ያለፈው ዓመት የአማራ ክልል የቱሪዝም እንቅስቃሴ ምን ያክል ነበር ?

0
35
ባሕር ዳር: መስከረም 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ዓለም አቀፍ ቅርሶችን ጨምሮ በርካታ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ የቱሪዝም መስህብ ሀብቶች የሚገኙበት ነው፡፡
በክልሉ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች በዘርፉ ተሰማርተው አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ለመኾኑ በ2017 ዓ.ም የአማራ ክልል የቱሪዝሙ ዘርፍ እንቅስቃሴው ምን ይመስል ነበር?
በጎንደር ከተማ የአንድ ሆቴል ሥራ አስኪያጅ የኾኑት አቶ ደሳለኝ ይልማ የጎንደር ከተማ በሺዎች የሚቆጠሩ ጎብኝዎችን የምታስተናግድ ከተማ ናት ብለዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በጸጥታ ችግር ምክንያት በቱሪዝም ዘርፉ ተቀዛቅዞ ነበር፤ በ2017 ዓ.ም በተወሰነ ደረጃ መነቃቃት መፈጠሩን አንስተዋል፡፡ የጥምቀት በዓል በደማቅ ሁኔታ መከበሩ፣ ክልላዊ የባሕልና ኪነ ጥበብ ፌስቲቫል እና ሌሎች ኮንፈረንሶች በጎንደር ከተማ መካሄዳቸው ቱሪዝሙ እንዲነቃቃ አድርገዋል ነው ያሉት።
የጎንደር ከተማ በርካታ የቱሪዝም ጸጋዎች ያለበት ነው ያሉት አቶ ደሳለኝ ለዘርፉ መቀዛቀዝ ዋናው ችግር የሰላሙ ሁኔታ ነው ብለዋል። መንግሥት እና ኅብረተሰቡ ለሰላም በጋራ መሥራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የቅዱስ ላሊበላ እና አካባቢዋ የቱሪስት አስጎብኝዎች ማኅበር ሊቀ መንበር እስታሉ ቀለሙ የላሊበላ ከተማ ዓመቱን ሙሉ ጎብኝዎች የማይለዩት ነበር ብለዋል፡፡ በኮሮና ቫይረስ መከሰት፣ በሰሜኑ ጦርነት እና በአማራ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ዘርፉ ተጎድቶ ቆይቷል ነው ያሉት፡፡
የከተማዋ ዋናው የኢኮኖሚ ምንጭ ቱሪዝም በመኾኑ ከፍተኛ ጉዳት ገጥሟት እንደቆየም አንስተዋል፡፡ በ2017 ዓ.ም በክልሉ ቢሮ በኩል በቱሪዝም ዘርፍ ለተሰማሩ አካላት የማነቃቂያ ሥልጠና መሰጠቱን አንስተዋል፡፡ አልፎ አልፎ በአውሮፕላን የሚመጡ ጎብኝዎች ቢኖሩም የየብስ ትራንስፖርት ላይ ባለው ችግር ምክንያት የሃይማኖት ተጓዦች እንደበፊቱ ዓመቱን ሙሉ እንደማይመጡ ነው የተናገሩት።
ሰላም ለቱሪዝም መነሻ መሰረት በመኾኑ ችግሩን ለመፍታት መንግሥት እና የሚመለከታቸው አካላት ለሰላም ሊሠሩ ይገባል ብለዋል፡፡ በአከባቢው አንጻራዊ ሰላም በመኖሩ ጎብኝዎች ወደ አካባቢው እንዲሄዱ ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዓባይ መንግሥቴ የክልሉ የጸጥታ ሁኔታ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ተጽዕኖ አሳድሮ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ ይሁንና በ2017 ዓ.ም በተፈጠረው አንጻራዊ ሰላም በቱሪዝም ዘርፍ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል፡፡
በቅርስ ጥገና እና እንክብካቤ በኩል ከፌደራል መንግሥት ጋር በመተባበር የጎንደር አብያተ መንግሥታት እና የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ዓለም አቀፍ ቅርሶች ጥገና እየተከናወነ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በክልሉ መንግሥትም 80 ሚሊዮን ብር በመመደብ እና ከ59 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ከማኅበረሰቡ እንዲያዋጣ በማድረግ 156 ቋሚ እና 604 ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ላይ የጥገና እና እንክብካቤ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል፡፡
የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ተገንብቶ መጠናቀቁን ያስታወሱት ምክትል ኀላፊው በደቡብ ወሎ ዞን የሚገኘው የሎጎ ሐይቅ የቱሪስት መዳረሻ ልማት ግንባታ እየተቀላጠፈ መኾኑን አንስተዋል፡፡ በጣና ሐይቅ በሚገኙት ገዳማትን ለጎብኝዎች ምቹ የእግረኛ መንገድ እና የወደብ ግንባታ ሥራዎችም መሠራታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በ2017 በጀት ዓመት ከ12 ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥ እና 27 ሺህ በላይ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ክልሉን መጎብኘታቸውንም ተናግረዋል፡፡ ይህም ከተያዘው ዕቅድ በላይ ነው። በክልሉ የቱሪስት ቁጥር ሳይኾን ፍሰት መረጃ የሚያዝ ሲኾን ይህም በየመዳረሻዎች ከአንድ ጊዜ በላይ የሚቆጠር ቱሪስት መኖሩን ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህም ከ5 ነጥብ 83 ቢሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል፡፡ በክልሉ የነበረው የጸጥታ ችግር ለቱሪዝም እንቅስቃሴው አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳደረ ነበር ያሉት ምክትል ኀላፊው እነዚህ ቱሪስቶች በተንቀሳቀሱባቸው የክልሉ አካባቢዎች ጎብኝዎችን በተገቢው ሁኔታ በመቀበል እና ደኅንነታቸውን በማስጠበቅ በኩል የኅብረተሰቡ ድርሻ የጎላ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ በዘርፉ ከ38 ሺህ በላይ ዜጎች በቋሚ እና በጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፈጠሩንም ገልጸዋል፡፡ እነዚህን ተግባራት ለማከናወን የማርኬቲንግ እና ፕሮሞሽን ሥራዎች እንደተሠሩም ገልጸዋል፡፡
የሀገር ውስጥ ቱሪስት ፍሰትም ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ5 ሚሊዮን ብልጫ እንዳለው ተመላክቷል።
በተያዘው በ2018 ዓ.ም የሚከናወኑ መደበኛ ተግባራትን በተሻለ ከመፈጸም ባለፈ የክልሉን የቱሪዝም ጸጋዎችን በማስተዋወቅ ጎብኝዎችን ወደ ክልሉ ለመሳብ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ አመላክተዋል፡፡
በተለይም ደግሞ የክልሉን ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ክብረ በዓላትን ታሪካዊ ይዘታቸውን እና ዕሴቶቻቸውን ጠብቆ በማክበር የጎብኝዎች መስህብ እንዲኾኑ ለማድረግ እንሠራለን ብለዋል፡፡ ቱሪዝም ሰላም ይፈልጋል ያሉት ምክትል ኀላፊው የክልሉን የመስህብ ሀብቶች በማልማት እና በማስጎብኘት ኅብረተሰቡን ከቱሪዝም ተጠቃሚ እንዲኾን ሁሉም ለሰላሙ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here