ሰቆጣ: ነሐሴ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሻደይ በዓል በሰቆጣ ከተማ “ዝክረ ሌተናል ጄኔራል ኃይሉ ከበደ” በሚል መሪ መልዕክት እየተከበረ ነው።
በበዓሉም የባሕል ትርዒቶች እና የአደባባይ የሻደይ ጨዋታ የቀረበ ሲኾን ተጋባዥ አርቲስቶችም የሙዚቃ ድግሳቸውን አቅርበዋል።
በዚህ ዓመት የሻደይ ጨዋታ ልዩ ድምቀት ከኾኑት መካከል የኮረም፣ የዛታ እና የወፍላ ወረዳ የባሕል ተጫዋቾች ይገኙበታል።
ወጣት ሰላም ተፈሪ የሻደይን በዓል በሰቆጣ ከተማ በማክበሯ መደሰቷን ገልጻለች። “ሻደይ ለዘመናት የተነጠቅነውን ማንነት መልሰን እንድንጎናጸፍ አድርጎናል” ያለችው ወጣቷ የኮረም የሻደይን ባሕላዊ አጨዋወትም በሰቆጣ ከተማ በማቅረባቸው መደሰቷን ለአሚኮ ተናግራለች።
ሌላኛዋ የኮረም ከተማዋ ወጣት ሳምራዊት ካሳ ሻደይ የነጻነት ቀን መኾኑን ያረጋገጥነው በዚህ ዓመት የሻደይ በዓል ነው ብላለች። “ሻደይን ከወንድም እህቶቻችን ጋር እንደማክበር ያለ ደስታ የለም” ነው ያለችው ወጣት ሳምራዊት። በዋግ ኽምራ በሚካሄዱ የመድረክ ክዋኔዎች ሁሉ የኮረም ከተማ አሥተዳደር መሳተፉ የቀደመ ማንነታችንን እንድናገኝ አግዞናል ያሉት ደግሞ የኮረም ከተማ አሥተዳደር የባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መዓዛ አብርሃ ናቸው። የኮረምን ባሕላዊ አለባበስ እና ባሕላዊ ቁሳቁስ በባሕላዊ ትርዒቱ ማሳየታቸውንም አስገንዝበዋል። የዋግ ሕዝብ ልዩ ድጋፉን እንደሰጣቸውም ነው የጠቆሙት።
“ሻደይ ለዘመናት ያጣነውን ማንነት መልሰን እንድናገኝ አግዞናል” ያሉት ወይዘሮ መዓዛ የዋግ ሕዝብም ለሰጣቸው ፍቅር በኮረም ሕዝብ ሥም ምሥጋና አቅርበዋል። የዚህ ዓመት የሻደይ በዓል ለየት የሚያደርገው የኮረም፣ የዛታ እና ወፍላ ወረዳ የሻደይ ባሕል ተጫዋቾች መሳተፋቸው ነው ያሉት ደግሞ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ኢዮብ ዘውዴ ናቸው። በችግር ውስጥ ኾነውም እንኳን ሻደይን ከማክበር ማንነታቸውን ከመመስከር ወደ ኋላ አላሉም ያሉት ኀላፊው የሻደይ በዓል የማንነት ማረጋገጫ ማኅተም መኾኑን በተግባር ያሳየ በዓል እንደኾነ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን