ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ ጥቅምት ሰባት የሥላሴ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል ይከበራል።
በሰሜን ጎጃም ዞን ይልማና ዴንሳ ወረዳ ከአዴት ከተማ በ5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የጻድቁ አቡነ ዘርዓ ብሩክ ገዳም ላይም ይሄው በዓል ይከበራል፡፡ ቀኑም ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ትዕይንት በየፈርጁ የሚታዩበት ነው።
የጺማ ደብረ ምህረት አቡነ ዘርአብሩክ ገዳም አሥተዳዳሪ መላከ ምህረት ጌታነህ አድማስ የጺማ ደብረ ምህረት አቡነ ዘርአብሩክ ገዳም በ16ኛው ክፍለ ዘመን መመስረቱን ተከትሎ ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ባሻገር በጊዜ ሂደት ከበዓሉ ትይዩ በዓመት አንድ ጊዜ የሚውል ባሕላዊ ገበያ መኖሩን ገልጸውልናል።
ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ እና ባሕላዊ ገበያው ጥቅምት ሰባት ቀን የመኾኑ ምክንያትም ጻድቁ አቡነ ዘርዓብሩክ ገዳሙን ገንብተው ያጠናቀቁበት ከመኾኑ ጋር የተያያዘ እንደኾነ አንስተዋል።
መላዕከ ምህረት ጌታነህ አድማስ በቀደመው ጊዜ ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ገዳሙ ለጸበል የሚመጡ ሰዎች ስንቃቸውን በጋማ ከብቶች ጭነው ነበር ነው ያሉት።
ድኅነት አግኝተው ወደቀያቸው ሲመለሱ የተረፋቸውን ስንቅ እና የጋማ ከበቶች ስጦታ የመስጠት እና የመሻሻጥ ኹኔታ ነበር፤ ያንን ምክንያት በማድረግ ባሕላዊ ገበያው እንደተጀመረ ታሪክ ያስረዳል ብለዋል።
በባሕላዊ ገበያው ባሕላዊ እና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው ቁሳቁሶች ሽያጭ እና ግዥ እንደሚከወን ነው የነገሩን። የጋማ ከብቶች ማጌጫ ባሕላዊ ጌጣጌጦች፣ አልባሳት፣ የአርሶ አደሮች የግብርና እቃዎች፣ ጠገራ ብርን ጨምሮ በተለያዩ ዘመኖች ሲያገለግሉ የነበሩ መገበያያ ሳንቲሞች፣ ብራና፣ የቤተክርስቲያን ንዋየ ቅዱሳትን ለማሳመር እና ጽሑፎችን ለመጻፍ የሚያገለግሉ የብዕር ቀለሞች፣ የጋማ ከብቶቸ፣ ባሕላዊ ምግብ እና መጠጦች ለሽያጭ እንደሚቀርቡም ጠቅሰዋል።
ቀደም ባሉት ዓመታቶች ባሕላዊ ገበያው ላይ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እና ከውጭ ሀገር የተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ይታደሙ እንደነበር አስታውሰዋል።
በተለይም ደግሞ ከብዙ ዓመት በኋላ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የሰላም ስምምነት በተደረገበት ወቅት ኤርትራውያንም ተሳታፊ እንደነበሩ ገልጸዋል።
ከሀገር ውስጥ ደግሞ አጎራባች የኾኑ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች እንደሚታደሙ ነግረውናል። በብዛት ከዋሸራ፣ ከቋሪት፣ ከደጋዳሞት፣ ከእስቴ እና አካባቢው፣ ከአዊ ዞን እና ሌሎች አካባቢዎች ይታደሙ እንደነበር ነው የነገሩን።
ለባሕላዊ ገበያው ካላቸው ጉጉት አንጻርም በእግራቸው አቆራርጠው ለሽያጭ እና ለግዥ ይመጡ እንደነበርም አስታውሰዋል።
ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን በአማራ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት እየተቀዛቀዘ መምጣቱን ነው የጠቀሱት።
የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር መልካሙ አዳም የጥቅምት ስላሴ ዓመታዊ ባሕላዊ ገበያ እና ሃይማኖታዊ ሥርዓት ከጥንት ጀምሮ ሲከበር ነበር ነው ያሉት።
ለሃይማኖታዊ ሥርዓቱ እና ለግብይት ለሚሄዱ እንግዶች እዛው ገበያው ላይ ምግብ እና ባሕላዊ መጠጥ እንደሚሸጥም አንስተዋል። ከዚያው ገበያው ላይ እንግዳ የሚሸኝበት ሁኔታ ለየት ያደርገዋልም ነው ያሉት።
አብዛኛው ሰው ከጥቅምት ስድስት ጀምሮ ቦታው ላይ እንደሚገኝም ነግረውናል። በበዓሉ ዕለትም በአይነቱ ለየት ያለ የፈረስ ግልቢያ ውድድር እንደሚካሄድ ነው የገለጹት። ባሕላዊ ገበያው በ18 እና በ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ይከበር እንደነበር የሚነገርለት ነው ብለዋል።
የታሪክ መዛግብት እንደሚያስረዱትም ከአረብ ሀገር ድረስ የሚመጡ ታዳሚወች በገበያው ላይ ይሳተፋ ነበር ነው ያሉት።
ሁነቱ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ፋይዳ ያለው ነው ያሉት ዳይሬክተሩ የተለያዩ አካባቢ ማኅበረሰቦች በዓመት አንድ ጊዜ የሚገናኙበት በመኾኑ የእርስ በርስ ግንኙነት መፍጠሪያ፣ ስለቀያቸው መወያያ፣ የተጣሉ አካባቢዎችን ለማስማማት መገናኛ ኾኖ እንደሚያገለግልም አንስተዋል። ተናፋቂ ሁነት መኾኑንም ጠቅሰዋል።
ከዚህ በፊት የሁነቱ አከባበር በኮቪድ መከሰት እና በክልሉ በተፈጠረ የጸጥታ ችግር ቢቀዛቀዝም በተቻለ መጠን ሲከበር ቆይቷል ነው ያሉት።
ባሕላዊ ገበያው በሀገር እና በክልል ደረጃ በቅርስነት ተመዝግቦ ይገኛል፤ የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮም የማስተዋወቅ ሥራ ሲያከናውን ቆይቷል ነው ያሉት።
ዓመታዊ ባሕላዊ ገበያው ትውፊቱን ጠብቆ እንዲከበር እና ለትውልድ እንዲሸጋገር ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ ያለው የባሕል እና ቱሪዝም መዋቅር ከኅብረተሰቡ እና ከሃይማኖት አባቶች ጋር በመተባበር ሢሠራ ቆይቷል፤ ቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በዘንድሮው ዓመትም ነባር ይዘቱን ጠብቆ እንዲከበር ሥራዎች እየተከናወኑ እንደኾነ ተናግረዋል።
በተለያየ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎችም በዘንድሮው የጥቅምት ሥለሴ ሃይማኖታዊ ሥርዓት እና ባሕላዊ ገበያ ላይ እንዲሳተፉም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!