ደብረ ታቦርን በደብረ ታቦር

0
62

ደብረ ታቦር: ነሐሴ 06/2017 ዓ.ም (አሚኮ)

“ደብረ ታቦር ከዋለ የለም ክረምት፣ ምነው አለ እንጂ ወር ከሁለት ሳምንት”

ስንኙ የቡሔን ወይም የደብረታቦር በዓልን ተከትሎ የሚዘወተር ነው። ለምን ሲባል ከበዓሉ ማግስት የክረምቱን መጠናቀቅ እና የበጋውን የመምጣት ተስፋ ለማሳየት እንደኾነ ይነገራል።

የቡሔ ትርጉም መገለጥ፣ ክረምቱ አልፎ የብርሃን ጎህ የሚወጣበት ወቅት ማብሰሪያ መኾኑን የነገሩን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የደብረ ታቦር ኢየሱስ እና የመካነ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ አሥተዳዳሪ እና የተክሌ አቋቋም ምስክር ትምህርት ቤት ምክትል መምህር መልአከ ታቦር ዘውዴ መንግሥቱ ናቸው።

በዓሉ ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከነብያት እና ከሐዋርያት ጋር በመኾን በደብረ ታቦር ተራራ ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበትን ምሥጢር የሚያዘክር ነው ይላሉ።

በዓሉ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ይዘቱን እንደጠበቀ ለተተኪ ትውልድ ለማስረከብ መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል።

የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አለበል ደመላሽ ቡሔ መነሻው ሃይማኖታዊ ሥርዓት መኾኑን ገልጸዋል። ባሕላዊ ክዋኔዎችም የሚንጸባረቁበትን በዓል ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ሥርዓቱን ጠብቆ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን ተናግረዋል።

የዋዜማው ዕለት የእቴጌ ጣይቱ እና የአጼ ምኒልክ የልደት ቀን መኾኑ በዓሉን ያደምቀዋል ያሉት ኀላፊው በዓሉም በድምቀት እንደሚከበር ነው የተናገሩት።

የቡሔ በዓልን ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ይዘቱን ጠብቆ ማክበር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለውም ጠቁመዋል። በዓሉ አንድነትን የሚያጎለብት፣ አብሮነትንም የሚያጠናክር ነው ብለዋል።

በዓሉ የቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቃት ለገቢ ምንጭነት እንዲውል ከማድረግ ባሻገር ባሕልን ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ መኾኑን ተናግረዋል።

ይህን መሠረት በማድረግም ወጣቶች፣ ሕፃናት እና ልጃገረዶች የተካተቱበት በርካታ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እየሠሩ መኾኑን ተናግረዋል።

በሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ሥርዓቶች የሚደምቀው በዓሉ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ እየተሠራበት መኾኑን ነው አመላክተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here