“ደብረ ታቦርን በደብረ ታቦር”

0
35
ባሕር ዳር: ነሐሴ 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በነሐሴ ወር ከሚከበሩ በዓላት መካከል የደብረ ታቦር በዓል አንዱ ነው። በዓሉ በደብረ ታቦር ከተማ ነሐሴ 13 በድምቀት ይከበራል።
ይህ በዓል በመላው አማራ ክልል የሚከበር ቢኾንም በተለየ ድምቀት “ደብረ ታቦርን በደብረ ታቦር” በሚል መሪ መልዕክት በደብረ ታቦር ከተማ ተከብሮ ይውላል። የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዓባይ መንግሥቴ በዓሉ ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ በተጨማሪ ባሕላዊ እሴቱም የጎላ መኾኑን ገልጸዋል። የቡሄ በዓል ለረጅም ዘመናት የኖረ፣ የትውልድ ማስተማሪያ እና የእሴት መገንቢያ በመኾኑ እየጠበቅነው እና እየተንከባከብነው ነው ብለዋል።
በዓሉ የሕዝብ በዓል መኾኑን የጠቆሙት አቶ ዓባይ ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶት እንዲለማ፣ እንዲተዋወቅ እና ለተተኪው ትውልድ እንዲተላለፍ እየተሠራ ስለመኾኑም ተናግረዋል። የአካባቢውን ባሕል፣ ወግ እና እሴት አጉልቶ በማውጣት ሰፊ የጎብኝዎች መዳረሻ በመኾንም ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ነው የገለጹት።ይህ በዓል በተለይም የአካባቢውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማነቃቃት ትልቅ ድርሻ እንዳለው አንስተዋል። በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች ለማክበር ቢሮው ከክልል ጀምሮ እስከታች ድረስ ሰፊ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አንስተዋል።
ከሌሎች ክብረ በዓላት ጋር ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ታች በማውረድ ድጋፍ የማድረግ እና የማስተዋወቅ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውንም አስታውቀዋል። የደብረ ታቦር በዓል በደብረ ታቦር ከተማ በፓናል ውይይቶች እና በተለያዩ ዝግጅቶች መከበር መጀመሩንም ገልጸዋል። ይህንን በዓል ከክብረ በዓልነት ባለፈ የቱሪስት መዳረሻ በማድረግ ለአካባቢው ማኅበረሰብ የኢኮኖሚ ምንጭ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም አቶ አባይ አመላክተዋል።
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here