የእንግጫ ነቀላ እና ከስይ አጨዳ ባሕላዊ ክዋኔዎች አብሮነትን በማጠናከር ረገድ ጉልህ ፋይዳ አላቸው፡፡

0
38
ደብረ ማርቆስ፡ ነሐሴ 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ምሥራቅ ጎጃም ዞን የበርካታ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ባሕላዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ታሪካዊ ቅርሶች እንዲሁም ትውፊቶች ባለቤት ነው፡፡ በምሥራቅ ጎጃም ዞን የእንግጫ ነቀላ እና ከስይ አጨዳ ባሕላዊ ክዋኔዎች ልጃገረዶች እና ወጣት ወንዶች የአዲስ ዓመት መምጣትን እና የአሮጌው ዘመን መገባደድን ምክንያት በማድረግ የሚያከናውኗቸው ጨዋታዎች ናቸው፡፡
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ብርቄ ይዘንጋው በዞኑ በርካታ የማይዳሰሱ ባሕላዊ ክዋኔዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።
ከእነዚህ ክዋኔዎች መካከል የእንግጫ ነቀላ እና የከስይ አጨዳ በድምቀት እንደሚከበሩ አስረድተዋል፡፡ የአዲስ ዓመት መምጣትን አስመልክቶ የሚከበሩት እነዚህ በዓላት ከነሐሴ 16 ጀምሮ እስከ አዲስ ዓመት መግቢያ ድረስ ይከበራሉ፡፡
የከስይ አጨዳ በዓል በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች ከነሐሴ 16/2017 ዓ.ም ጀምሮ የሚከበር መኾኑን የገለጹት መምሪያ ኀላፊዋ በተለይ በእናርጅ እናውጋ፣ እነማይ እና ሸበል በረንታ ወረዳዎች በድምቀት እንደሚከበር ተናግረዋል፡፡ የእንግጫ ነቀላ በዓል ልጃገረዶች እና ወጣቶች የአዲስ ዓመት እና አዲስ ተስፋ መምጣትን ለማብሰር የእንግጫ ጉንጉን፣ አድዮ እና ሶሪ አበባዎችን በመጨመር የእንኳን አደረሳችሁ መልካም ምኞታቸውን የሚገልጹበት በዓል መኾኑንም መምሪያ ኀላፊዋ አብራርተዋል፡፡
ማኅበራዊ መስተጋብርን እና አብሮነትን በማጠናከር ረገድ እነዚህ በዓላት ጉልህ ፋይዳ እንዳላቸው ያነሱት ኀላፊዋ “የባሕል እሴቶቻችን ለዘላቂ ሰላማችን” በሚል መሪ መልዕክት ከነሐሴ 16/2017 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም ወረዳዎች ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውንም አመላክተዋል፡፡ የጎጃም ሕዝብ መገለጫ የኾኑትን የእንግጫ ነቀላ እና ከስይ አጨዳ በዓላት ለማስተዋወቅ እየተሠራ መኾኑን የገለጹት መምሪያ ኀላፊዋ በዓሉን በጋራ እናክብር ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here