ከ4 መቶ ዓመታት በላይ አጽማቸው ያልፈረሰ ፍየሎች የሚገኙበት ገዳም።

0
111

ባሕር ዳር: ሐምሌ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ጩጊ ማርያም ወአቡነ ምዕመነ ድንግል አንድነት ገዳም በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ወገራ ወረዳ ጉንዳ ጩጊ ቀበሌ ትገኛለች።

ገዳሟ ከጎንደር ከተማ 37 ኪሎ ሜትር፣ ከወረዳው ዋና ከተማ አምባጊዮርጊስ ምዕራብ አቅጣጫ በ18 ኪሎ ሜትር ርቀት፣ እንዲኹም ከኮሶዬ ከ2 ሰዓት የእግር ጉዞ በኋላ የምትገኝ ገዳም ናት፡፡

ገዳሟ በ1 ሺህ 632 ዓ.ም አባ ምዕመነ ድንግል በተባሉ አባት እንደተመሰረተች ይነገራል፡፡ በወገራ ወረዳ ከሚገኙ ጥንታዊ ገዳማት እና የጎብኝዎች መዳረሻ መካከልም አንዷ ናት፡፡

በወገራ ወረዳ ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ቡድን መሪ እንዳልክ ተቀባ በጩጊ ማርያም አንድነት ገዳም ጥንታዊ የብራና መጻሕፍት፣ ጥንታዊ መስቀሎች እና ሌሎችም ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ቅርሶች የሚገኙባት መኾኑን አስረድተዋል።

በገዳሟ ውስጥ ጥልቀቱ በውል የማይታወቅ፣ ካህናት እና ዲያቆናት ብቻ እየገቡ የሚቀዱት የዋሻ ውስጥ ጸበል ይገኛል ነው ያሉት። “የዋሻ ውስጥ ጸበሉ መፍሰሻ የለውም፤ ልክ እንደኩሬ ኾኖ ጥርት ያለ ነው፤ መጠኑ አይቀንስም፤ አይጨምርም” በማለት የጸበሉን የተለየ ገጽታ ይናገራሉ።

ወድቆ የተነሳ ችብሃ ዛፍ፣ የኢትዮጵያ ካርታ ቅርጽ ያለው ዋሻ፣ ከተራራ መካከል ብርሃን የሚያሳይ ልዩ ቦታና ሌሎችም ጎብኝዎችን የሚያስደንቁ መስህቦች በገዳሟ ይገኛሉ ነው ያሉት።

በገዳሟ ውስጥ ከ4 መቶ ዓመት በላይ የቆዩ አጽማቸው ያልፈረሱ 16 ፍየሎች ይገኛሉ ብለዋል። እነዚህ ፍየሎች በገዳሟ የሚገኘውን የዮርዳኖስ ጸበል (ማይ ዮርዳኖስ) ጠጥተው እንደኾነ ገልጸዋል።

ይህም ጸበሉን የጠጣ አካሉ ሳይፈርስ ለብዙ ዘመን እንዲቆይ ለቦታው የተሰጠ ቃል ኪዳን እንደኾነ የገዳሙን የታሪክ ድርሳናትን ጠቅሰው ያብራራሉ። በቦታውም ላይ የብዙ ቅዱሳን አፅም እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

ሌላው በዚህ አካባቢ ከሚገኙ ሳቢና ማራኪ ተራሮች መካከል ኑር እምባ ተራራ ይገኛል፡፡ ይህም ስያሜውን ያገኘው አፄ ሱስንዮስ አባ ምዕመነ ድንግልን “ይኑሩ አባ” ብለው እንዲቀመጡ አደረጓቸው፤ በዚህም ተራራው ይኑሩ የሚለውን ቃል በመጠቀም ኑሩ አምባ የሚለውን ስያሜ እንዳገኘ ይነገራል፡፡

በተራራው መካከል አባ ምዕመነ ድንግል ከገዳሟ ወደ ዋሻው በሚመጡበት ጊዜ ደክሟቸው በትረ መስቀላቸውን ተደግፈው ከተራራው ስር ሲቆሙ መሀል ላይ እንደተከፈተላቸው ይገለፃል፡፡

ገዳሟ በየዓመቱ ሰኔ 21፣ ጥር 21 እና ጳጉሜ 3 የንግሥ በዓሏ እንደሚከበርም ነው የተናገሩት፡፡ ከነዚህ ውስጥ ሰኔ 21 ቀን ከፍተኛ የኾነ የሀገር ውስጥ ቱሪስት ፍሰት ይገኝበታል፡፡

ጩጊ ማርያም ከታሪካዊና ሃይማኖታዊ መስህቦች በተጨማሪ እጅግ አስደማሚ በኾኑት የኮሶዬና ውናንያ የተራራ ሰንሰለቶች ግርጌ የምትገኝ በመኾኗ አስደናቂ የመልክዓ ምድር ገጽታዎችንም ለማየት ዕድል የምትሰጥ ልዩ ቦታ ናት፡፡

አካባቢው የመሠረተ ልማት ችግር ያለበት መኾኑን ጠቁመዋል። የገዳሟን የቱሪዝም ፀጋ በሚገባ ለማስተዋወቅ እና ጎብኝዎች ወደ አካባቢው እንዲመጡ ለማድረግ የመንገድ ግንባታ እና ሰፊ የማስተዋወቅ ሥራዎችን መሥራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here