ባሕር ዳር: ሰኔ 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በርካታ ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ የመስህብ ሀብቶች ይገኛሉ። በዓለም የተደነቀው የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት፣ ታሪክን፣ ጥበብን እና ተፈጥሮን አዋሕዶ የያዘው የጣና ሐይቅ፣ የፋሲል አብያተ መንግሥታት እንዲኹም ሌሎች ዘመን የማይሽራቸው ባሕላዊ እሴቶች ለአብነት ይጠቀሳሉ።
ታሪክ ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍበት የብራና መጻሕፍት፣ በየዘመኑ ኢትዮጵያን የመሯት የነገሥታት መገልገያዎችም በየአድባራቱ፣ መስጊዶች እና ሙዚየሞች ተሰንደው የሚገኙ ቅርሶችም በርካታ ናቸው። እነዚህ ሁሉ የቱሪዝም ምርቶች ተደርገው ይወሰዳሉ። ቱሪዝሙ ከሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ተቋዳሽ ለመኾን አይነተ ብዙ የኾኑትን የቱሪዝም ምርቶች በዘመናዊ መንገድ በማስተዋወቅ ወደ ዓለም ዓቀፉ ገበያ ማስገባት የግድ ይላል።
ቅርሶች እና ሌሎች መዳረሻዎችን በመለየት ወደ ቱሪዝም ገበያው ማስገባት የሚቻለው መለያ (ብራንድ) በመፋጠር ማስተዋወቅ ሲቻል ነው። በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝም እና ሆቴል ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል መምህር ብርሃኑ እሱባለው (ዶ.ር) የቱሪዝም መለያ (ብራንዲንግ) የሚባለው መዳረሻዎች ከሌሎች የሚለያቸው መገለጫዎችን አጠቃሎ የሚይዝ ልዩ መታወቂያ ነው በማለት ያብራራሉ።
ይህም በሰዎች አዕምሮ በቀላሉ ተቀርጾ ምናባዊ ምስልን የሚፈጥር እና ለረጅም ጊዜ የሚቆይ በመኾኑ የጎብኝዎችን ስሜት የመሳብ ኀይል እንዳለው ይገልጻሉ። የቱሪዝም መለያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቱሪስቶችን ለመሳብ ዋነኛ መሳሪያ ኾኖ ያገለግላል ነው ያሉት። በርካታ ሀገሮችም በስፋት የሚጠቀሙበት የገበያ ስልት እንደኾነም አመላክተዋል።
እንደ ዶክተር ብርሃኑ ገለጻ የቱሪዝም መለያ በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት። ዕውቅናን ያስገኛል፣ ጎብኝዎችን በቀላሉ ይስባል፣ ተደጋጋሚ ንግድን ይጨምራል፣ ዘላቂነትን ያመጣል ገጽታንም ይገነባል ነው ያሉት። በኢትዮጵያ የቱሪዝም መለያ በመቅረጽ በስፋት መሥራት የተጀመረው በአውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር ከ2016 ጀምሮ እንደኾነም ጠቅሰዋል።
በአማራ ክልል ደረጃ እስካኹን ድረስ የቱሪዝም መለያ እንዳልተዘጋጀ ጠቁመው የክልሉን እምቅ የቱሪዝም ሀብት በአግባቡ ማስተዋወቅ የመለያ ብራንድ እንደሚያስፈልገው ጠቁመዋል። ጎብኝ ወደ መዳረሻዎች እንዲመጣ አይረሴ መልዕክት በመቅረጽ፣ ስለመዳረሻዎች የተሟላ መረጃ መስጠት እና ዘመኑን በዋጀ የመረጃ ሥርዓት ማስተዋወቅ ለዘርፉ ዕድገት ወሳኝ እንደኾነም ነው ያብራሩት።
አካባቢያዊ የኾኑ ባሕላዊ ኹነቶችን አጭር እና ገላጭ በኾነ የቋንቋ አገላለጽ በመጠቀም እንደ መለያ ኾነው በማገልገል የጎላ ሚና እንዳላቸውም ነው የገለጹት። በተለይም ለሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አመላክተዋል። በክልል ደረጃ ክልላዊ የቱሪዝም መለያ ተሠርቶ በመጠናቀቅ ላይ መኾኑን የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል።
የተቀረጸው ክልላዊ የቱሪዝም መለያ በቅርቡ በይፋ ተመርቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ በቢሮው የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር መልካሙ አዳም ገልጸዋል። ከክልላዊ የቱሪዝም መለያ በተጨማሪ መዳረሻዎች የየራሳቸው መለያ በመፍጠር ለማስተዋወቅ ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት።
ዞኖች እና ከተማ አሥተዳደሮች በአካባቢያቸው ጎልተው የሚከበሩ ክብረ በዓላትን፣ ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ የመስህብ ሃብቶች በመምረጥ መለያ አድርገው እንዲሠሩ እየተሠራ መኾኑንም አብራርተዋል። እስካኹን በርካታ አካባቢዎች የራሳቸውን ባሕላዊ እሴቶች፣ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ የመስህብ ሃብቶችን መሠረት በማድረግ መለያ ብራንድ ለይተው በመሥራት ላይ መኾናቸውን አንስተዋል።
ለአብነትም ገናን በላሊበላ፣ ጥርን በባሕር ዳር፣ ጥምቀትን በጎንደር፣ ሻደይ በዋግ ኽምራ፣ እንግጫ ነቀላ በምሥራቅ ጎጃም፣ የአገው ፈረሰኞች በዓል በእንጅባራ፣ መርቆርዮስ በእስቴ እና ደብረ ታቦር እንዲኹም ሌሎችንም ጠቅሰዋል። ዞኖች እና ከተማ አሥተዳደሮች በዚህ መንገድ መሥራታቸው ኅብረተሰቡ በየአካባቢው ያለውን ሀብት አውቆ በባለቤትነት እንዲይዘው ዕድል እንደሚፈጥርም አመላክተዋል።
አካባቢያዊ መለያዎች ጎብኝዎች በክልሉ ያለውን እምቅ የቱሪዝም ሃብት በዝርዝር ለማወቅ እና በቀላሉ ለመጎብኘት ያስችላቸዋል ነው ያሉት።
የተጀመሩት አካባቢያዊ የቱሪዝም መለያዎች በየአካባቢው ያለውን የቱሪዝም ምርት በማስተዋወቅ ደረጃ ያላቸው ጠቀሜታ ከፍተኛ መኾኑን ጠቅሰው በሁሉም ዞኖች ከፍ ባለ ደረጃ እንዲተገበሩ ቢሮው እየሠራ ነው ብለዋል።
እነዚህን መነሻ በማድረግም በቀጣይ ለሁሉም ዞኖች ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ ከክልላዊ የቱሪዝም መለያው ጋር አስተሳስሮ ለመሥራት ጥረት እየተደረገ ስለመኾኑም ጠቁመዋል።
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን