“በነሐሴ ወር የሚገለጡ የአማራ ክልል ሕዝብ መልኮች”

0
48
ደብረ ብርሃን: ነሐሴ 03/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአሮጌው ዓመት መሰናበቻ፤ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ፣ ከ13ኛው ወር ቀደም ብሎ በወርሐ ነሐሴ ሁለተኛው ሳምንት ጀመሮ የአማራ ክልል ሕዝብ የማንነቱ መገለጫ የኾኑ እሴቶቹን በዓደባባይ የሚገልጥባቸው በዓላት መከበር ይጀምራሉ።
የክልሉ ሕዝብ እጅግ በርካታ እሴቶች፣ ባሕሎች እና ወጎች ባለቤት ነው። አዲስ ዓመት መጣሁ መጣሁ ሲል በዓደባባይ የሚያከብራቸው በዓላት ነባር እሴቱን እና ማንነቱን በወጉ እና በቅጡ ማሳየት የሚችልባቸው ናቸው። በእርግጥ ነሐሴ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ልዩ ትርጉም ያለው ነው።በግብርና ሥራ ለሚተዳደረው የክልሉ ነዋሪ ደግሞ ከሐምሌ ዶፍ ዝናብ ተሻግሮ፤ የነሐሴን ጭጋጋማ አየርም አልፎ የሰብሉ ቡቃያ ማደግ ጀምሮ፤ ለፍሬ ሲታጭ “ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት” ብሎ መንፈሱን በአዲስ ተስፋ ይሞላል።
“እንዴት ከረማችሁ”? ሲልም ወገኑን ይጠይቃል። ወርሐ ነሐሴ መልክ ላጭ ገጸ በረከት ይዞ ነው ብቅ የሚለው።
ከነሐሴ 13/2017 ዓ.ም ጀምሮ የሚከበሩ የዓደባባይ በዓላትን መሠረት አድርጎ አሚኮ ከክልሉ ባሕል እና ቱረዝም ቢሮ ኀላፊ መልካሙ ጸጋዬ ጋር ቆይታ አድርጓል።ቢሮ ኀላፊው ከነሐሴ 13 ጀምሮ በዓደባባይ በርካታ በዓላትን እናከብራለን ብለዋል። ደብረ ታቦርን በደብረ ታቦር፣ ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል፣ እንግጫ ነቀላ እና ከሴ አጨዳ ከነሐሴ 13 ጀምረው እስከ አዲስ ዓመት ዋዜማ ድረስ የሚከበሩ ነባር በዓላት ስለመኾናቸው አስረድተዋል።
በዚህ ዓመትም ደብረ ታቦርን በደብረ ታቦር፣ ሻደይ በዋግ ኸምራ፣ አሸንድዬ እና ሶለል በሰሜን ወሎ ይከበራሉ ነው ያሉት። የከሴ አጨዳ እና እንግጫ ነቀላ በዓላት ደግሞ በምሥራቅ ጎጃም በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራሉ ብለዋል።
እነዚህ በዓላት በሚከበሩበት አካባቢ ብቻ የተወሰኑ አይደሉም የሚሉት ኀላፊው በዓለም አደባባይ ከፍ ብለው እንዲታዩ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ስለመኾናቸውም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ሕዝብ የትኛውንም እንግዳ በክብር ተቀብሎ የማስተናገድ የቀደመ ልምዱ ዛሬም ቀጥሎ የበዓል እንግዶቹን እየጠበቀ ነው ነው ያሉት።ካሁን በፊት በዓላቱ ሲከበሩ በየአካባቢው ነበር ያሉት አቶ መልካሙ በተሠሩ ሥራዎች ክልላዊ መልክ እንዲኖራቸው እና በዓላቱ ሀገራዊ ኾነው እንዲመዘገቡ አስችለናል ብለዋል። ይህንን በማሳደግ ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባሕል ማዕከል ለማስመዝገብ ሰነዶችን የማደራጀት ተግባራት እየተሠሩ ናቸው ነው ያሉት።
የክልሉ ሕዝብ ነባር እሴቶቹን በመጠበቅ ለዛሬው ትውልድ አብቅቷል ያሉት አቶ መልካሙ ለዜጎች የእርስ በእርስ መስተጋብር እነዚህ በዓላት ሲጫወቱት የኖሩት ሚና ቀላል አይደለም ብለዋል። አሁን ደግሞ በዓላቱ ብሔሮች እና ብሔረሰቦችን በማካተት ኑ እና ውበትን እንግለጥ፤ ፍቅርን እንዝራ” እያሉ ነው ብለዋል።በክልላዊ የማጠቃለያ መርሐ ግብሩ ላይ እነዚህ የሕዝብ ተወካዮች ተገኝተው ይታደማሉ ነው ያሉት። በየትኛውም አጋጣሚ እና በምንም ሁኔታ ክልሉን የሚረግጥ እንግዳ በአሸንድዬ ወይንም ሶለል ላይ እንደሚታየው ለምለም ቄጤማ ጎዝጉዞ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት ተጠናቋል ነው ያሉት።
ዘጋቢ: ኤልያስ ፈጠነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here