ባሕር ዳር: ሐምሌ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዙር አምባ አቡነ አረጋዊ ገዳም በደቡብ ጎንደር ዞን ከሚገኙ ጥንታዊ ገዳማት መካከል አንደኛዋ ናት።
ከባሕር ዳር ከተማ በ153 ኪሎ ሜትር፣ ከደብረ ታቦር ከተማ 55 ኪሎ ሜትር፣ ከነፋስ መውጫ ከተማ ደግሞ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ ትገኛለች።
ዙር አምባ ቀጥ ብሎ በቆመ ተራራ ላይ በሚገኝ መጠነኛ አምባ ላይ የተመሠረተች ጥንታዊት ገዳም ናት። በገዳሟ ዙሪያ የቅዱስ ያሬድ ዛፍ፣ የገሊላ አምባ፣ 39 አይነት እፅዋት እና አቡነ ተክለ ሃይማኖት ለ7 ዓመታት የኖሩበት የጸሎት ዋሻ ይገኛሉ።
መጋቢ ብርሃናት ፈንታ አፈወርቅ በገዳሙ የዝማሬ መዋሲት መምህር ናቸው። ከቅዱስ ያሬድ ጀምሮ የዝማሬ መዋሲትን በማስተማር 46ኛው መምህር እንደኾኑ ነግረውናል።
እርሳቸው እንደገለጹት የገዳሟ ግንባታ በ528 ዓ.ም ተጀምሮ በ530 ዓ.ም እንደተጠናቀቀ አስረድተዋል።
በገዳሟ አፄ ገብረ መስቀል ገዳሟን እያሳነፁ፣ አቡነ አረጋዊ ወንጌልን እየሰበኩ 3 ዓመታትን እንደቆዩባት ጠቁመዋል። ቅዱስ ያሬድም የራሱ ድርሰት የኾነውን እና ዝማሬ መዋሲት የተባለውን መዝሙር እያስተማረ ሦስት ዓመታትን በቦታዋ ላይ እንደቆዩ አብራርተዋል፡፡
ዙር አምባ አቡነ አረጋዊ ገዳም በኢትዮጵያ ብቸኛው የዝማሬ መዋሲት ማስመስከሪያ ጉባኤ ቤት እንደኾነች ነው የተናገሩት። በዚህም ምክንያት መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ እየተባለች ትጠራለች።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዝማሬ የሚማር ተማሪ ብቁነቱ ተፈትኖ የብቃት ማረጋገጫ የሚሰጠው በዚህች ገዳም ብቻ እንደኾነም ነው የተናገሩት፡፡
እንደ መዋሲት መምህሩ ማብራሪያ ማንኛውም ተማሪ ሲመጣ 8 ጥያቄዎችን ተፈትኖ አራቱን ከመለሰ ወደ ጉባኤ ቤቱ ገብቶ እንዲማር ይፈቀድለታል፤ ካላለፈ ግን ሌላ ጊዜ አጥንቶ እንዲመለስ ይደረጋል ነው ያሉት።
የአብነት ትምህርት ቤቱ በአኹኑ ወቅትም 60 ተማሪዎችን እያስተማረ እንደኾነ ተናግረዋል።
በአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የቅርስ ምዝገባ ባለሙያ ሰለሞን ካሰው በገዳሙ ውስጥ በርካታ በቅርስነት ተመዝግበው የሚገኙ ቅርሶች መኖራቸውን ገልጸዋል።
ለአብነትም ጥንታዊ የብራና መጻሕፍት፣ የግድግዳ ላይ ሥዕላት፣ ልዩ ልዩ ንዋያተ ቅድሳት እና ከቀደምት ነገሥታት ለገዳሙ በስጦታ የተበረከቱ ዘውዶች፣ ጋሻዎች እና አልባሳት፣ ከቆዳ የተሠራ የጠጅ ማንቆርቆሪያ፣ የቅዱስ ያሬድ ፅናፅል እና ሌሎችም ቅርሶች እንደሚገኙ አንስተዋል፡፡
ዙር አምባ አቡነ አረጋዊ ገዳም ከታሪካዊነቱ ባሻገር ልዩ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ያለው በመኾኑ ለጎብኝዎች ተመራጭ እንደሚያደርገውም ተናግረዋል።
በገዳሙ የሚገኙት ቅርሶች ተጠብቀው ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ የሚያስችል ሙዚዬም በቢሮው እና በኅብረተሰቡ ተሳትፎ እየተገነባ እንደሚገኝም የቅርስ ባለሙያው አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!