ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ)
“ልጅቷ መቃዋ አንገቷ፣
ገንዘብ ጨረሰች በእርባን ለአንገቷ” የሚለው የአዊ ሴቶች የስንኝ ቋጠሮ ስለ ጌጣጌጦቻቸው ያላቸውን ክብር የሚገልጽ ነው።
በአዊ ብሔረሰብ የባሕላዊ ሙዚቃ ድምጻዊት እና የእንጅባራ ከተማ ነዋሪዋ ካሰች አማረ የአዊ ሴቶች በተለያዩ ጌጣጌጦች ተውበው በሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ሁነቶች ላይ ይታያሉ ይላሉ።
ከሚዋቡባቸው ባሕላዊ ጌጣጌጦች መካከል በመጀመሪያ አንገታቸው ላይ በአጭር የሚታሰር የብር መስቀል አንዱ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ተጣጣፊ መስቀል ይሰኛል፡፡
ተጣጣፊዋ መስቀል ከአዊ ሴቶች አንገት ላይ የማትጠፋ ለአለባበስም ቀላል እና ምቹ ስለኾነች ተወዳጅ ናት፡፡ የምትለበሰውም ከብር መስቀል ቀጥሎ ለብቻ በአንገት ላይ ከፍ ብላ እንደኾነ ነው የነገሩን።
ሌላው ማጌጫቸው የብር ቅጥል ነው። የጠገራ ብርን የማተብ ማስገቢያ በማስበሳት በአንገት ላይ የሚደረግ የአዋቂ ሴቶች ጌጥ ነው፡፡
ብር ቅጥል በብሔረሰቡ በዋናነት ለጌጥ ይለበስ እንጂ በወሊድ ሰዓትም ወላዷን ከርኩስ መንፈስ ጠባቂ ተብሎ ስለሚታሰብ የወለደች እናት ወዲያው እንደወለደች ብር ቅጥል በጥርሷ እንድትይዝ እንደሚደረግ ከብሔረሰብ አስተዳደሩ ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡
ድሪ ሌላው መዋቢያቸው ነው። ሁለት አይነት ነው፤ ጉብጉብ ድሪ እና ነጠላ ድሪ እንደሚሰኙም ነግረውናል፡፡
የድሪ አሠራር ቀጫጭን እና ክብ ቅርጽ ያላቸው ከብር የሚሠሩ ናቸው። እነዚህን ትንንሽ ክብ ቅርጽ ሀብል በባለሙያ በማሠራት በሴቶች አንገት የሚለበስ ባሕላዊ የሴቶች ጌጥ ነው፡፡
ርዝመቱም እንደ ሴትዮዋ የመግዛት አቅም እና ፍላጎት ከአንገታቸው እስከ ደረታቸው አለፍ ሲልም እስከ መቀነታቸው የሚደርስ እና ከሁለት ዙር ያላነሰ ኾኖ ከሌሎች የአንገት ጌጣጌጦች ጋር የሚለበስ ነው፡፡ ድሪ እንደ ብዛቱ የሀብት መጠን ማሳያ መኾኑንም ተናግረዋል።
ማርዳ/ጽቢ/ የቀለበት አይነት ቅርጽ ያለው እና በወፍራም ጥለት ተደርጎ ከሌሎች የብር መስቀሎች ጋር የሚጠቀሙበት እንደኾነ ነው የነገሩን፡፡
“ልጅቷ መቃዋ አንገቷ፣
ገንዘብ ጨረሰች በእርባን ለአንገቷ” በማለትም ለጌጦቻቸው ያላቸውን ክብር ለመግለጽ ያዜማሉ የአዊ ሴቶች፡፡
ሴቶች በአንገታቸው ላይ ከሚያደርጓቸው ጌጣጌጦች እርባን አንዱ ነው፡፡ የሚለበሰውም አብዛኛውን ጊዜ በበዓላት እና በሰርግ ነው፡፡ በተለይ ሲዳሩ ለሙሽራዋ ባይገዛላት እንኳን የእናቷን እንደምታደርግ መረጃው ያመላክታል፡፡
የአዊ ሴቶች ጆሮ ላይ የሚያደርጉት ደግሞ ጉትቻ/በአዊኛ ጉትቺ/ ነው፤ ጉትቻውም የአዊ ጥላ ቅርጽ ያለው ነው፡፡ ጉትቻ በአብዛኛው ሴቶች ካገቡ በኋላ የሚያደርጉት ጌጥ መኾኑንም ነግረውናል።
፡፡
አምባር በእጅ ላይ የሚደረግ ጌጥ ነው። ከብር፣ ከመዳብ እና ከነሐስ እንደየሰው አቅም የሚሠራ እና ከሕጻን እስከ አዋቂ ባሉ ሴቶች እጅ ላይ የሚለብስ ጌጥ ነው፡፡
የተለያዩ የአምባር አይነቶች ያሉ ሲኾን ጨንገር አምባር ሰፊ እና በአሠራሩም ከጫፍ እስከ ጫፍ መስመር ያለው ለብሔረሰቡ ሴቶች ቀዳሚው ነው፡፡
ሌሎቹ በቅርጽ እና በሚሠሩበት ቁስ ጽምብል አምባር፣ ባለጉጥ አምባር እና ጥምዝ አምባር ተብለው የሚጠሩ የአምባር አይነቶች አሉ፡፡
ሌላው የአዊ ሴት በሰርጓ ጊዜ የምትለብሰው የእግር ጌጥ አልቦ ይባላል፡፡ አልቦ ሴት ከሙሽርነት በኋላም ከቤት ውጭ ሌላ ቦታ ስትሔድ የምትለብሰው ሲኾን ልጅ ከወለደች በኋላ እንደሚወልቅ ነው የተናገሩት።
ከአዊ ሴቶች እጅ የማትጠፋው የአዊ ጥላ (አዊት ድጋጋ) ናት፡፡ የብሔረሰቡ መለያ ከኾኑት የባሕል መገለጫዎች አንዷ እና የሴቶች መዋቢያ በመኾኗ ከጌጣጌጦች እንደ አንዱ ናት፡፡
ጥላዋ ከቀርቀሃ የምትሠራ ስትኾን የአዊ ወይዛዝርት እራሳቸውን ከፀሐይ እና ከዝናብ ከመከላከል ባሻገር ወደ ተለያዩ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ሲሄዱ ለብሰው የሚዋቡበት የባሕል መገለጫም ነው፡፡
እነዚህ ባሕላዊ ጌጣጌጦች ይዘታቸውን ጠብቀው ለተተኪው ትውልድ እንዲተላለፉ ለማድረግ እየሠሩ መኾኑን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ወለሌ ጌቴ ይናገራሉ፡፡
ጌጣጌጦች የሚሠሩ አካላትም ዕውቀቱን እንዲያሸጋግሩ የአሠራር ጥበቡን ለመሰነድ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ ጌጣጌጦችን ለሚሠሩ ባለሙያዎች ሥልጠና፣ የገበያ ትስስር እና ለማስተዋወቅ ጥረት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን