መድመቀስ በራስ!

    0
    73

    ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 07/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ባሕላዊ አልባሳት ከበዓላት ቀን ውጭ በተለያዩ የዕለት ተዕለት ተግባራት ላይ ተዘውትረው ቢለበሱ የብዙ ሰው ፍላጎት ነው።

    ታዲያ የሀገር ልብሶች ምን ያህል ምቹ፣ ቀላል እና ሳቢ ናቸው?

    ለ35 ዓመታት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያገለገሉት ወይዘሮ ፈለጉሽ ገነት ከሥራ ጊዜያቸው 25 ዓመቱን የሀበሻ ቀሚስ በመልበስ ማሳለፋቸውን ይናገራሉ።

    አንዳንድ ሰዎች የሀበሻ ቀሚስ ለሥራ ምቹ አይደለም የሚል አስተያየት ቢኖራቸውም ወይዘሮ ፈለጉሽ በሥራ ቦታ የሀበሻ ቀሚስ መልበስ ምቾት እንደሰጣቸው እና ደስተኛ እንደሚያደርጋቸው ነው የነገሩን።

    “ቀሚስ ስለለበስኩ ቢሮዬ ቁጭ ብዬ አልውልም፤ እንደማንኛውም ሠራተኛ ወዲያ ወዲህ እየተንቀሳቀስኩ እሠራለሁ” በማለት ለሥራ ምቾት የለውም ለሚለው የብዙዎች ሃሳብ ምላሽ ሰጥተዋል።

    ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ለፋሽን ዲዛይን ከፍተኛ ፍላጎት እንደነበራቸው የሚናገሩት ወይዘሮ ሒሩት ታዬ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፋሽን ዲዛይን ትምህርት ክፍል በዲግሪ እና በማስተርስ ተምረው በከፍተኛ ማዕረግ ተመርቀዋል።

    ከምረቃ በኋላም በባሕር ዳር ከተማ የባሕል አልባሳት ፋሽን ዲዛይን ሥራ ላይ ተሰማርተው እየሠሩ ይገኛሉ። ይህ ሥራ ሰፊ የሥራ ዕድል እንደፈጠረላቸው እና ለሰባት ወጣቶችም ሥራ መፍጠር እንደቻሉ ወይዘሮ ሒሩት ይናገራሉ።

    “የባሕል አልባሳት በተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ እየተለመደ መምጣቱ በዘርፉ አዳዲስ ሥራዎች እንድንሠራ እና ገበያውም እንዲሰፋ አድርጎታል” ሲሉ አክለዋል።

    አልባሳቱ ሙሉ በሙሉ ከጥጥ የተሠሩ፣ ጠንካራ እና ለሥራ ምቹ እንዲኾኑ ዲዛይን ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

    የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፋሽን ዲዛይን ትምህርት ክፍል የኢትዮጵያ ባሕላዊ ልብሶችን ዘመናዊ በማድረግ በገበያ ላይ ተወዳዳሪ እንዲኾኑ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑን የትምህርት ክፍሉ ኀላፊ አሸናፊ ተክላይ ተናግረዋል።

    ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን ባሕላዊ አልባሳትን ለሥራ ምቹ፣ ቀላል፣ ዘመናዊ እና ማራኪ በማድረግ በገበያ ላይ ተወዳዳሪ እንዲኾኑ በማስተማር እና በማሠልጠን የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ ነው።

    የሀገር ልብስ አልባሳት ከበዓላት ቀን ውጭ በየጊዜው እንዲለበሱ ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው ከባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመኾን ፌስቲቫሎችን እና የፋሽን ትርኢቶችን በማዘጋጀት የማስተዋወቅ ሥራ እየሠራ ነው።

    በዩኒቨርሲቲው ግቢም “የባሕል አርብ ቀን” በሚል ሠራተኞች አርብ አርብ የባሕል አልባሳት እንዲለብሱ እና በማኅበረሰቡ ዘንድ እንዲለመዱ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነውም ይላሉ።

    አቶ አሸናፊ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሀገር ባሕል ልብሶቻችን በመልበስ የራሱን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

    የሀገር አልባሳትን መልበስ የራሳችንን ባሕል ማስተዋወቅ እና ተፈላጊነቱን ማሳደግ ብቻ ሳይኾን ውስጣዊ እርካታንም እንደሚያስገኝ አጽንኦት ሰጥተዋል።

    ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ

    የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

    https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
    ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

    LEAVE A REPLY

    Please enter your comment!
    Please enter your name here