“ርእሰ ርዑሳን መርጡለ ማርያም ገዳም”

0
14
ባሕር ዳር: መስከረም 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የርእሰ ርዑሳን መርጡለ ማርያም ገዳም ከአዲስ አበባ 364 ኪሎ ሜትር፣ ከባሕር ዳር 181 ኪሎ ሜትር እና ከደብረ ማርቆስ ከተማ 191 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ታሪከ ብዙ ገዳም ናት።
የገዳሙ ቅርስ ክፍል ዋና ኀላፊ ቆሞስ አባ ተስፋማርያም እንዳይላሉ ታሪካዊቷ መርጡለ ማርያም ገዳም በ333 ዓ.ም በአብርሐ ወአጽብሐ ዘመነ መንግሥት እንዴት እና በምን ሁኔታ እንደተሠራች በገድለ አብርሐ ወአጽብሐ ላይ በቀደምት አባቶች ተጽፎ እንደሚገኝ ነግረውናል።
ለገዳሟ የወጣላት ስም በአዲስ ኪዳን አሁን የምትጠራበት ርእሰ ርዑሳን መርጡለ ማርያም፤ በሕገ ልቦና ሀገረ እግዚአብሔር፤ በሕገ ኦሪት ደግሞ ሀገረ ሰላም እና ጽርሐ አርያም እንደነበር ነው የገለጹት።
በገዳሟ የሚንቀሳቀሱ እና የማይንቀሳቀሱ ዕድሜ ጠገብ ቅርሶች መኖራቸውን ተናግረዋል። የሚንቀሳቀሱት ቅርሶች በቦታ ጥበት ምክንያት በአንድ ላይ ታምቀው እንደሚገኙ ገልጸውልናል። በዚህም ቅርሶች በተለያየ ሁኔታ ጉዳት እየደረሰባቸው መኾኑን ጠቁመዋል።
ጎብኝዎች በብዛት ወደ ገዳሟ የሚሄዱት ጥቅምት አራት ቀን ለሚከበረው የአብርሐ ወአጽብሐ የእረፍት ቀን እና ጥር 21 ለሚከበረው የአስተርዮ ማርያም የንግስ በዓል መኾኑን ቆሞስ አባ ተስፋማርያም ገልጸዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከቤተ ክርስቲያኗ ሕንጻ ጋር እየተሠራ የሚገኝ ሙዚየም መኖሩን የጠቀሱት ቆሞስ አባ ተስፋማርያም በመጠናቀቅ ላይ የሚገኝ ቢኾንም ቀሪ ሥራዎችን ለመተግበር ከወቅቱ አኳያ የገንዘብ እጥረት ስለገጠመ ሥራው የመቆም ሁኔታ እንደገጠመውም አንስተዋል።
ታሪክ ለትውልድ እንዲተላለፍ እና ትውልድ እንዲገለገል በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ የሚኖሩ በጎ አሳቢዎች እንዲደግፉም ጥሪ አቅርበዋል።
የእነብሴ ሳር ምድር ወረዳ ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የቅርስ ጥበቃ እና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ ተመስገን እባቡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሕገ ኦሪት ይመለክባቸው ከነበሩት ከአክሱም ጽዮን፣ ከተድባበ ማርያም እና ጣና ቂርቆስ መካከል መኾኗን ነው የተናገሩት። ከአክሱም ጽዮን በመቀጠል ሁለተኛ ኾና እንደተሠራችም ገልጸውልናል።
እንደ ወረዳ ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት በሳይንሳዊ ቆጠራ ያረጋገጧቸው በርካታ ቅርሶች በገዳሟ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል። በ333 ዓ.ም አብርሐ ወአጽብሐ በነገሱበት ጊዜ በነገስታቶቹ አማካኝነት ተሠርቶ የነበረ ባለ 12 ቤተ መቅደስ የነበራት ገዳም ናት ነው ያሉት።
ይህ የማይንቀሳቀስ ቅርስ በ840 ዓ.ም አካባቢ ዮዲት ጉዲት በነገሰችበት ጊዜ ጉዳት ቢደርስበትም የኪነ ሕንጻው የአሠራር ጥበብ ድሮ በነበረው ቁመና እና ውበት ላይ ባይኾንም ሕያው የታሪክ ምስክር ኾኖ አሁንም ይገኛል ብለዋል።
የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ በ1990 ዓ.ም የከለላ ሥራ ሠርቶለት እንደነበርም ተናግረዋል። በ2010 ዓ.ም ደግሞ እንጨቱን ወደ ብረት የመቀየር ተግባር ተሠርቶለታል ነው ያሉት። ጥገናው ግን ከመፍረስ እና ከጉዳት እንዳላዳነው ተናግረዋል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥናት ተደርጎ ጥገና የማይደረግለት ከኾነ የምናየውን ቅርስ እናጣዋለን ሲሉም አሳስበዋል።
ከኪነ ሕንጻ ባሻገር የንግሥት ኢለኒ እና ራስ ኃይሉ ውድሞች (የነገሥታት ዙፋን ይቀመጥበት የነበረ፣ አካባቢውን ያሥተዳድሩበት እና ፍርድ ይሰጡበት የነበረ ቦታ)፣ የማይንቀሳቀሱ ቅርሶች ኾነው ተመዝግበው ይገኛሉ ነው ያሉት።
የነገሥታት ዘውዶች፣ አክሊሎች፣ የራስ ቁሮች፣ ካባዎች እና አልባሳቶች (የንግሥት ኢለኒ፣ የራስ ኃይሉ እና የግራኝ አሕመድ)፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ስትገለገልባቸው የነበሩ እና አሁንም እየተገለገለችባቸው የሚገኙ ከ200 የማያንሱ የብራና መጽሐፍት፣ ከወርቅ፣ ከብር እና ከነሐስ የተሠሩ እና ሌሎች ንዋየ ቅዱሳት ያሉባት መኾኗንም ተናግረዋል።
ከቅርስ ክምችት አንጻር ቅርሶች ብዛት ያላቸው በመኾኑ አሁን ላይ የተቀመጡበት ሁኔታ ለጉብኝት ምቹ ያልኾነ እና እርስ በርስ የተጨማመቀ እና አስጊ ሁኔታ ላይ ያሉ መኾናቸውንም ገልጸውልናል።
በክልሉ መንግሥት እና በኅብረተሰቡ ተሳትፎ ደረጃውን የጠበቀ ሙዚየም እየተገነባ እንዳለ እና የማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
የበር፣ የመስኮት እና የማስዋብ ሥራዎች መቅረታቸውን ነው የተናገሩት። በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሁኔታ ሥራው እንደተጓተተ ገልጸዋል። ይሁንና በዚህ ዓመት ለማጠናቀቅ እየተሠራ እንደኾነ ነው የገለጹልን። ለቅርሶችም ይደርስላቸዋል ብለን ተስፋ አድርገናል ነው ያሉት።
በጥር ወር የአስተርዮ ማርያም የንግሥ በዓል ሲከበር ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ቁጥራቸው እስከ 100 ሺህ የሚደርሱ ጎብኝዎች እንደሚተሙ ነው ቡድን መሪው የገለጹልን።
እንደ ወረዳ ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ቅርሶችን የማስተዋወቅ ጅምር ሥራዎች ቢኖሩም እንኳ ባላቸው ታሪክ ልክ ግን የማስተዋወቅ ሥራ እንዳልተሠራ ገልጸዋል።
የሙዚየሙን ግንባታ በተያዘው ዓመት አጠናቅቆ ቅርሶችን ከጉዳት ለማዳን ማኅበረሰቡ ሲያደርግ የነበረውን ተሳትፎ እንዲቀጥል ጥሪያቸውንም አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here