ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 09/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዳጋ እስጢፋኖስ የወንዶች አንድነት ገዳም በአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞን ባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ በጣና ሐይቅ የሚገኝ ገዳም ነው።
ከባሕር ዳር ከተማ በስተሰሜን አቅጣጫ 44 ኪሎ ሜትር ርቀት በአማካኝ ከሦስት ሰዓት የጀልባ ጉዞ በኋላ ይገኛል።
ገዳሙ በጣና ሐይቅ ውስጥ ከተገደሙ ገዳማት መካከል የመጀመሪያው ነው። በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአፄ ይኩኑ አምላክ ዘመነ መንግሥት አቡነ ሂሩተ አምላክ በተባሉ አባት እንደተመሠረተ ከአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የተገኘ መረጃ ያስረዳል፡፡
የኪነ ሕንጻ ጥበብ እና ፍልስፍና ያረፈበት ታሪካዊው የዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም ገዳሙን በገደሙት ጻድቁ አቡነ ሂሩተ አምላክ ከሐይቅ ገዳም በመነሳት የእስጢፋኖስ ታቦተ ጽላት በመያዝ በድንጋይ ታንኳ ጣናን በመስቀላቸው እየቀዘፉ ወደ ዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም የገቡበትን ታንኳ ቅርፅ ይዞ እንደተሠራ ይነገራል፡፡
ዳጋን ከመካከለኛው ዘመን አንሥቶ ነገሥታቱ፣ መኳንንቱ፣ ጳጳሳቱ እና ምዕመኑ የሀገሪቱ ታሪክ ባለ አደራ አድርገውታል፡፡ በሀገሪቱ የደረሱ የእርስ በእርስ ጦርነቶች እና ወረራዎች ወደ ገዳሙ ባለመዝለቃቸውም ከ800 ዓመታት በላይ የተጠበቁ ቅርሶችን አቅፎ ይዟል፡፡
በዳጋ እስጢፋኖስ ከአፄ ይኩኑ አምላክ እስከ ቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ድረስ የነበሩ አራት ነገሥታት ማለትም አጼ ዳዊት (1382-1430)፣ አጼ ዘርዓ ያዕቆብ (1334-1468)፣ አጼ ፋሲል (1632-1667)፣ የአጼ ወድንግል (1603-1604)፣ የአጼ ሱስንዮስ (1606-1632) ዐጽሞች ዛሬም በክብር ይገኛል፡፡
የመስቀሉን ክፋይ ጨምሮ አያሌ ንዋየተ ቅድሳት፣ የነገሥታት መገልገያ ዕቃዎች፣ ካባዎች እና አክሊሎች፣ የገዳሙ መስራች አቡነ ሂሩተ ወደ ገዳሙ የመጡበት የድንጋይ ታንኳ እና በርካታ የብራና መጻሕፍት ይገኛሉ፡፡
ገዳሙ በታሪክ እና ቅርስ ማኅደርነቱ እንዲኹም ዓመቱን በሙሉ ልምላሜ በማይለየው ጥቅጥቅ ደን የተሸፈነ በመኾኑ በቱሪስቶች ከፍተኛ አድናቆትን ያተረፈ ገዳም ነው።
ከካህናቱ ጸሎት፣ ከአዕዋፋቱ ዝማሬ፣ ከእድሜ ጠገብ ዛፎች የእርስ በእርስ ቁርኝት፣ ከጣና ውኃ መገማሸር ያለፈ ድምጽ የሚፈልግ አይመስልም፡፡ ይህን ተከትሎም አንዳንዶች ዝምተኛው ገዳም በሚል ቅፅል ስም ይጠሩታል።
እሱ ባይቀሰቅስም በዝምታው መንፈስን የሚያድስ ሰማያዊ የኾነ መንፈሳዊ የሥነ ልቦና ሐኪምነቱ ተገደው እና በፍቅሩ ተማርከው የሚሄዱበትን ወዳጆቹን ግን ደጁን አልከለከላቸውም ቀጣይም አይከለክላቸውም፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ዳጋ ደጁ ጭር ብሏል። ዝምታውን ሰብሮ ጠያቂ ወዳጆቹን ኑልኝ የሚል ይመስላል ይላሉ ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ ገዳሙን በተደጋጋሚ የጎበኙት የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ዘማሪ አብርሃም ድረስ።
እስከ 2010 ዓ.ም አካባቢ ዳጋ ብዙ ጎብኝ ነበረው፡፡ በተለይ ነጮች በጣም ይጎበኙት ነበር፡፡ ከዛ በኋላ ግን የኮሮና ቫይረስ ሲከሰት በኋላም በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት እና አማራ ክልል ላይ በተፈጠረው ወቅታዊ ጉዳይ ምክንያት ጎብኝዎች እየጎበኙት አይደለም፡፡ የሀገር ውስጥ ጎብኝዎችም እየሄዱ አይደለም፡፡
እኔ እስከማውቀው ድረስ የበፊቱ እና የአሁኑ ጎብኝ ቁጥር አይገናኝም፡፡ ወደ ባሕር ዳር የመጣ ማንኛውም ሰው ገዳሙን መጎብኘት ቢፈልግ ቦታው ላይ ያለው አኹናዊ ኹኔታ ሰላማዊ ነው። ገዳሙ ያለበትን ኹኔታ እና ታሪካዊነት የማስተዋወቅ ሥራ ግን ያስፈልጋል ሲሉ ትዝብታቸውን ለአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ አጋርተዋል።
ሌላኛው የዳጋ እስጢፋኖስ የወንዶች አንድነት ገዳምን በተደጋጋሚ የጎበኙት ወልደ ተክለሃይማኖት አብርሃም ደግሞ ቀደም ባሉት ጊዜያት ዳጋ እስጢፋኖስ ገዳምን በተደጋጋሚ ጎብኝቻለሁ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ወደ ገዳሙ ሄጄ አላውቅም፡፡ የሰላሙ ኹኔታ ለጉብኝት ምቹ አይደለም፡፡ ሰዎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ልዩ ልዩ ተግባሮቻቸውን የሚያከናውኑበት ኹኔታ ላይ አይደለንም አሉን።
እንኳንስ የውጭ ሀገር ጎብኝ የሀገር ውስጥ ጎብኝም እየሄደ አይደለም፡፡ ይህ መኾኑ ደግሞ እንደ ሀገርም ኾነ እንደ ክልል ጉዳት ይኖረዋል፡፡
ሰላም ሲኖር ጎብኝዎች ብቻ ሳይኾኑ ከትናንሽ የንግድ ተቋማት ጀምሮ እስከ ትላልቅ የንግድ ተቋማት ተጠቃሚ መኾን ይችላሉ። ስለዚህ ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነውና ለሰላም መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
የገዳሙ ልዩ ልዩ ሥራዎች ጉዳይ አስፈጻሚ አባ ሐብተማርያም ዮሐንስ በዳጋ እስጢፋኖስ ዓለምን ንቀው ፈጣሪያቸውን እያመሰገኑ የሚኖሩ ከ180 በላይ ወንድ መነኩሳት ይገኛሉ።
አባቶች ስለ ሰው ልጆች እና ስለሀገር ሰላም በጾምና በጸሎት ከመለመን ባሻገር በገዳሙ የተለያዩ የእደ ጥበብ (የሸማ ሥራ) እና የመስኖ ልማት (ብርቱካን፣ ሸንኮራ አገዳና ሌሎች ፍራፍሬ) ሥራዎችን ይሠራሉ ብለዋል።
እነዚህ የልማት እና የእደ ጥበብ ሥራዎችን ወደ ባሕር ዳር ከተማ በማምጣት ለነጋዴዎች ያስረክባሉ እንጂ ወደ ገዳሙ የሚመጣ ጎብኝ ስለቀነሰ በገዳሙ አካባቢ መሸጥ የሚቻልበት ኹኔታ የለም ነው ያሉት።
ክልሉ ላይ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያትም ጎብኝ የለም። ገዳሙ ራቅ ያለ ከመኾኑ የተነሳ ጎብኝዎች ስጋት ስላለባቸው በቅርብ ወደ ሚገኙ ተቋማት ነው የሚሄዱ። አልፎ አልፎ የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ይመጣሉ ሲሉ አባ ሐብተማርያም ተናግረዋል።
በተለይም ደግሞ መንግሥት ሠራተኞች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች እና የሰንበት ት/ቤት አገልጋዮች ናቸው የሚመጡት። አኹን ላይ የገዳሙን ትውፊት ጠብቆ በገዳሙ እየተገነባ የሚገኘው ትልቅ ሙዚየም በመጠናቀቅ ላይ ነውም ብለዋል።
በክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ አማካኝነት የገዳሙ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች እና ሌሎችም ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው።
የገዳሙ ቅርሶችም ደኅንነታቸው ተጠብቆ ከ300 ዓመት በላይ ሲያገለግል በቆየው ነባር ሙዚየም ደኅንነታቸው ተጠብቆ ይገኛል።
ገዳሙ እንደቀደመው ጊዜ ጎብኝዎች እንዲጎበኙት ግን የአካባቢው ሰላም አስፈላጊ ነው፣ እግዚአብሔር የሀገሪቱን ሰላም እንዲያስተካክልልን በጸሎት እየጠየቅን ነው ያሉት።
መልካሙ አዳም የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር ናቸው። አማራ ክልል ላይ ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰት የሚኖርበት ወቅት ከመስከረም እስከ የካቲት ወር ድረስ ነው ይላሉ።
ዳይሬክተሩ ከመጋቢት ወር በኋላ ግን የቱሪስት ፍሰቱ የሚቀንስበት ጊዜ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ባለው የክልሉ ቱሪዝም ፍሰት ልምድ መሰረት እየሄደ እንዳለ የሚያስረዳ ነው ብለዋል። ነገር ግን አሁን ላይ ቱሪስት የለም እና አለ ማለት አይቻልም፡፡ በጥናትና ምርምር ማረጋገጥ ያስፈልጋልም ነው ያሉት።
በዳጋ እስጢፋኖስ በፌደራል መንግሥት አስተባባሪነት፣ በክልሉ መንግሥት ድጎማ እና በማኅበረሰብ ተሳትፎ የገዳሙን የቀደመ ትውፊት ጠብቆ ሙዚየም እየተገነባ ነው ብለዋል።
የማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ይገኛል። በቅርቡ ይመረቃል፤ በውላችን መሰረት እስከ መጪው የኅዳር ወር መጨረሻ ያልቃል ነው ያሉት፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞም የጉብኝት ትስስር የሚፈጥሩ የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን ሠርተን አብረን ለማስመረቅ እየሠራን ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ በዚህ በጀት ዓመት በእቅድ ተይዞ እየተሠራ ያለ ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የዳጋ እስጢፋኖስ የጉብኝት ማዕከል እና ወደ ገዳሙ ለሚመጡ ቱሪስቶች ማረፊያ ክፍሎች፣ ሻወር እና መጸዳጃ ቤቶች ግንባታ በጨረታ ለኮንትራክተሮች ሠጥተን ሥራው ተጀምሯል ብለዋል፡፡
ደጋ እስጢፋኖስ በአኹኑ ሰዓት ከፀጥታ ችግር ስጋት ነጻ ኾኖ የክረምቱን ቅዝቃዜ መርሻ እና ዝምታውን የሚሰብሩ ታሪክ ነጋሪ ጎብኝዎችን ይሻል።
ለዚህ ደግሞ በጎብኝዎች አማካኝነት ተጠቃሚ የሚኾኑ የአካባቢው ማኅበረሰብ እና የመንግሥት አሥተዳደር አካላትን የጋራ ጥረት ይጠይቃል ነው ያሉት።
ዘጋቢ:-ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!