የራያዎች የጥበብ እጅ በወጣቶች ላይ ሲገለጥ

    0
    111

    ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ራያዎች
    ‎‎‎”ጥርቅ ጫማ ቦፌ – መለያ ልብሳቸው፣
    የመዋጣ ዱላ አይጠፋም ከእጃቸው” ተብሎ ተዘፍኖላቸዋል።

    ይህንን የሙዚቃ ግጥም በአጭር ቀነጨብኩ እንጅ ስለ ራያዎች አለባበስ ብዙዎች አቀንቅነዋል፤ ብዙ ተገጥሟል። ከልጃገረዶቹ የሶለል ድምቀት እስከ እረኞቹ የጓዳና ውሎ ድረስ በራያዎች ዘንድ የሚዘወተሩ ድንቅ ባሕላዊ አለባበሶች እና አጊያጊያጦች አሉ። በመግቢያው ላይ የጠቀስኩትን ስንኝ ዜማ የሰማ ሰው የራያ ወጣት ወንዶች ባሕላዊ አለባበስ እንደምን ያለ ይኾን ብሎ መጠየቁ አይቀርም።

    ከአንድ በስልክ ብቻ የማውቀው ባሕሉን አክባሪ እና ጠባቂ የራያ ወጣት ጋር ተቀጣጥረናል። ወጣት ሽመልስ ወርቁ ይባላል። የራያ ወጣት ወንዶች ባሕላዊ አለባበስ እና አጊያጊያጥ ምን እንደሚመሥል ከራሱ በመነሳት ይነግረናል።

    ወደተቀጣጠርንበት አካባቢ ስደርስ ነጣ ያለ ከሸማ የተሠራ ልብስ ከላይ እስከ ታች ለብሷል። ወገቡ ላይ ነጭ ነገር በብዙ ዙር ጠምጥሟል፤ በረጅም ወገቡ ላይ አምሮ በተጠመጠመው ነጭ ነገር ውስጥ በቆዳ የተለጎመ ጩቤ ስጎበታል።

    ከወገቡ በታች አሸርጧል፤ ከላይ ጋቢ የመሰለ ነገር አገልድሟል። ሶሉ ሳሳ ያለ እና የተጠላለፈ ነጠላ ጫማ ተጫምቷል። ወጣቱ እግሮቹን አጣምሮ በመቆም ወዝ የጠገበ ዱላ በብብቱ እና በመሬት መካከል ወድሮ ተደግፏል። ጸጉሩ በደንብም ባይኾን በመጠኑ ተበጥሯል።

    ወጣት ሽመልስ በራያ ባሕላዊ አለባበስ ደምቆ ስለጠበቀኝ ደስ ብሎኛል። እንዳገኘሁት ይህንኑ ገልጥኩለት። እርሱም ከታች ወደ ላይ ማስረዳት ጀመረ። ጫማው ጥርቅ ጫማ ይባላል። የአካባቢው ማኅበረሰብ በራሱ የእጅ ጥበብ የሚሠራው ነው። ብዙ ጊዜ ከፍየል ቆዳ ይሠራል። በሶል ቅርጽ የተቆረጠ እስከ 12 የፍየል ቆዳ ድርብርብ ለአንድ ጫማ እንደሚያስፈልግ ነግሮኛል። ምናልባትም ዓለም ስለጫማ ማሰብ ሳይጀምር የራያ ሰው ግን የራሱን ጫማ በራሱ እጆች እየሠራ ይለብስ የነበረ ቀደምት ጥበበኛ ስለመኾኑም ወጣቱ አጫወተኝ።

    ከወገቡ ግርጌ ያሸረጠው ነገር “ጎንቢሶ” ይባላል። ቀለሙ በጥቁር እና በነጭ መካከል ያለ በውል የማይታወቅ ነው። “የክረምት ደመና” የመሰለ ነው ይላል ወጣቱ። ጎንቢሶ ከሸማ የሚሠራ ነው። ከታች በጠርዙ ላይ አንድ ጣት በሚያስጥል ስፋት ብቻ ጠቆር ባለ ጥለት ይደመደማል። ትክክለኛውም ይህ ነው።

    ከታች የተለያየ ቀለም ባለው ሰፊ ጥለት የሚጠለፈው ጎንቢሶ የራያን ጥንተ ባሕል የማይገልጽ፣ ይልቁንም ብልጭልጭ ነገር ፈላጊነት የወለደው አዲስ አለባበስ ነው ብሎኛል ወጣቱ። “ጎንቢሶ” ሲሸረጥ እስከቁርጭምጭሚት አይረዝምም፤ እስከጉልበትም አያጥርም። ትክክለኛው አለባበስ የታችኛው ጠርዝ ባትን ሸፈን አድርጎ ሲያርፍ ነው።

    አንዳንዴ የጎንቢሶው የታችኛው ባለጥለት ጠርዝ ከወደወገብ በኩል ተገልብጦ ይለበሳል አለኝ ወጣቱ። ይህ አለባበስ ጉልበተኛ እና አልሸነፍም ባይ ወጣቶች የሚለብሱት ነው። እንዲህ የለበሱ ሁለት ወጣቶች ቢገናኙ ትግል ለመግጠም ይፈላለጋሉ። ጉልበት እና ሥልትን የሚጠይቀውና ባሕላዊ የትግል ጨዋታ ይገጥሙና አሸናፊው የጎንቢሶውን የታች ጠርዝ ወደወገቡ አዙሮ በክብር መልበሱን ይቀጥላል። የተሸነፈው ግን ጎንቢሶውን እዚያው ላይ አውልቆ በመደበኛ መልኩ ይለብሰዋል።

    “ላም የከረመበት ያበቅላል እምቧይ፣
    ቤቱን የወደደ ይኾናል አገልጋይ” እንዲሉ ራያዎች “ነገር በቃኝ፣ ምንም አይነት ጥል አልፈልግም፤ መሸምገል ፈልጌያለሁ ያለ ወጣት ጎንቢሶውን በወጉ ለብሶ ከላይ ባላ ያለው ዘንግ ይይዛል። ይህ አለባበስ ወጣቱ ጭምት እና በአስተዋይነት የዕድሜ ክልል ውስጥ ስለመግባቱ ያሳብቃል ብሎኛል።

    ወጣት ሽመልስ በወገቡ ዙሪያ ነጭ ሸማ ጠምጥሟል። “ድግ” ይባላል፤ 40 ክንድ ይረዝማል አለኝ። 20 ሜትር ማለቱ ነው። እንዴት ወገቡ ቻለው የሚለው ጥያቄ ያናውዘኝ ጀመር።

    “ጉተናየን በላም ቅቤ አሳድጌ፣
    ቀጭን ድጌን በረዥሙ አደግድጌ” የሚለው የራያዎች ስንኝ ድንገት ትዝ አለኝና “ድጉ” ርዝመት ይኑረው እንጅ ቀጭን ነው የሚል መልስ ሰጠኝ። ሽመልስ እንዳለው “ድግ” ሢሠራ እንደለባሹ ቁመት የሚወሰን ሲኾን በዚህ መሠረትም ርዝመቱ ከ22 ክንድ እስከ 40 ክንድ ይረዝማል። ይህ ነጭ፣ ቀጭን እና ረዥም “ድግ” ለራያዎች ብዙ ጥቅም አለው። አንድም ለግላጋ ወገባቸው ቀጥ ብሎ ቅርጹን እንዲጠብቅ፣ ሁለትም ሰዎች ችግር በሚገጥማቸው ወቅት በቃሬዛ አስሮ ወደሕክምና ለማድረስ ያገለግላል አለኝ።

    ወጣት ሽመልስ ይህንን እያወራኝ በሰፊው ትክሻው ላይ አጣፍቶ የለበሰው እንደጋቢ ያለ አልባስ ዐይኔን ያዘው። ይህ የራያዎች ባሕላዊ ልብስ እርቦ ይባላል። ልክ እንደ “ድጉ” የክረምት ደመና የመሰለ ቀለም ነው ያለው። ልክ እንደጋቢ ተጣፍቶ ይለበሳል። አንዳንዴም ተጠቅልሎ ከትክሻ ላይ ጣል ይደረግና ከብብት ግርጌ ሸብ ተደርጎ ይታሠራል።

    “ላሊበላ በታች ስሙነው ሽምሸሀ፣
    ከቦፌም አለወይ ሀብታም እና ደሀ፣
    አንደኛው ቂቤ ነው አንደኛው ግን ውኃ” ይላሉ ራያዎች ጎንቢሶ እና እርቦ የተባሉት ከቦፌ የተሠሩ ባሕላዊ ልብሶች በአሽኩቲ እና ናትራ መአዛ በሚያውድ ቂቤ ወዝተው ነው የሚለበሱት። በቂቤ የወዛ “ጎንቢሶ” እና “እርቦ” መልበስ የሃብታምነት ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል።

    ወጣት ሽመልስ ካሸረጠው “ጎንቢሶ”፣ በትክሻው ላይ አጣፍቶ ከለበሰው “እርቦ” እና በወገቡ ላይ አጥብቆ ከጠመጠመው “ድግ” በተጨማሪ ነጭ በትር በቀኝ እጁ ይዞ መሬቱን ወጋ እያደረገ ነው የሚጓዘው። ይህ በትር “መዋጣ” ከተባለ የአካባቢው ዕጽዋት የሚዘጋጅ ነው። እንጨቱ ተቆርጦ በእሳት ይለበለብና ቅርፊቱ ተልጦ ይለሰለሳል። በልክ ተቆርጦ ከባሕላዊ አልባሳት ጋር ይያያዛል። የራያ ባሕላዊ ልብስ ለብሶ “መዋጣ” ዱላ አለመያዝ ጎዶሎ ጌጥ ነው ያለው።

    ወጣት ሽመልስ ከግራ እጁ ክርን ወደ ብብቱ ከፍ ብሎ ከቆዳ የተሠራ እና ዛጎል የተሰካበት ነገር አጥልቋል። “ጨኸቲ” እንደሚባል ነግሮኝ ይህም የልጅነት ጊዜያቸውን አልፈው የጎረመሱ የራያ ወጣቶች “ለአካለ መጠን” ስለመድረሳቸው እንደጠቋሚ ምልክት የሚያስሩት ጌጥ ስለመኾኑ አብራርቶልኛል። ጨኸቲ “ሰሳ” ከተባለች የዱር እንስሳት ቆዳ ተተልትሎ ገመድ በመሰለው ቆዳ ላይ በተሰካካ ጨሌ ወይም ዛጎል ይሠራል።

    “ጨኸቲ” መልበስ በራያዎች ዘንድ “አንበሳ ገዳይ” ተብሎ የሚነገርለት እና የጀግንነት ምልክትም ኾኖ ያገለግላል። “ጨኸቲ” የለበሰ ወጣት ዕድሜው ወደ ሽምግልና አየገፋ ሲሄድ “ጨኸቲውን” ያወልቃል።

    “መዋጣየን ሙሌ ጎመጅ የቆረጥኩኝ፤
    ሀገር ስትቆም የሀገር ማገር ያቀበልኩኝ” ይላሉ ራያዎች ስለ “መዋጣ” ዱላ እና ስለሀገር ባለውለታነታቸው ሲያወሱ። “መዋጣ” ዱላ አንዱ የራያዎች ማጌጫ ሲኾን በብዛት “ጎመጅ” በተባለ አካባቢ ከሚበቅል “መዋጣ” የሚባል ዛፍ የሚዘጋጅ ነው። ዱላው ቀጥ ብሎ የበቀለ “መዋጣ” ዛፍ ተቆርጦ በእሳት ይለበለባል። ልጡ ይላጥና እንደየ ሰዎች ቁመት ተለክቶ በመቆረጥ ይዘጋጃል። የባሕል ልብስ የለበሰ የራያ ሰው የግዴታ “መዋጣ” ዱላ መያዝ ይጠበቅበታል።

    ይህ ሁሉ የራያ ወጣት ወንዶች ባሕላዊ አለባበስ ተጠብቆ እንዲዘልቅ ወጣቱ የማስተዋወቅ ሥራ እያከናወነ ስለመኾኑም ነግሮናል። በየበዓላት አልባሳቱን በማስተዋወቅ በስፋት እንዲለበሱ እያደረጉም ነው። አንዱ የቱሪዝም ስበት ኾኖ እያገለገለ እና ኢኮኖሚ እያመነጨ መኾኑንም ወጣት ሽመልስ ገልጾልኛል። ሙሉ የኾነው የራያ ወጣት ወንዶች አልባስ ማለትም ጥርቅ ጫማ፣ ጎንቢሶ፣ እርቦ፣ ድግ፣ መዋጣ ዱላ፣ እስከ 14 ሺህ ብር ያወጣል።

    በአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የባሕል ዕሴቶች ልማት ባለሙያ ነህምያ አቤ እንዳሉት እነዚህን የራያ አልባሳት ጨምሮ ሌሎችም የክልሉ ሕዝብ ባሕላዊ አልባሳት ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ እየተሠራ ነው። የአልባሳቱ ባሕላዊ የአሠራር ይዘት እና የአለባበስ ሥርዓት እንዳይበረዝ ከዞን እና ወረዳ የቱሪዝም ተቋማት ጋር በመተባበር እየተሠራ ስለመኾኑም አብራርተዋል።

    ባሕላዊ አልባሳት እና ቁሳቁሶች እየተመዘገቡ ነው፤ የተለያዩ ምሁራንም የባሕል እና እሴት ጥናት እና ምርምር ሥራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ። ባለሙያው እንዳሉት እነዚህ ባሕላዊ አልባሳት በስፋት እንዲለበሱ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸውም እንዲያድግ በብዛት ማምረት ያስፈልጋል። አልባሳትን ከሚያመርቱ ድርጅቶች እና ተቋማት ጋር ውል ተይዞ እየተሠራ ስለመኾኑም ጠቁመዋል።

    ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው

    የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

    https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

    ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

    LEAVE A REPLY

    Please enter your comment!
    Please enter your name here