መስቀል በአገው ምድር

0
31
ባሕር ዳር: መስከረም 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “ድሩፃ” በአገውኛ ቋንቋ እንኳን አደረሳችሁ ማለት ነው። የጽሑፋችን መቆያም እዚያው በገጠሩ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አካባቢ ስለኾነ “ድሩፃ!” ብለን እንጀምራለን።
መስቀል በሁሉም የኢትዮጵያ ገጠራማ አካባቢዎች በእሸት እና አበባ ታጅቦ የሚከበር የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች በዓል ነው። በዓሉ በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ውስጥ በገጠራማው አካባቢ ልዩ መልክ አለው። በዚህ ቀን እንኳንስ ሰዎች የቤት እንስሳት ሁሉ “ድሩፃ” እየተባሉ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ይደርሳቸዋል። አቶ መሠረት ወርቄ በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ውስጥ የሚኖሩ እና የመስቀልን በዓል በገጠሩ አካባቢ በስፋት የሚያከብሩ አባት ናቸው። አቶ መሠረት በዓሉ በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ያለው አከባበር ምን እንደሚመስል ነግረውናል።
“ጳጉሜን እንዳለቀ የመስቀል በዓል ዝግጅት ይጀመራል” ነው ያሉን። አሮጌው ዓመት አልፎ አዲሱ ዓመት ከሚገባበት የእንቁጣጣሽ ቀን ጀምሮ እስከ መስቀል ዋዜማ ድረስ ሽርጉዱ ይደምቃል ማለታቸው ነው። ወንዶች እና ሴቶች ሁሉም የራሳቸውን ዝግጅት ያደርጋሉ። ወንዶች ወደ ጫካ ወርደው ለደመራ የሚኾን እንጨት እና ግንድ ያዘጋጃሉ። የደመራ እንጨት እና ግንዱ የመስቀል ዋዜማ ደርሶ ወደ ሚቃጠልበት ቦታ እስከሚሰበሰብ ድረስ በዚያው በጫካ ይቆያል። ችቦ ማዘጋጀትም ሌላው የወንዶች ሥራ ነው። ችቦው የሚዘጋጀው ድንቅ ሽታ ካለው “ከሴ” የተባለ ተክል ነው።
ሴቶችም ለመስቀል በዓል ሰፊ ዝግጅት ያደርጋሉ። ለመስቀል በዓል የሚዘጋጀውን “ጉዝጉዞ” የተባለ ጣፋጭ ምግብ ይሠራሉ። ጉዝጉዞ በቅቤ እና በርበሬ የተቀባ ድርብ እንጀራ ነው ብለውናል። “ሻሽኮይ” የተባለው ምግብም ይዘጋጃል። የሻሽኮይ አዘገጃጀት እንደ ጉዝጉዞ ኾኖ እንጀራው ግን ድርብ ሳይኾን ነጠላ ነው። በሁለቱም ምግቦች ላይ የሚጨመረው ቅቤ የሚዘጋጀው በልዩ ጥንቃቄ ነው። ከጫካ ተቆፍሮ የሚመጣ “መቅመቆ” የተባለ ተክል ስሩ ተደቁሶ ይጨመርበታል። ይህም እርድ መሰል ቅመም ነው። መቅመቆ ለሚዘጋጀው ጉዝጉዞ እና ሻሽኮይ ልዩ ቀለም እና ጣዕም ይሰጠዋል።
ጠላ በአዊ ብሔረሰብ ለመስቀል በዓል የግድ መገኘት ያለበት መጠጥ መኾኑንም ነግረውናል። ይህንን እውነት ለማሳየት ሳይኾን አይቀርም” በአዊ ብሔረሰብ ለመስቀል በዓል እንኳንስ ሰው ወፍም በዛፍ ቅርፊት ትጠነስሳለች” የሚባለው። ከእንቁጣጣሽ ጀምሮ ሽር ጉድ የተባለለት የመስቀል በዓል ዋዜማው ሲደርስ ወንዶች በየጫካው ያስቀመጡትን የደመራ እንጨት እና ግንድ ይሰበስባሉ። በመስቀል ዋዜማ ወንድ ልጆች “ባላፉቺ” የተባለ የተላጠ እንጨት እና ሻሽኮይ ይዘው ወደ ማሳ ይወርዳሉ። “አረሙን አጥፋው፤ ሰብሉን ወደ ላይ አውጣው” እያሉ እንጨቱን ከየአዝመራው መካከል ይተክላሉ። ከያዙት ሻሽኮይ ይቆርሱና ከተተከለው “ባለፉች” ላይ በትንሹ ያስቀምጣሉ። የቀረውን በዚያው ተቀምጠው ይቀማምሳሉ።
በመስቀል ዋዜማ ችቦ ይታሰራል። የሰፈር ሰዎች በጋራ ከሚያቃጥሉት ደመራ በተጨማሪ በተመረጡ አባቶች ቤት በር ላይ ትንንሽ ደመራም ይተከላል። ደመራው በሚደመርበት ወቅት ጉዝጉዞው፣ ሻሽኮዩ፣ ጠላው እና ሌላውም ባሕላዊ ምግብ እና መጠጥ ይቀርባል። ይበላል ይጠጣል።
በዚሁ ቀን አመሻሽ ላይ የሰፈሩ ትልቅ አባት ተመርጦ ግንድ ማቃጠል ይጀመራል። የሚዘጋጀው ግንድ ዋርካ፣ ግራር፣ ወይም ምሳና ኾኖ ጭስ ሊያወጣ የሚችል መኾን አለበት። ጭሱ እንደ እጣን ይቆጠራል። የሰፈሩ ሰዎች “ኩኩ” በሚል ድምጽ እየተጠራሩ የተዘጋጀውን ግንድ ወደ ተመረጠው አባት ቤት ያስገቡና ለቤቱ አደጋ በማይፈጥር መልኩ በጥንቃቄ ያቃጥላሉ። አባት “ድሩፃ” ይባላል። እሱም “ሊኻ ሻይ አሜታ ታምፕ ” ይላል። መቶ ሺህ ዓመት ያድርሰን ማለት ነው። ዓመቱ የሰመረ እንዲኾንም አባት ይመርቃል። እስከ ሌሊቱ ሰባት ሰዓት ድረስ በየቤቱ እየተዞረ ይሄው ግንድ የማቃጠል ሥርዓት እና ምርቃት ይቀጥላል።
ግንድ በማቃጠል ሥርዓቱ ላይ አምሽተው የደከሙት ሁሉ አርፈው ያድሩና መስከረም 17 ጥዋት ዋናው የመስቀል በዓል አከባበር ይጀመራል። የሰፈሩ ሰዎች የተዘጋጀውን ባሕላዊ መብል እና መጠጥ እየያዙ በጋራ ወደ ተዘጋጀው ደመራ ይመጣሉ። ወንዶች ችቦ ይዘው በደመራው ዙሪያ ይሰባሰባሉ።
ከአንድ አባወራ ቤት የሚዘጋጀው ችቦ ቁጥር በቤቱ ውስጥ ከሚኖሩት ወንዶች እኩል መኾን አለበት። አራት ወንድ ልጆች ካሉ የአባትን ጨምሮ አምስት ችቦ ይዘጋጃል ማለት ነው። የልጆች እድሜ አምስት ዓመት ወይም ከዚያ በታች ኾኖ ችቦውን መያዝ እና ማብራት ባይችሉ እንኳን ታላቅ የኾነው ወንድማቸው ደርቦ በመያዝ ያበራላቸዋል። በአዊ ብሔረሰብ በሕይወት የተለየ አባትም ለሁለት ተከታታይ ዓመታት የመስቀል ችቦ ይዘጋጅለታል። ሁለት ዓመት እስከሚሞላው ድረስ ሞቷል ተብሎ የቤቱ ችቦ ቁጥር አይጎድልም ማለት ነው። ልጅ ከራሱ በተጨማሪ በቅርቡ በሕይወት የተለየ አባቱን ችቦ የማብራት ድርብ ኀላፊነት አለበት።
በአዊ ብሔረሰብ ደመራ የማቃጠል ሂደቱም ልዩ ነው። ደመራ ለመለኮስ ሰዎች በጡሩንባ ድምጽ ይጠራራሉ። ቅድሚያ “እንኳን አደረሰን” ተብሎ ጉዝጉዞ ይቆረሳል። ወንዶች ችቦ ለኩሰው በደመራው ዙሪያ ይዞራሉ። ሴቶችም በዙሪያው ኾነው ይጨፍራሉ። ሦስት ጊዜ ከተዞረ በኋላ የሃይማኖት አባቶች ካሉ ጸሎት ያደርሳሉ፤ ሽማግሌዎችም ይመርቃሉ። ታላቅ የተባለው አባት ተመርጦ “ድሩፃ” ካለ በኋላ በያዘው ችቦ ደመራውን ማቃጠል ይጀምራል። ሌላውም መለኮስ ይቀጥላል። የደረሱ የበቆሎ እና ሌሎችም እሸቶች ወደ ደመራው እሳት ውስጥ ተጨምረው ይጠበሳሉ። በመጀመሪያ የሚበላው ይሄው እሸት ነው። በመቀጠልም እርድ ይፈጸምና ሥጋው፣ ጉዝጉዞው፣ ሻሽኮይ፣ ጠላ እና አረቄ በየአይነቱ ቀርቦ ሁሉም እንደየፍላጎቱ በጋራ ይስተናገዳል።
ደመራው ተለኩሶ፣ ተበልቶ እና ተጠጥቶ ከተመረቀ በኋላ ወንዶች በዚሁ በደመራው ቦታ አካባቢ ይቆያሉ። ሴቶች ግን ወደ ቤት ይመለሱና የልምላሜ ምልክት የኾነውን “ግራምጣ” በእጃቸው በመያዝ “ድሩፃ” እያሉ እና እየጨፈሩ ወደ ታላላቅ አባቶች ይዘልቃሉ። በዚያም ቤት ጉዝጉዞ እየተዘጋጀ ይቀርብላቸዋል። ይህ ሴቶች የሚደሰቱበት እና በየቤቱ እየተዘዋወሩ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት የሚያስተላልፉበት የበዓሉ አንዱ ተወዳጅ ኹነት ነው። በዚህ መልኩ የመስቀል በዓል ይጠናቀቃል።
አቶ መሠረት እንደሚሉት የመስቀል በዓል በዚህ መልኩ ቢጠናቀቅም በየቤቱ እየተጠራሩ ቤት ያፈራውን በጋራ የመመገቡ ሂደት በቀጣዮቹ የመስከረም ቀናትም ይቀጥላል ብለዋል። ይህ የአዊ ብሔረሰብ የመስቀል በዓል አከባበር ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ ትውፊቱን ጠብቆ እንዲዘልቅ የበኩላቸውን እየተወጡ መኾናቸውንም አቶ መሠረት አመላክተዋል። ሌሎችም የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ወጣቶች የበኩላቸውን በማበርከት የአዊ ብሔረሰብ የመሥቀል በዓል አከባበር ሥርዓቱን የጠበቀ እና ራሱን ችሎ የቱሪስት መስህብ እንዲኾን መሠራት እንዳለበትም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here