ጎንደር: መስከረም 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የቱሪዝም ሚኒስቴር የጎንደር የቀደሞ ነገሥታት በአጼ ፋሲል አብያተ መንግሥታት አኗኗራቸው ምን እንደሚመስል የሚዘክር “ሕይዎት በአብያተ መንግሥት” በሚል መሪ መልዕክት ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ሁነቱን የሚያሳይ የማስጀመሪያ መርሐ ግብር አካሂዷል።
የመርሐ ግብሩ ዓላማ ቀደምቶቻችን ያቆዩትን ታሪክ፣ ወግ እና ባሕል ሰንዶ ለጎብኝዎች ማስተዋወቅ መኾኑን የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል። ቀደምቶቻችን ያቆዩትን ታሪክ፣ ወግ እና ባሕል ሰንዶ ለጎብኝዎች ማስተዋወቅ እንደሚገባም ሚኒስትሯ አስታውቀዋል።
ጎብኝዎች ኪነ ሕንጻውን ከመጎብኘት ባሻገር የነገሥታት ውሎ ምን ይመስል እንደነበር እንዲያስታውሱ እንደሚያግዝም አንስተዋል።
የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት የተጀመረው ውጥን ትልቅ ፋይዳ አለው ያሉት ሚኒስትሯ የጎብኝዎችን የቆይታ ጊዜ ያራዝማልም ብለዋል።
የተጀመረውን ተግባር አጠናክሮ ለማስቀጠል ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራ የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ መልካሙ ጸጋየ ናቸው።
አማራ ክልል ያልተነካ ጸጋ እና ተውፊት አለው ያሉት ቢሮ ኀላፊው ትውልዱ ከቀደምቶቹ ታሪክን መማር አለበት ብለዋል።
ከቀደምቶቹ ታሪክ ለመማር ደግሞ ያሉትን ቅርሶች ማወቅ፣ መንከባከብ እና መጠበቅ ይኖርበታል ነው ያሉት።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው በበኩላቸው በከተማው ሰባት ቅርሶች በዓለም ቅርስ መዝገብ መመዝገባቸውን አስታውሰዋል።
እነዚህን ሃብቶች ለጎብኝዎች በሰፊው ለማስተዋወቅም እየተሠራ መኾኑን አስረድተዋል። ለጎብኝዎች ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ ነውም ብለዋል።
ዘጋቢ:- አዲስ ዓለማየሁ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!