ደብረ ዕንቁ ማርያም የአንባዋ ገዳም

0
36

ባሕር ዳር: መስከረም 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ማሕደረ ሰላም ለፊሊጶስ ወወለተ ጴጥሮስ ደብረ ዕንቁ ማርያም የአባቶች እና እናቶች አንድነት ገዳም እንደኾነች ይነገርላታል፡፡ የምትገኘው ደግሞ በደቡብ ጎንደር ዞን ስማዳ ወረዳ የኳሳ ቀበሌ ውስጥ ነው፡፡

ከወረዳው ዋና ከተማ ወገዳ ደቡባዊ ምሥራቅ አቅጣጫ 30 ኪሎ ሜትር የመኪና መንገድ በኋላ መራሜ ከምትባል ከተማ ይደርሳሉ፡፡ ከመራሜ ወደ ደቡብ አቅጣጫ ሰባት ኪሎ ሜትር የእግር መንገድ ተጉዘው ነው ደብረ ዕንቁ ማርያም ገዳም የምትገኘው፡፡

ገዳሟ የምትገኝበት ሥፍራ በተራራ ስትኾን በሸለቆ የተከበበች ናት፡፡ የመውጫ እና መውረጃ መንገዷም አንድ ብቻ ነው፡፡ የተራራው አናትም ብዙ ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ ያስቃኛል።

የገዳሟ አሥተዳዳሪ አባ ኪዳነ ማርያም ገብረ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያኗ ስትተከል ሀቃሊት ጽዮን ማርያም ትባል እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩልም ታቦተ ጽዮን ትባልም እንደነበር አንስተዋል።

አቡነ ፊሊጶስ ከሸዋ ወደ በጌምድር መጥተው ሲያርፉባት ደብረ ዕንቁ ማርያም ብለው ሰየሟት ይላል ታሪኳ። ዛሬ ደግሞ አምባሰል መሄድ ያልቻሉት ስለሚሄዱባትም ዳግማዊ ግሸን ደብረ ከርቤ እየተባለች ትጠራለች፡፡

ከክርስቶስ ልደት 15 ዓመት በፊትም በድንኳን እንደቆየች አመላካች ነገሮች አሉ ያሉት አባ ኪዳነ ማርያም ወደ ገዳምነት የተቀየረችው ግን በአጼ ሰይፈ አርዕድ ዘመን በአቡነ ፊልጶስ እጅ እንደኾነ የጽሑፍ መረጃ መኖሩን ገልጸዋል።

በግብጻዊው ጳጳስ አቡነ ሰላማ የተጻፈ የአቡነ ፊልጶስ ሃይማኖታዊ ተጋድሎም በሰነድነት ይገኛል።

የአቡነ ፊሊጶስ ደቀ መዝሙር የነበሩት ጻድቁ አባ ተከስተ ብርሃንም የደብሩ የበላይ ኾነው ማገልገላቸውን እና በትረ መስቀላቸውን እና የእጅ መስቀላቸው በገዳሟ መኖሩን ገልጸዋል፡፡ ገድላቸውም በገዳሟ ይገኛል፡፡

ቅድሥት ወለተ ጴጥሮስም ወደ ገዳም ስትገባ የመጀመሪያ ገዳሟ ደብረ ዕንቁ ማርያም እንደኾነች ይነገራል። በዚህች ገዳምም ለ17 ዓመታት ቆይታለች። የቤተ ክርስቲያኗ አቀማመጥ እና መውጫ መግቢያው አንድ ብቻ መኾኑ ከግሸን ደብረ ከርቤ ጋር ያመሳስላታል፡፡

የታነጸችውም በበርሐ በሚገኝ የተለየ ድንጋይ ነው። ይህንን ድንጋይ ወደ ተራራው ለማዝለቅም መንፈሳዊ ኃይል አገልግሎት ላይ እንደዋለ ይታመናል፡፡

ቤተ ክርስቲያኗ የቃጠሎ አደጋ ደርሶባት እንደነበር የጠቀሱት አባ ኪዳነ ማርያም እንደ መጽሐፈ ጤፉት ያሉ የሃይማኖት ታሪክ የያዘ ቅርስ ቅጅ እንደነበራት አውስተዋል፡፡ በቅርቡም ካለበት ቦታ ተቀድቶ እንደመጣ ገልጸዋል፡፡

መስከረም 21 የመስቀሉ፣ ሕዳር 21 የታቦተ ጽዮን፣ ሕዳር 17 የቅድስት ወለተ ጴጥሮስ መታሰቢያ፣ ሐምሌ 28 የአቡነ ፊሊጶስ ረፍት በቦታው ይከበራል፡፡ ገዳማውያኑ እና ምዕመኑ ቅዳሴ በሌለበት ጊዜ እንኳ የእጣን መዓዛ እንደሚሸታቸው ይናገራሉ።

በገዳሙ ከ40 በላይ መነኮሳት ይኖራሉ፡፡ በመቃብር ቦታዎች እና በዛፎች ሥር የሚኖሩት መነኮሳት ውኃ ጥሙን እና ረሐቡን ተቋቁመው ለሀገር ይጸልያሉ።

ገዳማውያኑ ከቤተ ክርስቲያኗ ጣሪያ የሚጠራቀመውን እና ከአካባቢው ሕዝብ በሰንበት የሚመጸውታቸውን ውኃ ይጠቀማሉ። በዚያ ውስጥም ረዳት የሌላቸውን ደካሞች ይደግፋሉ፡፡

በገዳሟ ዙሪያ የሚመረተው ማር መድኃኒትነቱ የተመሰከረለት እንደኾነም ይነገራል፡፡ ታማሚዎቹ በአልጋ መጥተው በእግራቸው ይመለሳሉ ነው ያሉት አባ ኪዳነ ማርያም።

ከገዳሟ አናት ጀምሮ እስከ ታችኛው ቦታ ድረስ ያሉ ማረፊያ ቦታዎች የቀድሞ ግብራቸውን እና ስያሜያቸውን ይዘው ይገኛሉ፡፡

አንበሳው ማሰሪያ፣ አይገድል አይገደል፣ ትልቁ ጎራ፣ ትንሹ ጎራ፣ ምዕራፍ፣ ግዝት በር፣ የሚባሉ ቦታዎች ሁሉ የቀድሞ ታሪኮች ስያሜ መኾናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡ ሰው ሲሞት ከመቀበሩ በፊት ፍትሐት የሚፈጸምበትም አቡነ ፊሊጶስ ከሸዋ መጥተው ያረፉበት ቦታን ታሳቢ ተደርጎ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡

ደብሯ በተፈጥሮ ነጻነት አላት። ዙሪያ ገባውን ለመቃኘትም ምቾት አላት፡፡ በዚህም ነገሥታት በክረምትም፣ በእረፍታቸው ወይም ለሱባኤ ያሳለፉባት ነበር፡፡ የአጼ ዘርዕያ ያዕቆብ መስቀል፣ መጽሐፈ ጤፉት፣ የመሳሰሉት ቅርሶች ባለፉት ዘመናት የተሰጧት ቅርሶች ናቸው።

የቅድስት ወለተ ጴጥሮስ በገዳሟ ቆይታዋ ውኃ እየቀዳች ስትመላለስ ታርፍበት የነበረችው የድንጋይ ወንበር ክብሯ የተገለጸበት ቦታ ለመታሰቢያ መኖሩንም አንስተዋል፡፡

ወደ አንባዋ መዝለቂያ መንገዱ ጠባብ እና አስፈሪ ነው። አስፍቶ ለመሥራትም ይፈርሳል ተብሎ ስለሚታመን ለማሻሻል እንዳልተሞከረ ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ:- ዋሴ ባዬ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here