ሻደይን በድምቀት ለማክበር መዘጋጀታቸውን የሰቆጣ ወረዳ ልጃገረዶች ተናገሩ።

0
29
ሰቆጣ: ነሐሴ 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሻደይን በድምቀት ለማክበር የቡድን ልምምድ መጀመራቸውን የሰቆጣ ወረዳ ልጃገረዶች ተናግረዋል።
ሻደይ ሃይማኖታዊ መሠረት ያለው ባሕላዊ የልጃገረዶች ጨዋታ ነው። የሻደይ ሳምንታት ሴቶች በነጻነት የሚጫወቱበት እና ባሕላቸውን የሚገልጹበት ልዩ የነጻነት በዓልም ነው። ወጣት መቅደስ ሞላ የሻደይ ባሕላዊ ጨዋታን ከልጅነቷ ጀምሮ እየተጫወተች እንዳደገች ለአሚኮ ተናግራለች። በብሔረሰብ ደረጃ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ የማክበር ዕድሉን እንዳገኘች የገለጸችው መቅደስ በዚህ ዓመትም በድምቀት ለማክበር መዘጋጀቷን ነው የተናገረችው።
ሌላኛዋ የሰቆጣ ወረዳ ነዋሪዋ ዓለምናት ቢበይን የሻደይ በዓል የሴቶች መድመቂያ ልዩ ቀን መኾኑን ነው የተናገረችው። በዚህ ዓመትም ሻደይን በባሕል አልባሳት ተውባ እና በጌጣጌጦች ደምቃ ለመዋል የአልባሳት ቅድመ ዝግጅቷን እንዳጠናቀቀች ገልጻለች። ከጓደኞቿ ጋርም የሻደይን ዜማዎች እየተለማመደች መኾኑን የተናገረችው ዓለምናት ሌሎች ቆነጃጅቶችም ከወዲሁ እንዲዘጋጁ መክራለች።
የሻደይ በዓል የሴቶች የነጻነት ቀን ቢኾንም ወንዶችም የትዳር አጋራቸውን የሚያገኙበት እና እጮኛቸውን የሚያዩበት በዓል መኾኑን የተናገረው ደግሞ ወጣት ተመስገን ጌታሁን ነው። ወንዶች በባሕላዊ አለባበስ ተውበው የሻደይ ተጨዋቾቹን እንደሚያጅቡ ነው የገለጸው።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ እዮብ ዘውዴ በዓሉ በብሔረሰብ ደረጃ ከነሐሴ 16 እስከ 18/2017 ዓ.ም ድረስ ባሉት ቀናት በድምቀት እንደሚከበር ተናግረዋል። በዓሉ እስከ ታች ድረስ ከነሐሴ 16 እስከ 21/2017 ዓ.ም ባሉት ቀናት መከበሩ እንደሚቀጥልም ነው የገለጹት። በዓሉን በደመቀ ሁኔታ ለማክበር በቂ ዝግጅት መደረጉንም ገልጸዋል። በዞን ደረጃ ለሚከበረው የሻደይ በዓል የንግድ፣ ባዛር እና የተለያዩ አውደ ርዕዮች እንደሚኖሩትም ተናግረዋል።
ወይዘሪት ሻደይን ጨምሮ የተለያዩ መርሐ ግብሮች እንደሚኖሩትም ገልጸዋል። ለዚህም በኮሚቴ የተዋቀረ የቅድመ ዝግጅቱ ሥራ እየተጠናቀቀ መኾኑን ነው ያመላከቱት። የሻደይን በዓል በሰቆጣ ከተማ ለማክበር የሚመጡ እንግዶችንም በዋግ ባሕል እና ሥርዓት ለመቀበል ተዘጋጅተናል ነው ያሉት። ለመላው ኢትዮጵያውያንም ሻደይን በሰቆጣ እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ: ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here