አሸንድዬ የላስታ ላሊበላ ድንቅ ውበት !

0
77
ባሕር ዳር: ነሐሴ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሕዝብ ማንነቱን የሚገልጽበት የራሱ የኾነ ባሕል እና ወግ ያለው ነው፡፡ የላስታ ላሊበላ ሕዝብ ማኅበራዊ ዕሴቱን ከሚገልጽባቸው ባሕላዊ እሴቶች መካከል በየዓመቱ የሚከወነው አሸንድዬ በዓል አንዱ የአካባቢው ማኅበረሰብ መገለጫ ክብረ በዓል ነው።
ይህ በዓል ሃይማኖታዊ መሠረት ያለው እንደኾነም ይነገርለታል፡፡ የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም የአራቱ ጉባኤያት መምህር ሊቀ ሊቃውንት ሳሙኤል አስናቀ የአሸንድዬ በዓል በፍልሰታ ጾም ፋሲካ የድንግል ማርያምን በዓለ ዕርገት አስመልክቶ የሚከበር መኾኑን ተናግረዋል፡፡ በዓሉ በሔዋን የመጣውን ዕዳ በድንግል ማርያም አማካኝነት ሴቶች ያገኙትን ነጻነት የሚያወሳ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ አሸንድዬ ቅጠሉ የብሉይ ዘመን ጨለማ በድንግል ማርያም እንዳበቃ አሁንም የክረምቱን ዘመን አብቅቶ አዲስ ዓመት መምጣቱን የሚያበስሩበት እንደኾነ ነው ያስረዱት፡፡
ወይዘሮ ገነት አሰፋ የላሊበላ ከተማ ነዋሪ ናቸው። በልጅነታቸው ያሳለፉትን የአሸንድዬ ክብረ በዓል ትውስታቸውን አካፍለውናል። አሸንድዬ ብለው የሚጠሩት በበዓሉ ወቅት ልጃገረዶች በወገባቸው የሚያስሩት ረጅም እና ስሩ ነጭ ከላይ አረንጓዴ የኾነ ቅጠል ነው። በዓሉም ስያሜውን ያገኘው ከዚሁ ነው ብለውናል፡፡
በላስታ ላሊበላ የአሸንድዬ በዓል በየዓመቱ ከነሐሴ 16 ቀን ጀምሮ የሚከበር ነው። ቅድመ ዝግጅቱ ከሳምንት በፊት ይጀመራል ነው ያሉት። ልጃገረዶች በሰፈራቸው በመሠባሠብ በዓሉን አንዴት እንደሚያከብሩት ይወያያሉ። ቡድኑን የምትመራው አለቃ የመምራት እና የማሥተባበር ችሎታ ያላት፣ በአካል እና በዕድሜ ከፍ ያለች መኾን እንዳለባትም ገልጸውልናል። ኀላፊነቷም ቡድኑን ማሥተባበር፣ መምራት እና ገንዘብ መያዝ ነው ይላሉ፡፡ ከዚያም መርሐ ግብራቸውን የሚጀምሩበትን እና እንዴት እንደሚከውኑት ይነጋገራሉ ነው ያሉት፡፡ በዓሉ ሦስት ቀን ሲቀረው ደግሞ ጸጉራቸውን እንደሚሠሩ ነግረውናል። የጸጉር አሠራሩም ታዳጊዎች ጋሜ፣ ቁንጮ እና ሳዱላ ሢሠሩ ከፍ ያሉት ልጃገረዶች ደግሞ ሹርቤ እና አፈሳሶ የሚባል የጸጉር ስሬት እንደሚሠሩ ትናንታቸውን አውስተውናል።
ልጃገረዶች ለበዓሉ ከጥጥ የተሠራ ጥልፍ ቀሚስ፤ የልጆች ከሌላቸውም የእናቶቻቸውን በመቀነት አሳጥረው እንደሚለብሱ ነግረውናል፡፡ በዕለቱ በእጅጉ ለመዋብ የአንገት ጌጦችን አጭር መስቀል፣ ትልቅ መስቀል፣ ድሪ፣ ማርዳ እና ድባ ልጃገረዶች ያደርጋሉ ብለዋል፡፡ ታዳጊዎች ደግሞ ቁርጥ የሚባል የአንገት ጌጥ ያደርጋሉ ነው ያሉት፡፡ በበዓሉ ዋዜማ አሸንድዬ ቅጠሉን ከዱር በማምጣት ሁሉም ሴቶች በወገባቸው ልክ በገመድ በመጎንጎን ይሠራና እንዳይደርቅ ሙጃ ሳር ውስጥ እርጥበት ባለበት ያድራል ነው ያሉት። ነሐሴ 16 በበዓሉ ዕለት በጠዋት ሁሉም ተነስተው በተቀጣጠሩበት ቦታ ተገናኝተው አሸንድዬውን ወገባቸው ላይ በማሰር፣ የባሕል ልብስ እና ጌጦቻቸውን ያስተካክላሉ ነው ያሉት። ከዚያም በመጀመሪያ በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ቤተክርስቲያን በመሔድ እና ለፈጣሪያችን ምስጋና በማቅረብ ከሃይማኖት አባቶች ምርቃን ይቀበላሉ።
በመቀጠል በየሁሉም ሰው መኖሪያ ቤት በመሔድ አሸንድዬ ጨዋታ የተለያዩ ስንኞችን በመግጠም እና በማዜም እንደሚጫወቱም አውስተውልናል።
አሸንድዬ አሸንዳ ሙሴ
ፈሰስ በይ በቀሚሴ
አበ ሙሴ ኧኸ ወርቅ አበሙሴ
ፈሰስ በይ በቀሚሴ…. እያሉ ያዜማሉ።
የቤቱ ባለቤቶችም ያላቸውን ብር እና ዳቦ ይሰጣሉ። ከሌለ ደግሞ ከዓመት እንዲያደርሰን ተመርቀን እንወጣለን ነው ያሉት፡፡ በዚህ ሂደት ለአንድ ቡድን ሁለት ወንዶች ጅራፍ የሚያጮኹ ይከተላሉ፡፡ እነዚህ ወንዶች የሴቶች አሸንድዬ በሌሎች ቡድኖች እንዳይበጥስ እና የሚፈልጋት ልጃገረድ ካለችም የመጠበቅ ዓላማ ያላቸው ናቸው። አሸንድዬ እየተባለ የተሰበሰበው ገንዘብ ይቀመጣል። አዲሱ ዓመት እንዳለፈ የቡድኑ አባላት በተሰበሰበው ገንዘብ ጠላና ዳቦ ያዘጋጃሉ፡፡ የመስቀል ዕለትም የአካባቢውን ሰዎች በመጥራት ደግሰው ያበላሉ፤ ያጣጣሉ። በአበውም ይመረቃሉ ነው ያሉን። የዚህ ዘመን የአሸንድዬ ተጫዋች የኾነችው በላይነሽ ገብረ አምላክ ደግሞ ለክብረ በዓሉ የአሸንድዬ ግጥም እና ዜማውን በቡድን እንደሚለማመዱ ለአሚኮ ተናግራለች፡፡
ከበዓሉ ቀደም ብለው ስለ አልባሳት፣ ጌጣጌጦች፣ ስለሚያካሂዱት መርሐ ግብር በመመካከር እንደሚዘጋጁ ነው የገለጸችልን፡፡ ከነሐሴ14 ጀምረው ልጃገረዶች ጸጉራቸውን ይሠራሉ፤ እንደቀደመው ሁሉ ልጆች ጋሜና ቁንጮ ልጃገረዶች ደግሞ ሹሩባና አፈሳሶ ይሠራሉ ብላለች፡፡
ልጃገረዶች አራት ውርድ ጥልፍ ቀሚስ በመቀነት ተሸንሽኖ ይለብሳሉ፤ ሕጻናት ደግሞ ትፍትፍ ቀሚስ ይለብሳሉ። አንገታቸው ላይ ደግሞ ቁርጥ፣ መስቀል፣ ድሪ እና ማርዳ በማድረግ ይደምቃሉ ነው ያለችው፡፡ የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዲያቆን አዲሴ ደምሴ የአሸንድዬ በዓል በላስታ ላሊበላ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ይዘቱን ጠብቆ የሚከበር በዓል ነው ብለዋል፡፡
በዓሉ የፍልሰታ ጾም ማብቂያ እና የድንግል ማርያምን የዕርገት በዓል አስመልክቶ በላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት በካህናት እና በሰንበት ተማሪዎች በመዝሙር እና በሃይማኖታዊ ክዋኔዎች ይከበራል ነው ያሉት፡፡ ይህንን መነሻ በማድረግ ማኅበረሰቡ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ በየዓመቱ ከነሐሴ 16 ጀምሮ ልጃገረዶች አምረው እና ተውበው የአሸንድየ ቅጠል በወገባቸው በማሰር አደባባይ የሚወጡበት መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በበዓሉ ላይ የሚሳተፉት ልጃገረዶች ሲኾኑ ባሕሉ እንዳይበረዝ እናቶች እገዛ እንደሚያደረጉላቸውም ገልጸውልናል፡፡ በዓሉ ሴቶች በነጻነት አደባባይ የሚወጡበት፣ አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበት ማኅበራዊ መስተጋብራቸውን ለማጠናከር የሚጠቀሙበት እንደኾነም ተናግረዋል፡፡ ባሕሉን በማይዳሰስ ባሕላዊ ቅርስነት በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ከክልሉ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ጋር እየተሠራ መኾኑንም ዲያቆን አዲሴ ገልጸዋል፡፡ በዚህ ዓመትም የአሸንድዬ በዓል ባሕላዊ እሴቱን ጠብቆ “ባሕላዊ ዕሴቶቻችን ለዘላቂ ሰላማችን” በሚል መሪ መልዕክት ትላንት ከዋዜማው የጀመሮ እየተከበረ ሲኾን በዛሬው ዕለትም ዋናው በዓል በላሊበላ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው፡፡
ዘጋቢ፦ ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here