ደባርቅ፡ ሰኔ 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት በፓርኩ ክልል ውስጥ ግጭ ቀበሌ ለነበሩ የልማት ተነሽዎች ዘላቂ የሥራ ዕድል መፍጠሩን ገልጿል።
ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ ከ104 በላይ ለሚኾኑ ነዋሪዎች የዘላቂ ኑሮ ማሻሻያ እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራ ተሠርቷል ነው የተባለው።
በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባሕል ተቋም ዩኔስኮ ጥናት መሠረት የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን ለመጠበቅ በፓርኩ አካባቢ የሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ወደ ሌላ አካባቢ የማስፈር ሥራ መሠራት እንዳለበት ታምኖበት ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ የሰፈራ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል።
በዚሁ መርሐ ግብር በስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ክልል ውስጥ አበርጌና ቀበሌ ግጭ አካባቢ ሲኖሩ የነበሩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ወደ ደባርቅ ከተማ የማስፈር ሥራ ተሠርቷል።
የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ማሩ ቢያድግልኝ የፓርኩን ደኅንነት ለመጠበቅ ይረዳ ዘንድ ተገቢውን የካሳ ግምት ክፍያ በመፈጸም ነዋሪዎቹን ከግጭ አካባቢ በማንሳት ወደ ደባርቅ ከተማ የማዘዋዎር ሥራ መሠራቱን አስታውሰዋል።
የተነሽ ነዋሪዎችን ሕይዎት በዘላቂነት ለማሻሻል እና የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ ከደባርቅ ከተማ አሥተዳደር እና ከሌሎች አጋር ተቋማት ጋር በመተባበር የተለያዩ ሥራዎች እየተከናዎኑ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞላልኝ አምሳሉ ለነዋሪዎቹ ለሥራ ዕድል ፈጠራ የሚያገለግል ከአምስት ሄክታር በላይ መሬት በማመቻቸት ወደ ሥራ መገባቱን አንስተዋል።
ከከተማ አሥተዳደሩ ሥራ እና ሥልጠና ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር የሥራ ዕድል ተጠቃሚዎችን በሥነ ልቦና እና በክህሎት የማብቃት ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል።
የአፍሪካን ዋይልድ ላይፍ ፋውንዴሽን የኅብረተሰብ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ከፍተኛ ባለሙያ ለማ ኤፍሬም ከተለያዩ ሀገራት ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በተገኘ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የዘላቂ ኑሮ ማሻሻያ ሥራ መከናዎኑን ተናግረዋል።
ነዋሪዎችን በአንደኛ ዙር ወደ ሥራ የማስገባት ሂደት 37 አባዎራዎችን በሦስት ልዩ ልዩ የሥራ ዘርፎች ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏልም ብለዋል።
በ2017 ዓ.ም በተሠራ የሁለተኛ ዙር ወደ ሥራ የማስገባት ሂደት ከ104 በላይ የሚኾኑ ተጠቃሚዎችን በልዩ ልዩ የሥራ መስኮች በ11 ማኅበራት በማደራጀት ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።
በቀጣይም የተጠቃሚዎችን የሥራ ክህሎት እና ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችሉ የክትትል እና ድጋፍ ሥራዎች እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
የሥራ ዕድሉ ተጠቃሚዎችም በበኩላቸው እየተደረገ ባለው ድጋፍ ደስተኛ መኾናቸውን ገልጸው ድጋፉ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ገልጸዋል።
የዘላቂ ኑሮ ማሻሻያ እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራው ለሁሉም ነዋሪዎች ተደራሽ ሊኾን እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በቀጣይም የተጠቃሚዎችን ቁጥር በማሳደግ የአገልግሎት ተደራሽነቱን ለማስፋት እንደሚሠራ ተመላክቷል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን