በምሽት ጨረቃ የሚደምቀው ለውፈረ ለውፈ – ዋርዳ ሆየ

0
14
ባሕር ዳር፡ መስከረም 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ ዘመን ብስራትን ተከትሎ ጨለማውን መሸኛ አዲሱን መማፀኛ ቀለል ያሉ ደመራዎች በዋግ ኽምራ ነዋሪዎች መንደር ይጠበቃሉ፡፡
ጭሱ የክረምቱን ጭፍና ሽኝት እና ብርሃኑ የመፃዔ ጊዜው ተስፋ ምልክት ተደርጎም ይወሰዳል፡፡ ይህ ሕዝብ ለእያንዳንዱ የጊዜ ዑደት የራሱ መገለጫዎች ያሉት የባሕል ሀብታም ነው፡፡
ለውፈረ ለውፈ ከአዲስ ዘመን ጅማሮ እስከ መስከረም የመስቀል በዓል ማግሥት የሚጠናቀቅ የ17 ቀናት የምሽት ጨዋታ ነው፡፡
የክርስቶስን ግማደ መስቀል ለማግኘት የተደረገው ፍለጋ የተጀመረው በጭስ ነው፡፡ የዋግ ወጣቶች የሚጫወቱት ለውፈረ ለውፈ ጨዋታ መስከረም 16 ንግሥት እሌኒ መስቀሉን ለማግኘት ሥራ የጀመረችበትን ተምሳሌት ያደረገ ነው ያሉት የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ቤተ ክህነት አስተዳዳሪ ሊቀ ኅሩያን ቀሲስ ኃይሌ ዓለሙ ናቸው፡፡
የመስቀሉ ፍለጋ የሰው ልጆች በአዲስ ዓመት የራሳቸውን ሕይዎት በአዲስ መልኩ እንዲፈልጉ የሚያነቃ ባሕላዊ ይዘት ያለው እየኾነ መምጣቱንም ነው ቀሲስ ኃይሌ የተናገሩት፡፡
መጋቢት 10 የተገኘው የክርስቶስ መስቀል ከእየሩሳሌም እስከ ቁንጥንጢንያ ተራሮች አማንያን ደመራ እየሠሩ እንዳከበሩ ሁሉ አሁንም ይህ ትውልድ በቅብብሎሽ ባሕላዊ ይዘትን ጨምሮ እያከበረው ነው ብለዋል ሊቀ ኅሩያን ቀሲስ ኃይሌ፡፡
ለውፈረ ለውፈ (ዋርዳ ሆየ) ጨዋታው ፀሐይ ወደ ማደርያዋ ስታመራ አካባቢው ለዐይን ያዝ ሲያደርግ ጀምሮ በኽምጠኛ ቋንቋ አርወ (አደባባይ) ተብሎ ከሚጠራ ሥፍራ ላይ ወጣት ወንዶች በትንሹ የሚንቀለቀል እሳት አቀጣጥለው የሚጫወቱት ሃይማኖታዊ ይዘት ያለው በጊዜ ሂደት ባሕላዊ ክዋኔ እየኾነ የመጣ ነው፡፡ የድንግዝግዙ ጨለማ ድባብ የሚደምቀው ቀድሞ በመጡ ተጫዋቾች ለውፈረ ለውፈ የግጥም ጥሪዎች ነው፡፡
ለውፈረ ለውፈ
ለውፈረ ለውፈ
እሆሆ ሽረሮ እሆሆ ሽረሮ
እሆሆ ሽረሮ እሆሆ ሽረሮ
የእኔማ እገሌ የምለው አይሰማማም ወይ
ሥራው አላልቅ ብሎት ጨለማው አስፈራህ ወይ
ኧረ ምን ዓይነት ነው ምን ዓይነቱ ፈሪ
አልቦ ያልጨረሰ፣ ጥጃ ያላሰረ፣ ያልታጠቀ ሱሪ
ለዛሬ ያልኾነ፣ ያልታጠቀ ቁምጣ
ጉልበቱ ይብረክረክ አንዳ’ይኑን ይጣ፡፡
እያሉ በሥራ ምክንያት የዘገዩ ጓደኞቻቸውን ጎንጦ በማያደማው ወግቶ በማይገድለው ወኔ ቀስቃሽ ግጥሞቻቸው ይጣራሉ፡፡
በተለይ በተራራዎች አካባቢ መንደሮቻቸውን ያደረጉት እነዚህ ሕዝቦች የገደል ማሚቶ እያስተጋባ የሚያጮኸው ድምፅ ወንድነታቸውን ይፈታተናል፡፡ የላሞች እና የጥጆዎች ጥሪ በቀነሰበት፣ የከብቶች ልፈፋ ፀጥ ረጭ ባለበት ወቅትማ አብዛኛው መንደርተኛ እራት እየበላ ወይም ሥራ ያዛለውን ሰውነታቸውን ለማሳረፍ ጥድፊያ የሚኾንበት ነው፡፡
አንዳንዴ በየመንደሩ ወጣቶቹ በሚያሰሙት ሩጫ ጋጣቸውን ለማስጠበቅ ከሚጮሁ ውሾች በቀር ከለውፈረ ለውፈ ተጫዋቾችን ድምፅ አልፎ የሚሰማ የለም፡፡ ፍየሎቻቸውን በየማታው እየበተነ የአመሉን የሚያደርሰው ነብር ሲመጣ ውሾች ጮኽ ብለው ሲጮኹ ባለቤቶች ወጥተው ‘‘ጅላው ጅላጉ …. ጅላው ጅላጉ’’ እያሉ ውሻውን የሚያደፋፍሩበት ድምፅ ጥሶ ሊደመጥ ይችላል፡፡
ታዲያ የለውፈረ ለውፈ ጉነጣው ለዘገዩ ወጣቶች ብቻ ሳይኾን ልጆቻቸውን ላዘገዩ ወላጆችም ይደርሳቸዋል፡፡ ያኔ ስማቸው እየተጠራ ሲሾመሩ … ‘‘አረ ተነስልን!’’ ወይም ‘‘ቶሎ በልተህ ሂድ!’’ ብለው ያጣድፉታል፡፡ ‘‘አሁን የእንትና ልጅ ተጠራ! አሁን ደግሞ እገሌን እንዲህ አሉት! ውይ እገሌንም እንዲህ አሉት’’ በማለት የዕለት በዕለት ግንኙነታቸው የሚያዩቸውን የሰዎችን ባሕሪ እያነሱ እየተሳሳቁ ይጎሽሟቸዋል፡፡ ለዚህ ሁሉ ማረፍያው ግን ደርሶ መገላገል ነው፡፡
የእኛማ እገሌ መልካሙ መልካሙ
ልጅን ጉያ ይዞ ምነው አስታመሙ፡፡
የኛማ እገሌ በጣም ይገርማሉ
ነብር ጋር እንዳልዋሉ
አብረው እንዳልታገሉ
ዛሬ ፈርተው መሰል፤ ምነው እምቢ አሉ፡፡
በማለት ፍላጎቱ እንዲነሳሳ አቅል ያሳጣሉ፡፡ ከሞላ ጎደል አብዛኞቹ ከመጡ በኋላ በሚንቦገበገው መለስተኛ የደመራ እሳት ላይ በኽምጠኛ ‹‹ቕርጘ ብረው›› (የብርቱካን መጠን ያለው ትኩስ ድንጋይ) ይጨመራል፡፡
ከዚያማ ከለውፈረ ለውፈ (ናማ ኑማ) ወደ እሆሆ ሽረሮ ያመራል፡፡ በጋራ በለውፈረ ለውፈ ጥሪው በኋላ በትልቅ ግርማ ባላቸው ተምሳሌትነታቸው የትጋት የኾኑ እንስሳት ስም ሁለት ቡድን ፈጥረው ወደ ውድድር ሜዳ ይገባሉ፡፡ አብዛኛው ጊዜ አንበሳ እና ነብር የሚል ስያሜን የየቡድናቸው መጠሪያ ያደርጉታል፡፡
እሆሆ ሽረሮ ከመለስተኛ የደመራ እሳት ላይ የገባውን የሚለበልበውን ድቡልቡል ድንጋይ የተሰየመው ዳኛው በእንጨት ገፋ አድርጎ በሳር እየጠበጠበ ይወረውራል፡፡ በቃ ምን ታደርጉት ልክ እሳት ካለመኖሩ በቀር እንደአውሮፓውያኑ ራግቤ በሉት፡፡ ከዚያማ ዳኛው ‘‘እሆሆ ሽረሮ…’’ ብሎ ራቅ ብለው ከደመራው በወጣው የእሳት ነበልባል ውር ውር እያሉ ወደሚታዩት ተጫዋቾች በኃይል እያንከባለለ መሬት ለመሬት ያሾረዋል፡፡
የለውፈረ ለውፈ ተጫዋቾቹ አቋቋም መስመር የለውም ድንጋዩ ሊገኝ በሚችልበት ሁሉ ተዘበራርቀው ነው የሚፋለሙት፡፡
ይሄ ቀላል ጉዳይ አይደለም፤፡ የወንድነት ማረጋጋጫ በዘገዩ ጊዜ በሽሙጥ የተሰደቡበትን ተረክ ፉርሽ የሚያደርጉበት መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ ማን ነው ያንን የሚፋጅ ድቡልቡል እሳት በመዳፉ ይዞ ከዚያ ሁሉ ወጠምሻ አምልጦ ከደመራው እሳት ላይ ጨምሮ ጮቤ የሚረግጠው? አጓጊ ነው፡፡ ብቻ ተቀባብለውም ቢሆን አለያም በፍትጊያ ውስጥ በስልትም ሆነ በጉልበት ልቆ ያ ነበልባል ውስጥ የሚፋጅ ድንጋይን የመጨመር ትግል ነው፡፡
ድቡልቡሏ ድንጋይ እሳቷን በወጣቶቹ እጆች እየተሻሸች አንዳንዴም ፍጅቷ ሲጠና መሬት ላይ በጉረምሶች እግር እየተረጋገጠች ነበልባልነቷ ይቀንሳል፡፡ በየትኛውም ዘዴ ከመጨወቻ ሜዳው ወደ ነበረችበት እሳት ድንጋዩን ለጨመረ ቡድን እና ግለሰብ የሚቀርብ ሙገሳ፣ ድልቂያ፣ ዘፈን እና ግጥም ያንጎማልላል፡፡
በእርግጥ የመጀመሪያዋ ድንጋይ እሳቱ ጋር ስትጨመር ማንም አያሸንፍም፤ የቅድስት ድንግል ማርያም ነው ተብሎ ይጣላል፡፡ (ጨዋታው ሃይማኖታዊ ይዘት አለው ብያችሁ የለ?)፡፡ የእሷን በረከት ይዞ የመታገል ዕድል ማግኘት የጨዋታውን አጠቃላይ አሸናፊ እንደሚሰማው ዓይነት ነው፡፡ ለአሸናፊዎቹ እንዲህ ተብሎ ሊገጠምላቸው ይችላል፡፡
እሆሆ ሽረሮ እሆሆ ሽረሮ
እሆሆ ሽረሮ እሆሆ ሽረሮ
የብርቱ ልጅ ብርቱ
አንድ ጋን አተላ አይደርስም ካንጀቱ
ከድንጋይ ላይ ድንጋይ ከዚያ ላይ እሳት
እገሌ መብረቁ፤ አንበሳ ጉልበት፡፡
በዚህ የሚያበቃ እንዳይመስላችሁ አሸናፊዎቹ ከተሸናፊዎቹ ወገብ ላይ ቁብ ብለው በመደዳ ‘‘ዝቋላ ደርሼ፣ ሰቆጣ ደርሼ፣ ኮረም ደርሼ፣ ጎንደር ደርሼ፣ ደሴ ደርሼ’’ እያሉ ይደልቃሉ፡፡ አቤት ያኔ ተሸናፊ አያድርገኝ፡፡ ምንኛ ያስችላል፡፡
ጨዋታው በዚህ መልክ ያለገደብ ሊጫወቱት ይችላሉ፡፡ አንዳንዴም እስከ ንጋት የሚዘልቁበት አጋጣሚ እንዳለ ንጉሴ በሪሁን የተባሉ የሰቆጣ ከተማ ነዋሪ ነግውኛል፡፡
ከመስከረም አንድ ቀን ጀምሮ እስከ መስቀል በዓል የሚዘልቀው ይህ ጨዋታ ከአደባባዩ ትዕይንት ባለፈ በየቤቱ በመዞር ወተት እና የወተት ተዋፅኦ፣ ጠላ፣ እንጀራ እና ሙክት ይሰጣል፡፡ በወቅቱ ስጦታ ያላዘጋጁት ደግሞ ‘‘የመስከረም ማርያም፣ የኅዳር ሚካኤል፣ የታኅሣስ ገብርኤል አንድ ጋን ጠላ፣ አንድ ሙክት፣ ይህን ያህል እንጀራ…’’ እያሉ ይሳላሉ፡፡
ወጣቶቹም ቀኑን ጠብቀው ቃል የተገባላቸውን ስለት ይጠይቃሉ:: ‘እምቢ’ ከተባሉ ይመካከሩና በየአቅጣጫው ተራርቀው በመቆም (ተራራ ላይ ሊሆን ይችላል) ከዚያም እርስ በራሳቸው እየተጠራሩ “እከሌ ኡኡ፣ ኧረ እገሌ.. አቤት ኡኡ…” በማለት አስደንጋጭ የሆነ ጥሪ ያደርጋሉ። ከዚያም ቃል ገብቶ አልሰጣቸው ያለውን ሰውየ ስም በመጥራት ‘‘አቶ እከሌ ሙቷል፤ ቀብር ድረሱ’’ ይላሉ። ሌሎችም የቡድኑ አባላት ሩቅ ቦታ ሆነው ልክ እንደሞተ ሁሉ ‘‘ዋይ፣ ዋይ፣ ዋይ፣ ዋይ…’’ እያሉ ለማሳቀቅ ያሳብቃሉ፤ ነገር ግን ይሄ ይደረጋል ከመባሉ ውጭ ብዙን ጊዜ አይከሰትም፡፡
ትውልድ ያላቋረጠ የሕይዎት ዥረት ፍለጋ በትኩስ ድንጋይ ታሽቶ ይፈተናል፡፡ ለአዲስ ዓመት የጥንካሬ መሠረት እና የበረከት ማግኛ መንገድ ሁኖ ይዘልቃል፤ ለውፈረ ለውፈ በምሽት ጨረቃ የደመቀው ባሕላዊ ጨዋታ፡፡
አብዛኛው ግጥም ከመገኛ ቋንቋው ኽምጠኛ ወደ አማርኛ ኪናዊ ሁኖ የተተረጎመ ነው፡፡
ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here