ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 04/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ጠላት መጣ መሰል ተንጫጩ ወፎቹ ጀግኖች ይጠሩልን አልዩ አምባዎቹ” ተብሎ የተገጠመላት፣ የበረሃዋ ገነት በመባል የምትታወቀው ውቢቷ አልዩ አምባ ዛሬም በታሪኳ ትዘከራለች።
የአንኮበር ታሪክ ሲነሳ፣ የስምጥ ሸለቆ አካል የኾነችው እና የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ የንግድ ማዕከል የነበረችው አልዩ አምባ ሁሌም ትጠቀሳለች።
በሰሜን ሸዋ ዞን አንኮበር ወረዳ የምትገኘው አልዩ አምባ የተመሠረተችው በ1266 ዓ.ም እንደኾነም ይነገራል ስያሜዋንም ያገኘችው “አልየ” ከተባለ የአካባቢው ነጋዴ እንደኾነ ታሪክ ይነግረናል።
ከአዲስ አበባ 187 ኪሎ ሜትር፣ ከደብረ ብርሃን 57 ኪሎ ሜትር፣ ከአንኮበር ወረዳ ዋና ከተማ ጎረቤላ ደግሞ 15 ኪሎ ሜትር ትርቃለች ይህችው ድንቅ ስፍራ።
አልዩ አምባ ለረዥም ርቀት ንግድ (ሲራራ ንግድ) ምቹ በመኾኗ በወቅቱ እስከ ዘይላ ወደብ ድረስ ተዘርግቶ የነበረው የሲራራ ንግድ ማዕከል በመኾንም አገልግላለች።
በ1834 እና 1835 ዓ.ም በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የኾነው የቀረጥ ውል በአልዩ አምባ ገበያ መሠረት ተፈርሟል።
በአጼ ምኒልክ ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረጥ መሥሪያ ቤት ሲከፈት በአልዩ አምባ የጉምሩክ ጽሕፈት ቤት ሥራውን የጀመረ ሲኾን ከዘይላ ወደብ በኩል ወደ ኢትዮጵያ በሚገቡ የንግድ ዕቃዎች ላይ የቀረጥ ክፍያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጀመረባት ከተማም ነች።
ከ1ሺህ 500 እስከ 1ሺህ 700 የሚጠጉ ግመሎች የሀገር ውስጥ ሸቀጦችን ወደ ውጭ ያጓጉዙባት እንደነበርም ይነገራል።
በአሁኑ ወቅት የአማራ፣ የአፋር እና የአርጎባ ብሔሮች እና ብሔረሰቦች በፍቅር እና በአንድነት የሚኖሩባት ድንቅ ቦታም ናት አልዩ አምባ።
በ19ኛው ክፍለ ዘመን የንግድ ማዕከል በነበረችበት ወቅት አራት መግቢያ እና መውጫ በሮች የነበሯት ይህችው ድንቅ ስፍራ በሮቿም አዋሽ በር (ጨው፣ ሻይና ሌሎች ሸቀጦች ከዘይላ ወደብ የሚገቡበት) እና ጨኖ በር በመባል የሚታወቀው በር ሌላው መግቢያ በር ነው።
ይህችው ድንቅ ስፍራ መውጫ በሮችም ነበሯት ይኸውም አንኮበር በር (ከመሀል ሀገር እስከ ሰሜን ዕቃዎች የሚላኩበት) እና ምንጃር በር (ወደ ደቡብ ሸቀጦች የሚላኩበት) ናቸው።
አልዩ አምባ ከፐርሺያ፣ ከሕንድ እና ከአረብ ሀገሮች የሚመጡ በርካታ የውጭ ዜጎች ይኖሩባት እንደነበርም ጎብኝዎች ጽፈዋል።
ስልክ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ ከእንጦጦ እስከ አልዩ አምባ ድረስ መስመር ተዘርግቶለት ነበር፤ እስካሁንም “ስልክ አምባ” የሚባል ሰፈር መኖሩ የዚሁ ማሳያ ነው።
አሁን ላይም አልዩ አምባ የንግድ እንቅስቃሴ በሰፊው የሚካሄድባት ታሪካዊ ከተማም ናት።
በሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን