ባሕር ዳር: ጳጉሜን 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የክረምት ወቅት ሊያልቅ ሲቃረብ፣ ምድሪቱ ስታሸበርቅ፣ ሜዳ እና ተራራዎች በአበቦች ሲያጌጡ፣ አዲስ ዓመት መዳረሻ ላይ የምሥራቅ ጎጃም ልጃገረዶች የሚያከብሩት ተወዳጅ ክብረ በዓል አላቸው። እሱም የእንግጫ ነቀላ እና ከሴ አጨዳ ነው።
በዓሉን ማክበር የተጀመረው በኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃ ታሪክን መሠረት በማድረግ ነው ይባላል። በኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃ ምድርን ሸፍኗት ነበር።
ኖኅም በመርከብ ነበር። የጥፋት ውኃም አቆመ። ኖኅም ውኃው መጉደሉን ለማጣራት እርግብን እንደላካት ይነገራል፡፡ እርግብም የውኃውን መጉደል እና የአካባቢውን መለምለም ለማሳየት በአፏ ቄጤማ ይዛ ወደ መርከቡ እንደተመለሰች ይነገራል፡፡
ይህም ውኃው ለመጉደሉ እና የጨለማው ዘመን የማለፉ የምስራች ምልክት ኾኖ ይወሰዳል፡፡ ከዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ጋር በማስተሳሰር የእንግጫ ነቀላ በዓል እንደተጀመረ ከአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ልጃገረዶች ልክ እንደ እርግቧ ነጭ ለብሰው የክረምቱ ጨለማ ማለፍን እና የጋራ ሸንተረሩ መለምለም እና ማበብን ለማየት ወደ መስክ ይወጣሉ። እንግጫ ነቅለው እና በአደይ አበባ አስጊጠው ወደ አብያተ ክርስቲያናት እና ዘመድ አዝማድ እየሄዱ “አዲስ ዓመት ገብቷል፤ ክረምቱ አልፏል፤ እንኳን አደረሳችሁ” እያሉ የምስራች ስጦታ ያበረክታሉ፡፡
ልጃገረዶች በዝማሬያቸው የሚያወድሱት እና የበዓላቸው ስያሜ የኾነው እንግጫ ስሩ ነጭ የኾነ የሳር ዘር ነው። ከሴ ደግሞ ጥሩ መዓዛ ያለው ተክል ነው።
በዚህ በዓል ዋናዎቹ ተሳታፊዎች ያላገቡ ልጃገረዶች ናቸው። ወንዶችም በሆያ ሆዬ ጨዋታ ያጅባሉ ያሉን በአነደድ ወረዳ ነዋሪ የኾኑት ወይዘሮ ሙሉቀን አይተነው ናቸው። ልጃገረዶች የተለያዩ ባሕላዊ ዜማዎችን እያዜሙ ወደ መስክ በመሄድ ለስጦታ የሚኾን ከሴ ያጭዳሉ፤ እንግጫ ይነቅላሉ ነው ያሉት።
የሚነቅሉት እንግጫም እምቡጥ ነው። ይህም ገና እምቡጥ ነን የሚለውን የልጅነት ጊዜያቸውን የሚገልጹበት ነው ይላሉ።
በሚነቅሉበት ጊዜ:-
“እንግጫችን ደነፋ፣ ጋሻውን ደፋ
እንግጫችን የወሩ፣ የቦረቦሩ …. ” እያሉም ያዜማሉ ብለውናል።
የነቀሉትን እንግጫ ከአደይ አበባ ጋር በመጎንጎን በመጀመሪያ ወደ ቤተክርስቲያን ሄደው አበባውን ያስራሉ ነው ያሉት። ከሃይማኖት አባቶችም ምርቃን ይቀበላሉ። ከዚያም ተመልሰው በየቤቱ እየዞሩ ዜማዎችን እያዜሙ እና ባሕላዊ ጭፈራ እጨፈሩ የሚያከብሩት ልዩ በዓል እንደኾነ ነው የገለጹት፡፡
በጭፈራቸውም ወንዶችም ደቦት (ከእንጨት የሚዘጋጅ መብራት) ይዘው ያጅቧቸዋል። በየቤቱ እየሄዱ እንጎሮጎባሽ እያሉ እንኳን አደረሳችሁ ይላሉ። ወጣት ወንዶች የሚፈልጓትን ቆንጆም የሚመርጡበት እና የሚያጩበት በዓል ነው። በቀጣዩ ጥር እና በሚያዚያ ወር ለሚደረጉ ጋብቻዎች የመተጫጫ ጊዜ ነው።
ይህ በዓል ልጃገረዶች ከቤት ሥራ ነጻ ኾነው አምረው እና አጊጠው ከእኩዮቻቸው ጋር የሚጫወቱበት እንደኾነም አንስተዋል። ከሚዋቡባቸው መካከል ነጭ የባሕል ልብስ ይለብሳሉ፤ በወገባቸው ላይ ምሪ ያስራሉ። ምሪ ማለት ከቆዳ የሚሠራ እና ጫፉ ላይ ዛጎል ያለበት ያላገባች ሴት የምትታጠቀው መቀነት ነው። በተለያዩ ጌጣጌጦች አምረው እና ደምቀው ለመታየት እንደ ክታብ፣ ድሪ፣ መስቀል፣ ጠገራ ብር፣ አምባር፣ አልቦ፣ የጆሮ ጉትቻ ጌጣጌጦችን በማድረግ ይዋባሉ ነው ያሉት።
ሌላኛዋ የአነደድ ወረዳ ነዋሪ እና የበዓሉ ተሳታፊ የኾነችው ወጣት ተጎዳን ንጉሤ የእንግጫ ነቀላ በዓል ከጳጉሜ 1 ጀምሮ ልጃገረዶች የሚያከብሩት በዓል መኾኑን ገልጻለች። በበዓሉ ወቅት ልጃገረዶች ነጭ ባሕላዊ ልብስ ለብሰው በተለያዩ ጌጦች አምረው በዓሉን እንደሚያከብሩት ተናግራለች።
በዚህ በዓል ልጃገረዶች ከሚወዷቸው የከንፈር ወዳጆች ስጦታ ይበረከትላቸዋል፡፡ ይሄንም በዘፈን ይቀባበሉታል ነው ያለችው።
“የላክህልኝ ድሪ ሰላላ መላላ
መልሰህ ውሰደው ጉዳዬም አልሞላ” ይላሉ።
ቀኑን በሙሉ በመሰል ዜማዎች ሲጨፍሩ እና ሲጫወቱ እንደሚውሉ ገልጻለች። ልጃገረዶቹ እጃቸውን እንሶስላ ሞቀው፤ ፀጉራቸውን አሳምረው፤ የባሕል ቀሚስ ለብሰው፤ ዝማሬ እያሰሙ ይወጣሉ፡፡ በዕለቱም ከሥራ ነጻ ኾነው ሲጫወቱ እና ሲጨፍሩ እንደሚውሉ ተናግራለች። ከሚያዜሙት ዜማ መካከል
እቴ አደይ አበባ ነሽ
ውብ ነሽ ውብ ነሽ
አበባስ ያብባል በየሁሉ ደጅ
ምነው እኔ የሌለኝ የከንፈር ወዳጅ
አንተ የከንፈር ወዳጅ በጊዜ ሳመኝ
ጤፍ አበጥራለሁ የሰው ግዙ ነኝ።
የሰው ግዙ ሆኖ የሰው ግዙ መውደድ
እሳት በገለባ እፍ ብሎ ማንድድ። እያሉ ያዜማሉ።
የአነደድ ወረዳ ባሕል አና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አየነው አበራ በዓሉ በአዲስ ዓመት መዳረሻ ላይ የሚከበር መኾኑን ተናግረዋል። የእንግጫ ነቀላ እና ከሴ አጨዳ ክረምት አልፎ የአዲስ ዓመት መምጣትን አስመልክቶ የሚከበር በዓል መኾኑን ነው የገለጹት።
በዓሉ በአረንጓዴው የጎጃም ምድር ልጃገረዶች ነጭ ለብሰው ድንቅ ዝማሬ እያሰሙ ከጳጉሜ አንድ ጀምሮ እስከ አዲስ ዓመት የሚያከብሩት ነው ብለዋል። ይህንን በዓል ይዘቱን ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ እየተሠራ እንደኾነም አንስተዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ሙሉ ዓለማየሁ የዘንድሮውን የእንግጫ ነቀላ እና ከሴ አጨዳ በዓል እንደ ዞን ጳጉሜን 3/2017 ዓ.ም ለማክበር እየተዘጋጀን ነው ብለዋል። በወረዳዎች ደረጃ ቀደም ብለው በተለያዩ ዝግጅቶች ማክበራቸውን ነው የተናገሩት።
በዓሉ በአደባባይ እና በመስክ ልጃገረዶች እንግጫ ነቅለው በአደይ እና ሶሪት በመጎንጎን በባሕላዊ አልባሳት ተውበው የሚያከብሩት እንደኾነ አንስተዋል። የተለያዩ ዜማዎችን በማሰማት፣ ባሕላዊ ጭፈራ እንደሚያቀርቡም ገልጸዋል።
በበዓሉ ላይ ከወረዳዎች የተውጣጡ ልጃገረዶች፣ ወጣት ወንዶች እና ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ፍሬሕይወት አዘዘው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!