ይዘው፣ ድፍድፉን፣ ዱቄቱን ጭነው ሙሽሪትን እንዴት ሰነበትሽ ብለው ለመጠየቅ ወደ ሙሽራው ቤት ይመጣሉ። ይህም ሥርዓት ፈቃጅ ይባላል። የሙሽሪት ቤተዘመድ ከሙሽራው ቤተሰብ ጋር ሲጫዋቱ አድረው በነጋታው ይመለሳሉ። ስለሙሽራዋ ደኅና መኾን ለወላጆቿ ይናገራሉ።

ምላሽ ከሁለት ወር በኋላ ነው የሚኾነው። የሠርጉ ሰሞን ቅበላ ከኾነ ከፋሲካ ግድፍት በኋላ ይደረጋል። ሠርጉ በፋሲካ ከኾነ ደግሞ የሰኔ ጾም ሲፈታ የሐምሌ አቦ ይኾናል። የሙሽሪት ወላጆች የሚመቸውን ቀን ወስነው ምላሽ ይጠራሉ።

የምላሹ ‘ዕለት ሙሽሮች ከአንድ አራት ሚዜዎች ጋር ኾነው፣ የበግ ሙክት ይዘው ከሙሽሪት ወላጆች ቤት ይሄዳሉ፣ እንደደረሱም የያዙትን በግ ሙሽራው ባርኮ ወደ ቤት ይገባሉ። ምላሹም ቀለል ያለ ሠርግ አይነት ነው። ቤተዘመዱ ይሠባሠባል፣ ይበላል፣ ይጠጣል፣ ይደነከራል። ሙሽሮቹ ወልዳችሁ፣ ከብዳችሁ ቤተሰብን የምትጠቅሙ ያድርጋችሁ ተብለው ይመረቃሉ።

ውድ አንባቢያን ያጋራኋችሁ ሀሳብ ከ30 ዓመታት በፊት በጎጃም የገጠሩ አካባቢ ባደግሁበት ሰፈር የነበረኝን የሠርግ ትዝታዬን ነው። እኔ ከአጋራኋችሁ የሠርግ ሥርዓት አሁን ላይ የጎደለ ወይም የተጨመረ ቢኖር ጊዜ የጨመረው ወይም የቀነሰው እንደኾነ ይወሰድልኝ።

በደመወዝ የቆዬ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here