የሻደይ በዓል በሰላም እንዲከበር እየሠሩ መኾኑን የሰቆጣ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ።

0
31
ሰቆጣ: ነሐሴ 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በመላው ዋግ ኽምራ ከነሐሴ 16 እስከ 21 ቀን ድረስ በድምቀት የሚከበረውን የሻደይ በዓል በሰላም ለማክበር ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር አደረጃጀት በመፍጠር እየሠሩ መኾኑን የሰቆጣ ከተማ ወጣቶች ተናግረዋል።
ሻደይ የነጻነት እና የእኩልነት ማሳያ በዓል ነው። ልጃገረዶች ያለ ከልካይ የሚጫወቱበት ትልቅ በዓል ነው። ወጣት ወልዴ ተክላት የሰቆጣ ከተማ ነዋሪ ነው። የሻደይ በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበር በሰፈር ተደራጅተው ሰላማቸውን ለማስጠበቅ መዘጋጀታቸውን ገልጿል። ሻደይ በራሱ የሰላም ምልክት ነው የሚለው ወጣት ወልዴ በዋግ ያለውን አንጻራዊ ሰላም አጽንተን በዓሉን በድምቀት ለማክበር ተዘጋጅተናል ብሏል።
ከልጅነት ጀምረን በሰላም እየተጫወትን ያከበርነውን በዓል እንዳለፉት ዓመታት በድምቀት ለማክበር ተዘጋጅተናል ያለው ደግሞ ወጣት ጣምተው ተክላት ነው። ሁሉም ወጣት በሰፈር በመደራጀት እና ሰላሙን በመጠበቅ ለሻደይ በዓል ድምቀት የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባልም ብሏል። የሻደይ በዓል በሰቆጣ ከተማ በማዕከል ደረጃ የሚከበር በመኾኑ የሰቆጣ ከተማ ወጣቶች ትልቅ ኀላፊነት እንዳለባቸው የገለጹት ደግሞ የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኮማንደር ነጋሽ ተንሳይ ናቸው።
ከወጣቱ ጋር የጋራ ውይይት በማድረግ የቅድመ ዝግጅቱን ሥራ እንዳጠናቀቁ የገለጹት ኮማንደር ነጋሽ የሻደይን በዓል ካለፉት ዓመታት በተለየ ሁኔታ ለማክበር የጸጥታ መዋቅሩ ከሰላም ወዳዱ ወጣት ጋር በቅንጅት እየሠራ ነው ብለዋል። በዋግ ኽምራ ያለው ሰላም የመጣው የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና በጠንካራ ወጣቶች ብርታት እንደኾነ የተናገሩት ደግሞ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ሃማሳ አለቃ አዘዘው አዳነ ናቸው። የሻደይን በዓል በድምቀት ለማክበር የጸጥታ መዋቅሩ ከማኅበረሰቡ ጋር በቅንጅት ተግባራትን እያከናወነ ነውም ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here