ሰቆጣ: ነሐሴ 02/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሻደይ በዋግ ኽምራ ከነሐሴ 16 እስከ 21 ባሉ ቀናት በድምቀት የሚከበር የሴቶች የነጻነት በዓል ነው። ይኽንን ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ በዓል ለማክበር ኮሚቴ ተዋቅሮ በዕቅድ እየተመራ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ሲሠራ መቆየቱን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የመንግሥት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኀላፊ እና የኮሚቴው የሚዲያና መዝናኛ ክፍሉ ሰብሳቢ ከፍያለው ደባሽ ተናግረዋል።
የሻደይን በዓል በድምቀት ለማክበር ሰፊ ሥራ መሠራቱንም ጠቅሰዋል።
ሻደይ ለዋግ ሕዝብ በየዓመቱ እንደሙሽራ የምትወደድ እና የምትታጀብ በዓል ናት ያሉት ኀላፊው በዓሉ ባሕላዊ ትውፊቱን ጠብቆ እንዲከበር ልዩ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ እንደኾነም ተናግረዋል። የዋግ ኽምራን ባሕላዊ የሻደይ ጨዋታ በዩኒስኮ ለማስመዝገብ ከክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመኾን እየሠሩ እንደኾነ የገለጹት ደግሞ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ እዮብ ዘውዴ ናቸው። የሻደይ ባሕላዊ ጨዋታ በሰቆጣ ከተማ ለማክበር ለሚመጡ እንግዶች በዋግ ባሕልና ወግ መሠረት ለመቀበል ተዘጋጅተናል ብለዋል።
የዋግ ተወላጆችም በሰቆጣ ከተማ ተገኝተው የናፈቃቸውን የሻደይ ጨዋታ እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርበዋል። መገኘት ያልቻሉ ደግሞ በያሉበት ከተማ በጋራ ተሰባስበው የሻደይን ባሕላዊ ጨዋታ በማሳየት በዓሉ እድገት እና ዓለም አቀፋዊነት እንዲኖረው የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን