ሰቆጣ: ሐምሌ 05/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሻደይ በዋግ ኽምራ ልዩ ትርጉም ያለው የልጃገረዶች ጨዋታ ነው። ሻደይ ከነሃሴ 16 እስከ 21 ድረስ በየዓመቱ በልዩ ልዩ የባሕል አልባሳትና ጌጣጌጦች የተዋቡ ልጃገረዶች በድምቀት የሚያከብሩት በዓል ነው።
በመኾኑም የሻደይን በዓል በልዩ ኹኔታ ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጀመሩን የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ካሳ ከበደ ገልጸዋል።
የሻደይ ባሕላዊ ጨዋታ ከኦሪት ጀምሮ ሲከበር እንደመጣ ይነገራል። በዓሉን በዞን ደረጃ ከ20ዐዐ ዓ.ም ጀምሮ በሰቆጣ ከተማ ከየወረዳው የተውጣጡ ልጃገረዶች የሚያከብሩት በዓል እንደኾነ ኀላፊው ተናግረዋል።
ሰቆጣ ከተማም በዓሉን በድምቀት ለማክበር ከወጣቱ፣ ከነጋዴው ማኅበረሰብ እና ከአመራሩ ጋር የጋራ ሥራ መጀመራቸውንም ጠቁመዋል።
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ባሕልና ቱሪዝም መሥሪያ ኃላፊ ኢዮብ ዘውዴ የሻደይ ባሕላዊ ጨዋታ በታዳጊዎች፣ በአዋቂ ልጃገረዶች እና በእናቶች ተከፍሎ የሚከበርና የዋግ ሕዝብ ልዩ መገለጫ ነው።
ወጣቶችም የሰቆጣ ከተማን ለእንግዶች ምቹ እንድትኾን ለማድረግ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በእቅድ በማካተት ወደ ተግባር ተገብቷል። በአካባቢው ያለውን ሰላም በማጽናት ለእንግዶች የተመቼ ከባቢ ለመፍጠር በጋራ መሥራት ይገባል ነው ያሉት አቶ ኢዮብ።
ሻደይን ከነሃሴ 01 ጀምረው ልጃገረዶች አልባሳት በማሟላት፣ እንሶስላ በመሞቅ እና ሻደይ በመንቀል፣ ባሕላዊ ጨዋታዎችንም በቡድን መለማመድ ይጀምራሉ።
መምሪያ ኀላፊው እንዳሉት እንደ ዞን በዓሉን በድምቀት ለማክበር ኮሚቴ በማዋቀር እና ተልዕኮ በመሥጠት ወደ ሥራ ተገብቷል።
ወጣቶችም የአካባቢውን ሰላም ከመጠበቅ ባሻገር ውብና ጽዱ ከተማን ለመፍጠር በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ዘጋቢ:- ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!