ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ውጥኑ የተጀመረው በ1995 ዓ.ም ነበር። በወቅቱ የነበሩ አንቱ የተባሉ የሀገሪቱ የኪነ ቅርጽ እጆች፣ አርክቴክቶች እና ሰዓሊያን ለሥራው ውበት እና ዘመን ተሻጋሪነት እጃቸውን እንዲያሳርፉ ታጩ።
እነዚህ የሕንጻው ዓለም ጠቢባን በጀ አሉና ጥሪውን ተቀብለው እንደየመክሊታቸው መትጋት ጀመሩ። በ1994 ዓ.ም ግንባታው ተጀምሮ በ1998 ዓ.ም ተጠናቀቀ።
ይህ የዓባይ ወንዝ ዳር የታሪክ ማማ ሲጀመር ከ1973 እስከ 1983 ዓ.ም ብቻ ያለውን የኢህዴን/ብአዴን ታሪክ ብቻ ቀንብቦ በመሰነድ ለታጋዮች መታሰቢያ ይኾን ዘንድ ነበር።
ስሙም፣ ግብሩ፣ የታሪክ ምዕራፍ አካታችነቱም ውስን የፖለቲካ እሳቤ የተጫነው ኾነ። በመኾኑም ከሕዝቡ ጥያቄዎች እየተነሱበት ትችቶችንም ማስተናገድ ጀመረ።
የሕዝብን ጥያቄ ተቀብሎ እና ውስንነቶቹን አስተካክሎ የክልሉን ባሕል፣ እሴት እና ረጅም ታሪክ የሚሰንድ ሁነኛ የሕዝብ ሃብት ለመኾን ወሰነ።
በ2013 ዓ.ም በጀመረው ተቋማዊ ማሻሻያ ፖለቲካ የተጫነው እና አካታች ያልኾነውን ስሙን በመቀየር “የአማራ ሕዝብ ዝክረ ታሪክ ማዕከል” ተብሎ እንደገና ተደራጀ።
ሕዝቡን የማይወክሉ ኪነ ቅርሶችን እና የሙዚየም አደረጃጀቱንም በሕዝብ አስተያየት መሠረት እና በጥናት ተመስርቶ እንደገና አረመ።
የአማራ ሕዝብ ዝክረ ታሪክ ማዕከል የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ በላይ ስማቸው ማዕከሉ አሁን የአማራ ክልል ሕዝብ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ያበረከተውን አስተዋጽኦ፣ ባሕሉን፣ እሴቱን እና ጉልህ ታሪኩን ሰንዶ ለትውልድ ለማስተላለፍ የሚሠራ የታሪክ ማማ ነው።
ማዕከሉ የሕዝቡን ጥንታዊ፣ መካከለኛ እና የዘመናዊ ዘመን ታሪክ በማደራጀት እና በማስረጽ ታሪኩን የሚያውቅ፣ በቀደመ ታሪኩ የሚኮራ እና አዳዲስ ታሪኮችንም የሚሠራ ትውልድ ይፈጠር ዘንድ አቅዶ የሚሠራ ስለመኾኑም አቶ በላይ ተናግረዋል።
ለታሪክ ምርምሮች የመረጃ ምንጭ ኾኖ ያግዛል፣ በተንጣለለው የቤተ መጻሕፍት አገልግሎቱም የንባብ እና የዕውቀት ምንጭ ኾኗል፣ በውብ ምድረ ግቢው ሰርግ እና መሠል የተለያዩ ኹነቶችን ለማዘጋጀት የከተማው ነዋሪዎች ይጠቀሙበታል ብለዋል ኀላፊው።
ዝክረ ታሪክ ማዕከሉ የተደራጀ ሙዚየም ያለው ነው። ሁሉንም የታሪክ አንጓዎች የሚነግር የኪነ ሕንጻ እና ኪነ ቅርስ፣ የዕውቅ ሰዓሊያን እጅ የተፈተነበት የሥዕል ጋለሪ፣ በየዘመኑ ለክልሉ ሕዝብ እና ለሀገርም ረብ ያለው ሥራ በመሥራት እንደ ዕንቁ ያበሩ ጀግኖች ታሪክ እና ምስል፣ እንደነ እትጌ ጣይቱ እና አምሳለ ጓሉ አይነት ሀገርን በብልሃት ሲያሻግሩ እና አይቻልም የተባለውን በመቻል ያሳዩ ተምሳሌት ሴቶችንም የሚዘክር ነው ሙዚየሙ።
ሕዝቡ በየዘመኑ ሲገለገልባቸው የነበሩ ባሕላዊ ቁሳቁሶች፣ ደምቆ የሚታይባቸው የእጁ ውጤት የኾኑ ባሕላዊ አልባሳት በዚሁ ሙዚየም በክብር ተሰንደው ይታያሉ።
ዓለም ገና ስለቴክኖሎጅ ሳያስብ የቀደሙ የክልሉ ሕዝብ የቴክኖሎጅ ጅምሮች፣ ከሀገራትም ቀድሞ ፊደል በመቅረጽ፣ ቀለም በመበጥበጥ እና ዘመን በመቀመር የተተለመ የዕውቀት አሻራ በዚሁ ዝክረ ታሪክ ማዕከል ውስጥ ነፍስ ዘርቶ ይታያል።
ዘመናዊ አንፊ ትያትር፣ መሠብሠቢያ አዳራሽ፣ ከ31 ሺህ በላይ መጻሕፍትን የያዘ ቤተ ንባብ፣ ለተማሪዎች የሚያግዝ የኢንተርኔት አገልግሎት፣ ፋውንቴን እና ሌሎች በርካታ የቱሪዝም አገልግሎቶችንም ይሰጣል ማዕከሉ።
አቶ በላይ ማዕከሉ ከ2013 ዓ.ም የለውጥ ሥራዎቹ ወዲህ በክልሉ ሲቪል ሰርቪስ የሚተዳደር የሕዝብ ተቋም ነው። ከለውጡ በፊት በነበረው የቀደመ አሠራሩ ብቻ በመረዳት ማዕከሉን በፖለቲካ መነጽር ብቻ የሚመለከቱ እና በትችት ብቻ የተጠመዱ ሰዎች አኹንም ድረስ ስለመኖራቸውም አንስተዋል።
“የአማራ ሕዝብ ዝክረ ታሪክ የክልሉ ባሕል፣ እሴት፣ ቋንቋ፣ እና ሌሎችም የቱሪዝም ሃብቶች የተሰነዱበት የሕዝብ ሃብት ነው” መኾኑን ማወቅ ይገባል ብለዋል።
ዝክረ ታሪክ ማዕከሉ በባሕር ዳር ከተማ በታላቁ የዓባይ ወንዝ ዳር በ27 ሺህ 300 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ተንጣልሎ ያረፈ ነው። ይህንን ቦታ የበለጠ በማልማት የክልሉን የቱሪዝም ሃብቶች እንደማስተዋወቂያ እና መጠበቂያነት ከመገልገል ባለፈ ራሱንም አንዱ የጉብኝዎች መዳረሻ ሁነኛ ቦታ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል አቶ በላይ።
የዓባይ ወንዝ ከጣና ሐይቅ ወጥቶ በጎኑ የሚያልፍ ልዩ ቦታ ነው፣ ከወንዙ ጋር የተሰናሰለ የፋውንቴን እና የአረንጓዴ ልማት ሥራ በዘመናዊ መልኩ ለመገንባት የዲዛይን ሥራው ስለመጠናቀቁም ኀላፊው ገልጸዋል።
የታቀደው የልማት ሥራ ከነባሩ የዓባይ ድልድይ ውብ ኾኖ እስከተገነባው አዲሱ ድልድይ ድረስ የሚያስተሳስር ነው ብለዋል።
በአዲስ የተሠራው ዲዛይን በመንግሥት በጀት፣ በባለሃብቶች ቅንጅት እና በልማታዊ ድርጅቶች ተሳትፎ ዕውን እንዲኾንም ታቅዶ እየተሠራ እንጀኾነም ጠቁመዋል።
ሕዝቡም ይህንን ዝክረ ታሪክ ማዕከል በውል በመገንዘብ እና ወደ ቦታው በመግባትም በውስጡ የያዘውን የቱሪዝም ሃብት በመመልከት ታሪክን ማስቀጠል ይገባዋል፤ ማዕከሉ ያቀደውን ተጨማሪ የልማት ሥራም በባለቤትነት መውሰድ እና የበኩልን ድርሻ እንዲወጣም ጥሪ አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን